ይቅርታ የአዙሪታችን ማቆሚያ

0
208
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በለውጥ፣ በመሻሻል እና በዘመናዊነት መስመር ውስጥ አስደማሚ ትዕይንቶችንና ፈጠራዎችን እያበረከተ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ዕድሜ አስቆጠረች ሲባል ይህ መንገድ፤ ይህ ዕድሜ፤ የዕውቀት፤ የፖለቲካ ልምድ፤ የታሪክና ጥበብ ሀብት እርሾ ሆኗት ልትለወጥ፤ ሀብታም ልትሆን በተገባ ነበር።
አራት መቶ እና ሦስት መቶ ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ሀገራት ዓለምን በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ እየመሯት የሺህ ዓመታት ዕድሜ እንዴት አይለውጥም? እንዴት የኢትዮጵያ ዕድሜ የእንጨት ሽበት እንዲሆን ፈቀድን?
ክርስቶፈር ኮለምበስ እ.አ.አ. በ1492 አሜሪካን በአሰሳ እንዳገኛት የታሪክ ድርሳናት አስቀምጠውታል። የሀገሪቱን እድሜ ከዚያ ጀምረን ብንቆጥረው 532 ዓመታት የአሜሪካ ዕድሜ ነው።
ዛሬ አሜሪካ የዓለም መሪ፣ የሠላም ደሴት ፣ የኢኮኖሚ ማማ፣ የስልጣኔና ዘመናዊነት ተምሳሌት ሆናለች። ክብሯንና ስሟን ለማስጠበቅ የትኛውም የዓለም ዳርቻ ድረስ ዘልቃ ገብታ የአድራጊ ፈጣሪነት ሚናዋን ታሳያለች::
የትኛውም መሪ ቢለዋወጥ አሜሪካ ክብሯ እና አንደኝነቷ አይለወጥም። አሜሪካ እዚህ ለመድረስ የተጓዘችበትን መንገድ ብንመለከተው ብዙ ሕዝብ ያለቀበትን ጦርነት ከውስጥም ከውጭም አድርጋለች።
ባለፉት አምስት መቶ ዓመታት እያንዳንዱ አሜሪካዊ ሀገሩን ገናና እና ጠንካራ ለማድረግ ሲሰራ አልፏል። እነሱ አውሎ ንፋሱን አልፈው ዛሬ ፀጥታው ላይ ደርሰዋል። የእኛን እሳትና አውሎ ነፋስ ለማረጋጋት ይመለከተናል እያሉ ናቸው። ተፅኗቸው ርግጥ ቀላል አልሆነም።
ኢትዮጵያዊያ በአንፃሩ ዓለም በሌሎች ሀገራት የኢኮኖሚ የበላይነትን ለመገንባት በሚሯሯጥበት ዘመን ከጠብመንጃ አዙሪት ያልወጣች ሆናለች።
ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማሕበረሰባዊ መስተጋብሯ ዓለም ከደረሰበት እድገት ለመድረስ ካላት አቅም አንጻር ሲለካ አነሰ እላለሁ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ምንም አይደለችም፣ ቆማለች ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ኋላ ሄዳለች እያልሁ አይደለም።
በታሪክ፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና በተቋማት ተለጣፊነትና ተጠምዛዥነት አንዱ ዘመን አልፎ ሌላው ሲተካ ሽግግር ሁልጊዜ ጦርነትና ፍጅት የሚፈራረቅባት ሆናለ።ጉዟችን አንዱ የሠራውን በማፍረስ፣ ሌላው የወጠነውን በማጣጣል፣ ቀደምቱን በማራከስ ዛሬን በማወደስ የቀጠለ ነው።
ኤድዋርድ ሰይድ “አሸናፊዎች ሁል ጊዜ ታሪክን ይጽፋሉ” እንደሚለው በሀገራችን አንዱ ሌላውን ጥሎ፤ ኋለኛውን ገድሎ በመቃብሩ ላይ የሙትን ታሪክ ሥም እጽፋለሁ ይላል። ደግሞም የሆነው ይህ ነው። አሸናፊዎች ናቸው የተሸናፊዎችን ታሪክ የሚጽፉት። የጦርነትና የቀውስ አዙሪት እስከመቼ መድረሻችን ይሆናል? ኢትዮጵያዊያን ቀደምት ታሪክና የሥነ መንግስት እውቀትና ጥበብ ይዘን ሳለ በሴራ በሚበልጡን ሰዎች ተከፋፍለን፤ ለከፋፋዮቻችን ተመችተን ስንጠፋፋ ታሪካችን በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በእንግሊዝዝ፣ በአሜሪካና በሌሎችም ሀገራት ተጽፎ ተሰጠን።
ባለፉት 100 ዓመታት የኢትዮጵያ መልክና ስልት ተቀይሮ በሴራ ተልእኮ በበለጧት የጠላት አጀንዳ ተሰማርታ የጥል እና የብጥብጥ ሜዳ ሆናለች። በኢትዮጵያ በየትኛውም ክልል ቀደምት ታሪክና እውቀት ጥበብና ማስተዋል አለ።
አክሱም፣ ላሊበላ ፣ ሉሲ ድንቅነሽ ፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት ታሪክ እና ሌሎችም በመሠረቱ አንድም የሰው ልጆች ዛሬ ላይ እንዲያስትውሉበትና አኗኗራቸውን ከትናንት ጋር አስማምተው እንዲቀጥሉና ሁለትም ቀደምቱን ስህተት እንዳይደግሙ፣ በመልካሙ ታሪክ እርሾ ጨምረውበት እንዲያሳድጉት፤ ሀገር ወይም ትውልድ እንዲሻሻል ማገዝ ነው።
የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ ጉዞ ግን በዘመን ከፍ የማይል እንዲያውም አድሮ መከራ የሚታጨድበት ማሳ ሆኖ በመስፋፋት መቀጠሉ ነው። “ ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንዲል የተዘራ ተንኮል፣ ሴራ፣ መገፋፋት፣ መፎካከር፣ መከዳዳትና ራስን ማስቀደም በትውልዱ ልቦና ውስጥ በመዘራቱ አሁን ሞት፣ስደትና መከራን እያጨድን እንገኛለን።
ግጭት ምድር ላይ ያለፍጥረት ሁሉ የሚያስተናግደው እውነት ነው። የአንዱ ማደግ በሌላው መሸነፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አልዘነጋሁትም። ይህች ምድር የአሸናፊዎች መኖሪያ ናት። አንዱ የአንበሳ ጎሳ ነኝ ባይ ከሌላው ጋር በመግጠም በጉልበት አሸንፎ ይኖራል።
የአንድ ሰው ጎሳ የተጋጣሚውን ፍላጎት አክብሮ በመጠንና ጉልበት ልክ ይኖራል። የሮናልድ ሬጌንን ሐሳብ ላስከትለው: “ሠላም የግጭት አልባነት ህይወት አይደለም፤ ይልቁንስ ግጭቱን በሠላማዊ መንገድ የመፍታት ስልት ነው” ይላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ሀገራት በስፋት የተለወጡበትን ዘመን፣ ፖለቲካዊ አስተዳደራቸውን በጸና ስርዓት ላይ በገነቡበት ጊዜ፤ አንዱ ባንዱ ሲሳለቅ፤ ነፍጥ ተሸኝቶ ነፍጥ ሲተካ በድህነታችን ቀጠልንበት። ከትናንት ትምህርት ወስደን ኑሯችንን አልቀየርንም። ከትናንት ተምረን ነፍጣችንን በጠረጴዛ አልተካንም።
ከላሊበላ ጥበብ ተውሰን የችግሮቻችንን መፍቻ ጥበብ አላገኘንም። ከላሊበላ ጥበብ የላቀ ሥራ ሲጠበቅብን ያለውን መጠበቅና ማቆየት አልቻልንም፣የገጠመንን ጉዳት መጠገን አልሆነልንም። ማብቂያ በሌለው የጦርነት አዙሪት የምንመላለስ፤ ዓለሙ በግርምትና በንቀት የሚያየን ውሃ ውስጥ ሆነን የምንጠማ፤ እህል ጎተራ ላይ ሆነን የምንራብ ግሩም ሕዝብ ለመሆን በቅተናል።
ባለፈው እንስቃለን፤ ባለፈው ከብዙው ነጥለን በአንዱ እንኩራራለን። ዛሬ ምን ሠራችሁ ብሎ ለሚጠይቀን፤ የትውልድ አሻራ የሌለን እንደመጣልን የምንመለስ፤ አልፎ ደግሞ ቀደምቱ ያበረከቱትን በስህተት ፈርጀን በቡድንና በብሔር ሽፋን ውስጥ የምናሴር ህዝቦች እየሆን ነው። በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) “እውን አባትህ አንተን ወለደ” ሲል የሚተቸው እኛንና የቀደመውን ዘመን ነው።
በአክሱም የምንመጻደቅ በላሊበላ የምንጣላ፤ አንዱ ለእኔ ሌላው ለእኛ በሚል አባቶች እና እናቶች በሰሩት ጥበብ ለክፍፍልና ሽሚያ የተጣላን የትውልድ አባላት ነን። አባቶች ቀደምት ብለው የነደፉትን የሀገራት ጉዞ እኛ ልጆች አሰልጥነን ዘመኑ ከደረሰበት ውድድርና እውነት ጋር አጣጥመን መቀጠል ነበረብን።
ካልሆነም በአያቶቻችን ታሪክ እየተኩራራን ያለንን እየበላን መቀጠል ባልከፋ ነበር። ግን እንዴት አባቶች የሠሩትን ታሪክ፤ ጥበብና እውቀት በማጥፋትና በመቀራመት ላይ እንጠመዳለን። ጦርና መሣሪያን አንድ ቦታ ማቆም አልቻልንም ። ከዚህ በኋላ በቃን ብለን እንጀምራለን በወራት እና ዓመታት ውስጥ ወደ በደልና ጦርነት አቅጣጫ እንዞራለን። እንደ ብዙው ኢትዮጵያዊ በኢህ አዴግ ስርአት የከፋም ባይሆን ትንሽ ተበድያለሁ። ከእስራትና የሰቆቃ ህይወት፤ ከከፋፋይና ዘረኛ አስተዳደር ለመላቀቅ በነበረኝ ጉጉት የለውጡን መንግስት በተስፋና ጥርጣሬ ተቀብየው ነበር።
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 24 ደግሞ ባህር ዳር በተደረጉ ሰልፎች ድጋፌንም አድርጌያለሁ ። ከመጋቢት እስከ ሰኔ 16 ድረስ የነበረኝን ለውጡን በጥርጣሬ የመመልከት አቋም ቀየርኩ። በተለይ እስከ ሰኔ ድረስ የተደርጉ ተግባራት በለውጡ የነበረኝን የተስፋ አቋም እንድገፋበት ረዱኝ። ከጠብመንጃ አዙሪት ለመውጣት ይቅርታ የሚል ሐሳብ በመኖሩ ከዚህ ቀደም የደረሱ በደሎችን በይቅርታ መሻገር የሚልን ሐሳብና ድርጊት በማየቴ ለውጡ የጦርነት አዙሪትን ያስቆማል የሚል ሐሳቤን አጠናከረው። ጃንሆይን በደርግ፣ ደርግን በኢህአዴግ፣ ኢህአዴግ ደግሞ በህዝብ፣ አሁን ደግሞ ብልፅግና በታጠቁ ኃይሎች ዘመቻ ተጀምሮበታል። በነፍጥ ቅብብል ልንወጣ አልቻልንም፣ ሐሳባችን ወደ ጠረይዛ አልመጣም። ሸፍቶ ጫካ ውስጥ እና በግራ መደበላለቅ ውስጥ ነው።ለውጡን የደገፍሁት ይህንን የጦርነት አዙሪት በይቅርታ ይፈታል፣ ሀገሬ በማፍረስ እንደገና መገንባትን ታቆማለች በሚል ነበር። የጦር መሣሪያ አዙሪት፤ የቂምና ጥላቻ ትርክት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሽጋገር በሽታ ነው። የይቅርታ ምዕራፍ በደላችንን ሽሮ፣ ጠብመንጃችንን ታሪክ አድርጎ በአዲስ የሐሳብ ጠረጴዛ ዙሪያ ሊያሰባስበን በተገባ ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የዛሬ ህፃናትና ወጣቶች አዕምሮ ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዲገባ አድርገነዋል። የዛሬ ህፃናት ከ20 ዓመታት በኋላ መሪዎች ይሆናሉ። አባቴን ያኛው ወገን ገድሎብኛል ፣እህቴን ይህኛው ወገን ደፍሮብኛል ብሎ ቂም አርግዞ ያድጋል። ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ ጫካ መግባትን፣ ጦር መሣሪያ መምዘዝን አማራጭ ያደርጋል። የጦርነት አማራጭን አንድ ምዕራፍ ላይ የሚያስቆም ማነው? አይሰለችም ግን አዙሪቱ? የዚህ ሁሉ ቀውስና የኋልዮሽ ጉዞ ምክንያቱ በአስተሳሰብ አለመቀየር፣ ባሉበት መቸከልና ከድጡ ወደ ማጡ መጓዝ ነው። ብላድሚር ጋልቫን ውጤትህ ሐሳብህ ነው ይላል። ጦርነት እያሰብን፤ ግጭት ስንፈጥር እያደርን፤ የበለጡንን እየገደልን፣ የሚቃወሙንን እያሰርን፣ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን እያሳደድን የተረጋጋ አገር ሊኖረን አይችልም። አዙሪታችን ጥይት ሆኖ ይቀጥላል። ሐሳባችን ይታያል፣ ለስሜት ይቀርባል፣ ለድርጊት ይጋብዛል። ውጤትም አለው። ሐሳባቻችንን ብንደብቀው ፊታችን እና ድርጊታችን ላይ ይስተዋላል፤ በውጤቱም ይለካል። ዓለም በሐሳብ ልቆ ፣በቴክኖሎጂ ተራቆ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን ሲፈለፍል በሚያድርበት ዘመን እኛ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ በጠላቶቻችን ስጋት፤ ከውስጥ እርስ በእርሳችን እሳት እያነደድን እንገኛለን። የሐሳብ ለውጥ ነው የጦርነትን አዙሪት የሚያቆምልን። የይቅርታ ልብ ነው፣ አዙሪታችንን የሚሰብርልን። የሐሳብ ለውጥ እናድርግ። ካለፈው መልካም ነገር ትምህርት ወስደን የዕይታ ለውጥ እናምጣ።
ግድባችን እና የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ግዙፍ ጥላ ስር የሚያሰባስቡን አጀንዳዎቻችን ናቸው። የጋራ ታሪኮቻችንን ላይ ብናተኩር የውይይትና የምክክር አግባብን ብናስቀድም ከጦርነት አዙሪት የማንወጣበት ምን አስማት አለና? ሌሎች ያደጉ ሀገራት የተለወጡት የፈጠሩትን ችግር ለመፍታት የዕይታ ለውጥ በማድረግ ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here