ያቤሎ ብሔራዊ ፓርክ

0
27

ብሔራዊ ፓርኩ ከዋና መዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 565 ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን ነው የሚገኘው:: የፓርኩ ስፋት 2500 ሜትር ሲሆን መልካ ምድራዊ አቀማመጡም ዝቅተኛው 1400 ሜትር፣ ከፍተኛው 2000 ሜትር ተለክቷል4 አማካዩም 1700 ሜትር መሆኑን ልብ ይሏል::

የፓርኩ ከባቢ ዓመታዊ ዝናብ መጠን በአማካይ 700 ሚሊ ሜትር ነው:: ከፍ ያለ የዝናብ መጠን  የሚጥለው በጥር እና የካቲት ወራት መሆኑንም ድረ ገፆች አስነብበዋል::

የዓየር ንብረቱ ወይና ደጋ የሚባል ነው፤ ቀዝቃዛው 13  ዲግሪ ሴልሺየስ፣ ሙቀቱ ደግሞ 25 ዲግሪ ሴልሺየስ ተለክቷል፤ አማካይ  19 መሆኑ ነው:: በጣም ሞቃቱ የአየር ንብረትም በጥር እና የካቲት ወራት ተመዝግቧል::

የፓርኩ መገኛ  የአፈር አይነቱ ቀይ ሲሆን  ቀጣናው በለበሰው  የግጦሽ ሳር መካከል የግራር ዛፍ በርከት  ብሎ ይታያል:: ቀደም ባሉት ዓመታት በየኮረብታው ከፍተኛ  ቦታዎች “ጃኒፐርስ ኘሮሴራ” ወይም የጥድ ዛፍ ነበር የሚታይባቸው:: ዛሬ ላይ ግን የጥድ ዛፍ ሳይሆን ግራር እና ሳር ለበስ ሆኗል::

በፓርኩ 210 የዓዕዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውም ተመዝግቧል፤ ከነዚህ ውስጥ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡት  “ቡሽ ክሮው” እና  “ኃይት ቴይልድ ስፓሮው” መገኘታቸው ተረጋግጧል:: ከሁሉም በበለጠ ባለግርማ ሞገሷ ሰጐን፣ የሶሟሌ “ ስፓሮ” እንደሚገኙ ነው የተጠቀሰው:: በአካል ግዝፈት ካላቸው የዱር አራዊት ቆርኬ “ስዋይን ኸርት ቢስት”፣ የሜዳ አህያ እና   የሜዳ ፍየል በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ::

ፓርኩ ለጐብኚዎች ዓመቱን ሙሉ ክፍት ቢሆንም በአየር ንብረቱ ምቹነት የዝናብ መጠኑ አነስተኛ የሆነበት ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት ወራት ተመራጭ ናቸው:: በዚህ ወቅት የዕፅዋት ሽፋኑም ጥቅጥቅ ባለመሆኑ ጐብኚዎች እንደፈለጉ ለመመልከት ወደ አካባቢው ይተማሉ::

የፓርኩ ጐብኚዎች ማረፈያ፣ ምግብ እና መጠጥ የሚያገኙባቸው እንደየአቅማቸው እና ፍላጐታቸው ቅንጡ ማረፊያ ሎጂዎችም ተዘጋጅተዋል:: ከዚህ ባሻገር በፓርኩ ክልል ውስጥ በተመቸ ቦታ ድንኳን ተክለው በቅርበት የዱር አራዊት ለመመልከት፣ የአፅዋፉን ዝማሬ ማድመጥም ያስችላል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኢትዮጵያን ዋይልድ ላይፍ፣ ባሌ ማውንቴንስ ትራኪንግ እና ሎንሊ ኘላኔት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here