ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
የያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ ምድረ ገነት በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን ያዩ ወረዳ ይገኛል። የጥራት ደረጃው ቀዳሚ የሆነው “አረቢካ” ቡና በተፈጥሯዊ ደን ጥላ ስር ከሚበቅል የቡና ተክል የሚሰበሰብበት በመሆኑ ወረዳውን ልዩ እና ተመራጭ አድርጐታል::
በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ከጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚለቀመው የያዩ ቡና ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እውቅና ተሰጥቶታል:: በዚህም በርካታ ሀገሮች ምርቱን ስለሚፈልጉት አምራቾቹ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል::
አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የያዩ የአረቢካ ቡና ዘረመል መጠበቂያ ደን በስድስት ወረዳዎች ተከልሎ ከሰዎች ንክኪ ተጠብቆ ዓመታትን መዘልቅ ችሏል::
ከሁሉም በላይ “Garden coffee system” እየተባለ በሚጠራው በደን እና እርሻዎች ውስጥ በሌሎች ሰብሎች መካከል በቤተሰብ ደረጃ የሚለማው ቡና ትልቅ አቅም ለመፍጠሩ ባለ ሙያዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል::
ዓለም አቀፍ የዓየር ንብረት ተነሳሽነት (IKI) የተሰኘ ድርጅት ባወጣው ህትመት ቡና የሀገሪቱን 30 በመቶ የውጪ ንግድ እንደሚሸፍን፣ የአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በአነስተኛ እርሻ ቡና አምራች ዜጐች መተዳደሪያ መሆኑን እና ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጐችም የሥራ እድል መፍጠሩን አስፍሯል::
በያዩ ተፈጥሯዊ የጫካ ቡና ክልል ቀደም ብሎ በተደረጉ ጥናቶች 50 አጥቢ 20 ተሳቢ የእንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ። ከ100 በላይ ብርቅዬ እጽዋት እና የዓእዋፍ ዝርያዎችም ተመዝግበዋል። ከነዚህ መካከል 44ቱ የመጥፋት አደጋ እንዳዣበበባቸው ተመላክቷል::
በያዩ ደን ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ደኑን ለተጨማሪ ገቢ ማስገኚያነት ስለሚመነጥሩት የያዩ የጫካ ቡና ዘላቂነቱ ላይ አደጋ አንዣቦበታል::
በወረዳው የተሰማራው (IKI) የተሰኘው ድርጅት ለሴቶች አማራጭ የገቢ ማግኛ ስልቶችን በመንደፍ፣ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመሥራት ላይ ይገኛል:: ከዚሁ ጐን ለጐን የቡና ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን በማቋቋም የዓየር ንብረቱ ለቡና ተክል ተስማሚ በመሆኑ ኗሪዎች በየማሳቸው እንዲተክሉ ጠንክሮ እየሠራ መሆኑ ነው የተገለፀው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት – ያዩ ባዮስፌር፣ ኢንተርናሽናል- ክላይሜት – ኢኒሺዬቲቭ፣ ሪሰርች ጌት ዶት ኔት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም