ደረሰኝ ምንድን ነው?

0
462

በዚህ ሳምንት የፍትሕ አምድ የምናስነብባችሁ ስለ ደረሰኝ ምንነት እና ከደረሰኝ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የፍትሕ ተጠያቂነቶች ዙሪያ ነው:: በጉዳዩ መረጃ የሚሰጡን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የክልል ዐቃቤ ሕግ  አቶ ስንታየሁ ቸኮል ናቸው::

አቶ ስንታየሁ እንደሚገልፁት በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 13/2012 አንቀጽ ሁለት ላይ በተሰጠው ትርጉም መሰረት ደረሰኝ ማለት እቃ ወይም አገልግሎት ለሚገዙ ሰዎች ሻጭ የሚሰጠው የግብይት ማረጋገጫ ሰነድ ነው:: ይህም የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝን፣ (ተጨማሪ እሴት የተርን ኦቨር) እንዲሁም ኩፖን እና ትኬትን ይጨምራል::

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ግብይት በደረሰኝ እንደሚከናወን ይታመናል፤ ከታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀፅ 13  እና የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር በመመሪያ ቁጥር 13/2012 አንቀጽ 9 እንደተገለጸው ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ናቸው::

የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀፅ 79 እንዲሁም የሒሳብ መዝገብ እና ሰነድ አያያዝ ሥርዓትን ለመወሰን ከወጣው መመሪያ ቁጥር 14/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር አንድ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለባቸው የሚባሉት  የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች  ናቸው፤ በተጨማሪም በፈቃደኛነት የሒሳብ መዝገብ የሚይዙ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች እና የካፒታል ሀብት በማስተላለፍ ጥቅም የሚያገኙ  ናቸው ይላል::

ከዚህ እንደምንረዳው ታዲያ በመጀመሪያ የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለባቸው   የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች  ናቸው። በፈቃደኛነት የሒሳብ መዝገብ የሚይዙ ደግሞ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መሆናቸውን የአብክመ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 240/2008 አንቀጽ 10፣ 13 እና 18 ላይ የሰፈሩት ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

በአቶ ስንታየሁ ማብራሪያ መሰረት በአዋጁ አንቀጽ 10 የተጠቀሱ ግብር ከፋዮች ከቅጥር ገቢ ግብር የሚከፍሉ፣ በአዋጁ አንቀፅ 13 የተጠቀሱት ግብር ከፋዮች ከቤት ኪራይ ገቢ ግብር የሚከፍሉ እና በአዋጁ አንቀጽ 18 የተጠቀሱት ግብር ከፋዮች ደግሞ ከንግድ ሥራ ገቢ ግብር የሚከፍሉ ናቸው::

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዋጁን መተላለፍም  ቅጣትን ያስከትላል፤ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች (በፈቃደኛነት የሒሳብ መዝገብ የሚይዙ) እንዲሁም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች እንዲሁም የካፒታል ሀብት በማስተላለፍ ጥቅም የሚያገኙ ግብር ከፋዮች ያለ ደረሰኝ ግብይት ቢያከናውኑ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀጽ 119 ንኡስ ቁጥር አንድ መሰረት ከብር ሃያ አምስት ሺህ ብር እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጫ እና ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚቀጡ ተደንግጓል::

እያንዳንዱ ግብይት ራሱን በቻለ እና በተለየ ደረሰኝ መመዝግበ አለበት የሚሉት የሕግ ባለሙያው ይሁን እጂ ይህን አሠራር በሚቃረን መልኩ  ለአንድ  ግብይት ጥቅም ላይ በዋለ የደረሰኝ ኮፒ ላይ የተለያዩ ግብይቶችን የመጠቀም ተግባር እየተለመደ መምጣቱን አብራተዋል:: ስለሆነም ይህን ድርጊት ለመከላከል ለአንድ ግብይት በተሰጡ ወይም ጥቅም ላይ በዋሉ ተመሳሳይ የደረሰኝ ኮፒዎች ላይ የተለያዩ ግብይቶችን በመመዝገብ የሽያጭ ዋጋን ማሳነስ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ድርጊት ሆኖ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀጽ 119 ንዑስ ቁጥር ሁለት ሥር ተደንግጎ ይገኛል::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ድርጊቱን በሚፈጽሙ ግብር ከፋዮች ላይ የሚጣለው ቅጣት በደረሰኙ ላይ የተመዘገበውን ትክክለኛ የግብይት ዋጋን መሰረት አድርጎ የሚወሰን ነው::

በደረሰኙ ላይ የተመዘገበው ትክክለኛው የግብይት ዋጋ ብር አንድ መቶ ሺህ ብር  እና ከዚያ በታች ከሆነ ቅጣቱ በብር አንድ መቶ ሺህ የገንዘብ መቀጫ እና ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል፤ አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀጽ 119 ንዑስ ቁጥር ሁለት  በደረሰኙ ላይ የተመዘገበው ትክክለኛው የግብይት ዋጋ ብር አንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ በደረሰኙ ላይ የተመዘገበው ከፍተኛው የገንዘብ መጠን በገንዘብ መቀጫነት እና ከ7 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል:: 119 ንዑስ ቁጥር  ሦስት ደግሞ ግለሰቦች በወንጀል ድርጊት ማትረፍ የለባቸውም የሚል ሃሳብ የያዘ ነው::

አቶ ስንታየሁ እንደሚሉት ማንኛውም ሰው ግብይት ሳይፈጽም ደረሰኝ መቀበል አይችልም:: ግብይት ሳይፈጽም በጓደኝነት ወይም ለመጠቃቀም ደረሰኝ የሰጠ ወይም የተቀበለ ሰው በአጠቃላይ የድርጊቱ ፈፃሚዎች የወንጀል ተጠያቂነት ያለባቸው ሲሆን ቅጣቱ ለሁለቱም ተመሳሳይ ሆኖ ሁለት ደረጃ አለው::

የመጀመሪያው ቅጣት ደረሰኙ ሁለት ሺህ ብር እና በታች የያዘ ከሆነ ከብር  አንድ መቶ ሺህ ብር እስከ ብር ሁለት መቶ ሺህ ብር  ሊደርስ በሚችል የገንዘብ መቀጫና ከ7 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጡ ይደነግጋል፤ ሁለተኛው ቅጣት ደረሰኙ ከ200 ሺህ ብር በላይ ከሆነ በደረሰኙ ከሰፈረው ገንዘብ ጋር እኩል የሆነ የገንዘብ መቀጫ እና ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል::

በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቅጽ 19 ንዑስ ቁጥር አንድ እና የታክስ ደረስኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 13/2012 አንቀጽ 24 እንደገለጸው ደረሰኝ የማሳተም ግዴት ያለበት ግብር ከፋይ ባለስልጣን መስሪያቤቱን ሳያስፈቅድ ደረሰኝ ማሳተም አይችልም ::

ከባለስልጣኑ ዕውቅና ውጭ ደረሰኝ ያሳተመ ግብር ከፋይ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 አንቀጽ 119 ንዑስ ቁጥር ስድስት መሰረት  ከሦስት መቶ ሺህ ብር አምስት መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል ::

ይህ ድንጋጌ የማተሚያ ድርጅቶችንም እንደሚመለከለት የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ያለ ዕውቅና ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ወንጀል ደረሰኝ ማሳተም የፈፀመ ከሆነ ህትመት የሠራው የማተሚያ ድርጅቱ የህትመት መሳሪያው  ይወረሳል፣ የንግድ ፈቃዱም ይሰረዛል ብለዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here