ደስታም ስጋትም

0
97

ከወር በፊት አልጋ ላይ ቀስቅሳኝ የት እንደምትቀበር߹ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደምትቀበር߹ የሚዲያውን ሁኔታ߹ የሚያለቅሱትን ሰዎች߹ የሕዝቡን ብዛት ስትነግረኝ እንደቀልድ አልፌው ነበር፡፡ ግን ያለችው ነገር ነው የሆነው” ሲል ድምጻዊ አቤል ሙሉጌታ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ  ስለ ሚስቱ አሟሟት እና ሕልሟ ተናግሮ ነበር፡፡ የአቤል ሚስት ተዋናይት ሰላማዊት አስማማው ድንገት ታመመች፤ ብዙም አልቆየችም፤ አረፈች፡፡ ቀብሯ በመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሕዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡

በተደጋጋሚ የማያቸው ሕልሞች አሉኝ፡፡ በተለይ ውሻ በድግግሞሽ ሲያሯሩጠኝ ነው የሚያድረው፡፡ ይህ ሕልም ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ የማየው ነው፡፡ የታቦት ስለት አለብህ የሚሉኝ ብዙ ናቸው፡፡ ሰይጣን እየተፈታተነህ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሰው ስደባደብ በተደጋጋሚ አድራለሁ፡፡

እናቴ “ሕልሜ መሬት ጠብ አትልም” ነው የምትለኝ፡፡ አያቴም እንዲሁ “እንዲያው በሕልሜ መጥፎ ሕልም ቀጠቀጠኝ” ካለች መጥፎውን ነገር እንጠብቃለን፡፡ ስጋት ገብቶን እንፈራለን፡፡ አያቴ ሞቷንም በሕልሟ አይታ ለእናቴ አጫውታት ነው ያረፈቸው፡፡

የእናቴ ሕልም አውነት መሆን እና ተደጋግሞ መከሰት ስለሚያስፈራኝ ሕልሟን መስማት ጭንቀት ይለቅብኛል፡፡ እናም እኔ በሕልም አላምንም፤ አትንገሩኝ እላለሁ፡፡ ብቻ ሕልም እፈራለሁ።

ሕልም እልም߹ ሕልም እንደፈቺው ነው߹ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እና ሌሎች መሰል አባባሎች በማሕበረሰባችን ውስጥ በስፋት ይነገራሉ፡፡ በሕልም ብዙ ሰው ያምናል፡፡

የባህል ጥናት (ፎክሎር) በውስጡ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ልማድ ነው፡፡ ሕልም ደግሞ ከሐገረሰባዊ ልማዶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሕልምን በሚመለከት  ብዙ ጥናቶች አልተደረጉም፡፡ ቢደረጉም እንኳን ለአንባቢያን ተደራሽ አይደሉም፡፡

ለዛሬ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩሊቲ ፎክሎር (ባህል ጥናት) ትምህርት ክፍል “የሕልም እሳቤ፣ ፍቺ እና ፋይዳ በእናርጅ እናውጋ ወረዳ” በሚል ርእስ በስለናት የላይነህ በሰኔ 2011 ዓ.ም የቀረበውን ጥናት እንቃኛለን፤ ሕልም እና ተያያዥ ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡

ይህ ጥናት ህዝባዊ ሁነት፣ ሀገረሰባዊ ጨዋታ፣ ሀይማኖት፣ ሀገረሰባዊ እምነት፣ ሀገረሰባዊ መድሀኒት እና የጊዜ ሰሌዳዊ ልማድ በሚል  ሀገረሰባዊ ልማድን በስድስት ከፍሎት እናገኘዋለን፡፡

ስለናት በጥናቷ “ሕልም ሰዎች በሚተኙበት ሰዓት (ወቅት) የሚተገብሩት የሀገረሰባዊ እምነት አንዱ ክፍል ነው፡፡ በምንተኛበት ሰአት አዕምሯችን የሚፈጥራቸው ምስሎች እና ሃሳቦች ውሕድ ነው” ትላለች፡፡ “የሚያዝናኑ፣ የሚረብሹ፣ ቀልዶች፣ የፍቅር ግንኙነቶች፣ የሚያስፈራሩ እና አንዳንድ ጊዜም ያልተለመዱ ክስተቶችን ይይዛል” በማለት ትርጉም ሰጥታዋለች፡፡ “ሕልም በእንቅልፍ ልብ የሚታይ ረቂቅ ራዕይ ነው” በማለትም ገልጻዋለች፡፡

ሕልም ከሀይማኖት፣ ከልማድ፣ ከባህል፣ ከስነ-ልቦና ባለሙያዎች፣ ከሀኪሞች፣ ከስነ-ባህሪ ተመራማሪዎች ዕይታዎች አንጻር በርካታ ትርጉሞች አሉት፡፡

ሕልም ከባሕሪው አንጻር አስደሳች፣ አስጨናቂ፣ አመራማሪ፣ ቶሎ የሚረሳ እና ለብዙ ዓመታት ከአላሚው ጋር አብሮ የሚኖር ሊሆን ይችላል፡፡ ከመጥፎ ነገር ማስጠንቀቂያ፤ ወደፊት የሚመጣውን የሚተነብይ፤ በልቦና ውስጥ ያለውን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያመለክትም ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡

የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ማህበራዊ ደረጃ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ስራ፣ ተግባር፣ እንቅስቃሴ፣ ምኞት እና  አጠቃላይ ግለሰቡን ያኖሩትን መገለጫዎች መሰረት ያደረገ ጉዳይ ነው፡፡ ሕልም እንዲፈጠር߹ እንዲታለም ያደረገው የግለሰቡ አጠቃላይ የሕይዎት መገለጫዎች ናቸው ትላለች፤ ስለናት በጥናቷ፡፡

ሕልም ፍቺው ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል፡፡ከሰው እምነት እና አመለካከት አንጻርም ልዩነት አለው፡፡ ሕልሙን በሚፈቱት ሰዎች ማንነትም ይወሰናል፤ የሕልም ትርጉም፡፡ ሕልም በመጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርአንም በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ በሕልም አማካኝነት ፈጣሪ በሰው ልጆች ማድረግ የሚፈልገውን አድርጓል፤ በሕልማቸው ተገልጾም አናግሯቸዋል፡፡

ጥናት አድራጊዋ ስለናት የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ነዋሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጋለች፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ አቶ ልንገረው ያለው የተባሉ ግለሰብ ሕልምን እንዲህ ሲሉ ተርጉመውታል፡፡

“ሕልም በእንቅልፍ ልብ በአብዛኛው ሰው የሚታይ ነው፡፡ ግን ስለሰው፣ ስለአዝመራው እና ስለሀገሩ ሕልም አልሞ የደረሰለት የሚባል ሰው በእግዛሄር የተመረጠ ሰው ነው፡፡ በእግዛሄር የተመረጠ ሰው ክፉንም ደጉንም ስለሚያሳየው ያልመዋል፡፡ እናም እግዛሄር እኛን ለመገሰጽ በእነዚህ ሰዎች አድሮ ይናገራል፡፡ ሕልም በውነቱ ስንኸድ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ሲነጋ የሚደርስብሽ መጥፍ ነገር ታለ አሳይቶሽ እንድትጠነቀቂ ያደርግሻል፤ ወደፊት የምታይው ደስታ ታለም ያሳይሻል፡፡ ግን ያለምሽውን ማሰብ እና ማስታወስ ተቻልሽ ነው” (ቃለ-መጠይቅ፣ የካቲት 2011 ዓ.ም)

በጥናቱ መሰረት እንጀራ በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ ዘወትር  የሚበላ ምግብ ነው፡፡ እንጀራ በሕልም ውስጥ በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ አንጻር  በአብዛኛው ጥሩ ትርጉም አለው፡፡    በመሆኑም በማህበረሰቡ እንጀራ ለራስ መብላት፣ መሸከም እና መጋገር መልካምነት ያላቸው ሲሆን እንጀራ በሌላ ሰው መቀማት፣ ሌላ ሰው ማብላት፣ እንጀራ እየጋገሩ ማረር፣ እንደያዙት መውደቅ እና ሌሎች መጥፎ ከሚባለት የሚመደቡ ናቸው፡ የአቶ ተስፋየ ደጉን ሕልም እንመልከተው፡፡

“በሕልሜ ተኝቸ ይመስለኛል፡፡ እንጀራ እየተጨመረኝ ስበላ ስበላ ከዚያ አባቴ ይመስለኛል አብረን እንብላ ብሎ መጥቶ አብረን እንበላለን፡፡ ከዚያ ጥቁር ሰውየ መጥቶ አብራችሁ አትበሉም ብሎ በቦንብ ሊመታን ሲል ባለቤቴ መጥታ ከኋላችን ሲያያት አንች ነሽ እንዲህ የምታደርጊ ብሎ በቦንብ ሲመታት ጣጥቸ ተነሳሁ፡፡ ከዚያ ያንን ሕልም እንዳየሁ ከሁለት ሳምንት በኋላ አባቴ ትንሽ ወረት ሰጥቶኝ ተማሪ እያለሁ ማውረትረት (የመነጋገድ) ስራ እሰራ ነበር፤ የንግድ ወረትም ሰፍቶልኛል፤ ብርም ይዣለሁ፡፡ ከዚያ  ጠበንጃ ስገዛ አባቴም ሊገዛ ብር ጎድሎት 25ሺ ብር ስሰጠው ከባለቤቴ ጋር ተጣልተን መርዝ ጠጥታ ሞተች፡፡ (አቶ ተስፋዬ ደጉ፡- ቃለ-መጠይቅ መጋቢት 2011 ዓ.ም)

ገንፎ በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ  ከስንዴ፤ ገብስ፤ በቆሎ እና ከመሳሰሉት እህሎች የሚዘጋጅ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ልጅ ሲወለድ እና ሰርግ ሲሰረግ የሚዘጋጅ ምግብ ነው፡፡ የሚዘጋጀውም ካልቦካ እህል በማህበረሰቡ አባባል (ከአዲስ እህል) ነው፡፡ ገንፎ በሕልም ውስጥ በዚህ ማህበረሰብ አስተሳሰብ እና አመለካከት የተለያየ ትርጉም አለው፤ የጥሩ ነገር ተምሳሌት  ሆኖ እናገኘዋለን፤ ምሳሌውን እንመልከተው፡፡ ርዕሰ ደብር መሪ ጌታ አባተ ንጋቴ እንደሚከተለው በሕልም የገንፎን ሕልማዊ ፍቺ ያሳያሉ።

“የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ ይመስለኛል በሕልሜ በቤታችን ውስጥ በሰፊው ገንፎ ተገንፍቶ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ እየበላ አየሁ፡፡ ተዚያ ያን ሕልም ባየሁ በሁለተኛው ወር በልጅነቱ ጠፍቶ የኖረው ልጃችን ሞተ እየተባለ ሳናስበው መጥቶ ደስታ በደስታ አድርጎን ያለምኩት ሕልም በአይነ ሌቦናየ እያየሁት መሆኑን ማመን እስቲሳነኝ ድረስ አሳምኖኛል፡፡”

ማር በጣም ጣፋጭ ሲሆን በመጠጥ መልክና በምግብ የምንጠቀመው ነው፡፡ ማር በመጠኑ ካልበላነው ጥሩ አይደለም፡፡ ከጣፋጭነቱ ብዛት የተነሳ የብዙ በሽታ መድኃኒት ቢሆንም በበሽታዎች ለመያዝም መንስኤ ነው፡፡ ማር ከከባድነቱ ባሻገር ሲበሉት ሆድን የሚነፋ ስለሆነ ጥቂት መጠቀም እንዳለብን ይመከራል፡፡ ማር በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ በሕልም ሲበሉ እና ሲሸከም ሲታይ ከባድ ነገር እንደሚገጥም ይታመናል፡፡ ስለማር በሕልም ውስጥ ያለውን ተግባር ወ/ሮ ሁልዬ እንዳላማው እንደሚከተለው ገልጻለች፡፡

“በሕልሜ ይመስለኛል የሚያምር ማር በሳህን አድርጌ እኔው ደፋ ደፋ እያልኩ አምሮት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ደብቄ እየጨመርኩ ጥርግ አድርጌ እስቲበቃኝ ድረስ በላሁ፡፡ ተዚያ በሶስተኛው ቀን ኪዲነ-ምህረትን አከብር ነበር። ተዚያ እረስቸው ውኃ ስቀዳ ተሸክሜ ወደ ቤት ስኸድ ያናቀፈኝን ሳላውቀው ወድቄ ገደል ተንከባልየ ግራ እጄን እንስራው ወድቆብኝ በወጌሻ ብታሽም ስላልተስተካከለ እስከ አሁን ድረስ ስራ አልሰራም፡፡ እጄም የተጧነዘ ሆነ፡፡ ህመሙም ብዙ ወራት አማቆኛል፡፡ ግን አልተስተካከለም፡፡ አሁንም እንደልቤ አልንቀሳቀስም ጤናየ ይሰማኛል፡፡

በተጠቀሰው ሃሳብ መሰረት ማር በሕልም ሲታይ እንደ ሁኔታው በአላሚው ወይም በሌላ ሰው ላይ ከባድ ነገር እንደሚመጣ ነው፡፡ ማር በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ ሁለት አይነት ሕልም ውስጥ ትርጉም እና ፍቺ አለው፡፡ ማር በሕልም መብላት፣ መሸከም፣ መቀባት እና  የመሳሰሉ ድርጊቶች በሕይወት ላይ ከባድ ነገር ሊመጣ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሕልም የተሸከሙትን ማር ማውረድ፣ ሳይበሉ መተው፣ ለሌላ ሰው መስጠት፣ ማቀበል ሊደርስብን ከነበረው ከባድ ነገር (አደጋ) ማምለጥ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ይቀጥላል…

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here