ያየር ንብረት ለውጥ ዳፋ

0
81

የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የሙቀት መጨመር በዚሁ ከቀጠለ በ2100 እ.አ.አ በአማካይ 40 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ደሀ ሊያደርገው እንደሚችል ተመራማሪዎች ማስጠንቀቃቸውን ዴይሊ ሜል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

በአውስትራሊያ የኒውዌልስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባካሄዱት አዲስ ጥናት ቀደም ብሎ የተተነበየው የሁለት ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጨመር በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል:: የሙቀት መጨመሩ አሁን ባለው ሂደት ከቀጠለ አራት ዲግሪ ሴልሺየስ ሊደርስ እንደሚችልና በዚህ የሙቀት መጨመር በአማካይ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ደሃ ሊሆን እንደሚችል ነው ተመራማሪዎቹ ያስጠነቀቁት::

ምንም እንኳን አገራት አጭር እና ረጅም ጊዜ የዓየር ንብረት ግቦችን ተልመው ቢንቀሳቀሱም የዓለም ሙቀት አሁንም በሁለት ነጥብ አንድ ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚጨምር ነው ያመላከቱት:: ይህ ደግሞ የየአገራት ምጣኔ ሀብት እድገትን ይፈትናል፤ ግለሰቦችም የየድርሻቸውን ይወስዳሉ እንደ ተመራማሪዎቹ ትንተና::

የአጥኚዎቹ መሪ ዶክተር ቲሞቲ ኒል ቀደም ሲል በተካሄዱ ጥናቶች የሙቀት መጨመር በአንድ አገር ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ በዚያው አገር ምርት ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ያገናዘበ ብቻ እንደነበር ተችተዋል::

አጥኚው አዲስ ባደረጉት ጥናት የአገራት ምርት በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) የተሳሰረ ወይም የተቆራኘ መሆኑን ነው ያሰመሩበት:: በአንድ አገር ላይ የሚደርስ የከፋ የዓየር ሁኔታ በሌላኛው ላይ ተፅእኖው እንደሚንፀባረቅ መገንዘብ ግድ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል::

በአንድ ቀጣና ሙቀቱ ጨምሮ ርጥበት ተሟጦ ድርቅ ሲከሰት በሌላኛው ቀጣና ዝናብ በዝቶ በወጀብ እና ጐርፍ ውድመት ማስከተሉ እንደማይቀር ነው ያብራሩት- ተመራማሪው::

በመጨረሻም አንዳንድ በጥናቱ ውስጥ ያልተሳተፉ ተመራማሪዎች የዓየር ንብረት ለውጥ በአንድ ቀጣና በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ክርኑን ቢያሳርፍ ከሌላው ቀጣና መጥቶ ይሸፈናል ቢሉም መሪ ተመራማሪው ዶ/ር ቲሞቲ ኒል  ግን የሙቀት መጨመር ሁሉንም ቀጣና እንደሚያዳርስ እና በምጣኔ ሀብት ትስስር ሁሉንም እንደሚጐዳ ነው ያደማደሙት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here