ያንጉዲ ራሳ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ነው የሚገኘው:: ፓርኩ ያንጉዲ ተራራን እና በዙሪያው የከበበውን የተንጣለ የራሳ ሜዳ አካቶ የያዘ ቀጣና ነው:: ፓርኩ በ1917 እ.አ.አ ነው እውቅና አግኝቶ የተመሠረተው::
ያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ 284 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በገዋኔ ከአዋሽ ወደ ሚሊ ከተማ በሚወስደው ጐዳና መድረስ ይቻላል:: የፓርኩ ስፋት 4731 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ሲሆን ከቀጣናው 1383 ሜትር የተለካው ተራራ እና በዙሪያው የሚገኘውን የራሳ ሜዳንም ያጠቃልላል::
የፓርኩ ቀጣና የዓየር ሁኔታ ደረቅ እና ሞቀታማ ሲሆን ከፍተኛው 42 ዲግሪ ሴልሺየስ ተለክቷል:: ዝናብ የሚጥልባቸው ሁለት ወቅቶች ሲሆኑ ከ200 እስከ 400 ሚሊ ሜትር ተመዝግቧል::
የፓርኩ መልካምድር ሜዳማ ይበዛዋል፤ ሣር፣ ቁጥቋጦ እና አልፎ አልፎ የግራር ዛፍም ይታይበታል::
የፓርኩ ዋና ጣቢያ ከአዲስ አበባ 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በገዋኔ ከተማ ነው የሚገኘው::
በፓርኩ 230 የዓእዋፍ ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጦ ተመዝግበዋል:: ቀጣናው ከተለያዩ አቅጣጫ ለሚፈልሱ የአእዋፍ ዝርያዎች መሸጋገሪያ ወይም ማረፊያ ሆኖ ያገለግላል፤ የአዋሽ ወንዝ ደግሞ የጥም መቁረጫ እና የሣር የእፀዋቱ ልምላሜ መሰረት ነው::
በፓርኩ 35 አጥቢ እንስሳት መኖራቸው ተመዝግቧል፤ የዱር አህያ፣ ሳላ፣ የሜዳ ፍየል፣ ዝንጀሮ፣ የሜዳ አህያ፣ አቦ ሸማኔ፣ አንበሳ፣ ዥንጉርጉር ጅብ ቀበሮ ተጠቃሽ ናቸው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ዋይልደርነስ ኤክስኘሎር አፍሪካ፣ አክሽን ኢትዮጵያ ቪዚት ኢትዮጵያ ድረ ገፆችን እና ዊኪ ፒዲያን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም