ከላፈው የቀጠለ
ውድ አንባቢያን ባለፈው ሳምንት በክፍል አንድ ንባባችን ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩሊቲ ፎክሎር (ባህል ጥናት) ትምህርት ክፍል “የሕልም እሳቤ፣ ፍቺ እና ፋይዳ በእናርጅ እናውጋ ወረዳ” በሚል ርእስ በስለናት የላይነህ በሰኔ 2011 ዓ.ም የቀረበውን ጥናት መነሻ በማድረግ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡
የመጨረሻው ክፍል ደግሞ አቀጥሎ ይቀርባል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
መቀነት እንደ ኩታ ሁሉ በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ ያገባች ሴት ብቻ በወገቧ የምትታጠቀው የልብስ ዓይነት ነው፡፡ መቀነት ቁመቱ ረጅም እና ወርደ ጠባብ ሆኖ እንደኩታ በአራት ማዕዘን የሚሰራ ሲሆን ጫፉ እና ጫፉ ላይ የተለያየ ቀለም ባላቸው ክሮች በመጠቀም የሚሰራ ነው፡፡ ስለሆነም በሕልም ውስጥ እራሱን የቻለ ትርጉም እና ፍቺ ያለው ነው፡፡ እንደ አላሚው የሕልም ሁኔታ ይወሰናል፡፡ መቀነት በሕልም ውስጥ አዎንታዊ እና አሉታዊ ፍቺዎች ያሉት በመሆኑ ነው፡፡ አወንታዊን ስንመለከት ከምንም በላይ ጥሩ ጎኑ ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ መቀነት መታጠቅ ሴትነትን (ሙያን) የሚገልጽ ሲሆን ማግባትን ምልክት እና የሴትን ጠንካራነት የሚገልጹበት ነው፡፡ በሕልም ውስጥ መቀነት ታጥቆ ማየት ጥሩ እንደሆነ ሁሉ የታጠቁትን መቀነት መፍታት ደግሞ መጥፎ ነው። ሴትነትን (የሙያ መጥፋትን) ማጣት እና ከባል ጋር መፋታትን ያመለክታል በማለት መረጃ አቀባዮች ለጥናት አድራጊዋ ተናግረዋል፡፡ መቀነት በሕልም ሲታይ ያለውን ፍቺ እንደሚመለከተው ይገልጻሉ፡፡
“በሕልሜ ስለሴት ልጆቼ እና ስለ የልጅ ልጆቼ ሲያልመኝ ሊያገቡ ሲሆን ሁል ጊዜ በሕልሜ መቀነት ሲታጠቁ አያለሁ፡፡ ሌላ ደግሞ ሊፈቱ ሲሉ መቀነታቸው ሲፈታ እና ሲጠፋቸው አያለሁ፡፡ እሱም ይደርሳል” በማለት አቶ አስራቴ ቢተው ተናግረዋል፡፡
ሱሪ በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ ከአልባሳት አንዱ ሲሆን ወንዶች ከወገባቸው በታች የሚታጠቁት ልብስ ነው፡፡ ሱሪ የጀግንነት መግለጫ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ወንድ ልጅ ሲወለድ “ሱሪ ያለው፣ ጀግና” ሆኖ እንዲያድግ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ነዋሪም የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ የተወለደው ልጅ ምን ሆኖ ማደግ እንዳለበት ገና ከተወለደ ጀምሮ ትግበራው ይካሄዳል፡፡ ሲያድግም ወንድ ልጅ ምን መሆን እንዳለበት ይመከራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ከዱር አውሬ አድኖ ከገደለ፣ ጠላት ካሸነፈ (ድል ካደረገ) “እገሌ እማ ሱሬ የታጠቀ ወንድ ነው” ይባላል፡፡ ስለዚህም ለሱሪ የሚሰጠው ክብር ከፍ ያለ ነው፡፡
ሱሪ በማህበረሰቡ አስተሳሰብ እና አመለካከት ሰርጾ የገባ ጠንካራ አቋምን የሚገልጽ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ሱሪ በሕልም ውስጥ መታጠቅ እና መውለቅ ራሱን የቻለ ትርጉም እና ፍቺ አለው፡፡ ይህን ሀሳብ በተመለከተ አቶ አለባቸው ከበበው ሕልሙን እና የሕልሙን ውጤት እንደሚከተለው ተናግሯል።
በሕልሜ ይመስለኛል ጓዴ የሚባል ሰውየ የታጠኩትን አዱስ ሱሪ አውልቆ ለሌላ ሰው ሲያስታጥቀው ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ ብየ ስለው ለአንተ አይገባህም ለአንተ የሚሆን ብሎ ትንሽ “የፋንት” መሳይ አስታጥቆኝ ኸደ፤ እኔም ነቃሁ፡፡ ተዚያም ሀሙስ ቀን ያለመኝ እሁድ ስብሰባ ተደርጎ ከወረዳ የመጡ ሰዎች ሊቀመንበር ነበርኩ በዚሁ ሀሳብ ሹመቴን አውርደው የቀበሌ የጎጥ ፈጅ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ ለልማት የጎጥ ቀስቃሽ ሆንኩኝ፡፡
ሱሪ በሕልም ውስጥ ሚስት ማግባት ጋር፣ ሰርቶ ባለጸጋ ከመሆን ጋር፣ ከሰው ጋር ገጥሞ ማሽነፍን፣ ሌሊት ከቀን የሚሰራን ለፊ ሰው፣ መምራት እና ማስተዳደር የሚችልን፣ ተናግሮ በንግግሩ ማሳመን የሚችል እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚወክል መሆኑን ያመለክታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሱሪ በሕልም መቃጠል፣ መውለቅ እና መጥፋት ከላይ ከተገለጹት ሀሳቦች በተቃራኒ የሚቆም ሀሳብ እንዳላቸው መረጃ ሰጭዎች ይገልጻሉ፡፡ ሌላኛው ሱሪን በተመለከተ ቄሰ ገበዝ ደረሰ ገላኤ ያለሙትን እና የደረሰላቸውን ሕልም እንደሚከተለው እንመልከት፡፡
“ተኝቼ በሕልሜ አዲስ ሱሪ የለበስኩ ይመስለኛል፡፡ ተዚያ ጎንበስ ብዬ ያየውት እንደሆን የአንደኛው እግሬ ሱሪ ልብስ አልቋል፡፡ ተዚያ በውኔ እንደምጨነቀው እየተገረምኩ ሳለሁ ብንን አልኩ፡፡ ሕልሙን እንዳለምኩት ብዙ ሳይሰነብት ሚስቴ ሞተች፡፡”
ሱሪ በተጠናው ማህበረሰብ ወንድን ልጅ የሚመለከት ሲሆን በሕልምም ይህ አስተሳሰብ እንደሚንጸባረቅ ያሳየናል፡፡ ይኸውም ወንድ ልጅ በሕልም ሱሪው ሲቃጠል፣ ሲያልቅ፣ ሲቆሽሽ፣ ሲቀደድ፣ ሲለብሰው ልኩ አልሆን ሲል (አላምርለት ሲል)፣ ሌላ ሰው ሲወስድበት ሲታይ የህልሙ ፍቺ እና አደራረሱ መጥፎ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከተጠቀሱት በተቃራኒ በሕልም ውስጥ ሲታይ ደግሞ የሕልሙ ፍቺ እና አደራረሱ በማህበረሰቡ በጥሩ ይታመናል፡፡
ጓንዴ፣ ረዥም ሚኒሽር፤ ክላሽ እና አጭር ሚኒሽር የጦር መሳርያዎች በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ በሕልም ውስጥ የራሳቸው ትርጉምና ፍቺ አላቸው፡፡ እነዚህ መሳርያዎች በሕልም ውስጥ በማህበረሰቡ በተደጋጋሚ የሚታዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ጓንዴ እና ረዥም ሚኒሽር ሲያዝ ወንድ ልጅ መውለድ (ማስረገዝ) ተብሎ ይፈታል፡፡ ክላሽ እና አጭር ሚኒሽር መያዝ ሲሆን ሴት ልጅ መያዝ ወይም ማርገዝ፤ ማስረገዝ ነው፡፡ መረጃ አቀባዮች እንደገለጡት ጓንዴ እና ረዥም ሚኒሽር ከክብደታቸው አንፃር፣ ከሚይዘው የሰው አይነት ሴት ወይም ወንድ ፆታ አንፃር የወንድ ልጅ ፀባይ፣ እርጋታ፣ ሲናገር አስደንጋጭነቱን በማገናኘት ወንድን ልጅ መያዝ ወይም መወከል እንደሚችል በማመን ነው፡፡ ክላሽ እና አጭር ሚኒሽር ሴት ልጅ መያዝ ትችላለች፡፡ ሴት ልጅ ከፍጥነቷ አንፃር፣ ነገሮችን ከተለያየ ከመመልከት አንፃር ሴት ቀዳሚውን ቦታ የምትይዝ እንደሆነ መረጃ አቀባዮች ይገልፃሉ፡፡
ካራ ወይም ቢላዋ በተጠናው ማህበረሰብ ከብረት የሚሰራ ስለታማ ነገር ሲሆን ለሽንኩርት መክተፊያነት፣ ለስጋ መቆራረጫነት የሚውል መሳርያ ነው፡፡ ካራ በተጠናው ማህበረሰብ የወንድ ልጅ መሳርያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ካራ ይቆርጣል እንጂ አይቆረጥም በሚለው አስተሳሰብ ወንድ ልጅም በዚሁ አስተሳሰብ ውስጥ ይገባል (ይሳላል)፡፡ ካራ አሸናፊ ስለሆነ በሕልም ውስጥ ሲታይ የወንድ ልጅ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሕልም ካራ መያዝ ወንድ ልጅ ማርገዝ ሲሆን በሕልም ካራ መጥፋት የወንዴ ልጅ ሞት ነው፡፡ ካራ ወንድ ልጅ የሚጠቀምበት (የሚገለገልበት) ቁሳቁስ በመሆኑ ስለካራ ጉዳይ ወይም ካራን የሚመለከት ሕልም ሲታለም ፍቺውም ሆነ አደራረሱ ትኩረት የሚያደርገው ወንድ ልጅ ላይ ነው፡፡ መረጃ አቀባዮች እንዳለት ካራ በጥሩም ሆነ በመጥፍ በሕልም ውስጥ ይታያል፡፡ ዞሮ ዞሮ ደጉም ሆነ ክፉው ሕልም ሲደርስ ወንድ ልጅ ላይ ያርፋል በማለት ይገልፃሉ፡፡ ስለካራ የሚከተለውን ሕልም እንመልከት፡፡ በሕልሜ ባሌ ይመስለኛል ካራውን እንቺ አስቀምጭው ብሎ ሊሰጠኝ ሲል እዛው ያዘው እስቲ ስለው አንቺ ያዥው ባንቺ ያምራል እኔማ እንዴት ብየ ይለኛል፡፡ ካራ መያዝ ከብዶህ ነው ብየ እቀበለዋለሁ፡፡ ተዚያ ተቀብየ ትንሽ እንደያዝኩት ይጠፋብኛል፡፡ ተዚያ ስፈልገው አጣዋለሁ ተስፋ ስቆርጥ ተውኩት፡፡ እንደዚያ እንዳለመኝ አጋጣሚ እርጉዝ ነበርኩ፡፡ እዳሪ ወጥ ስሰራ ምች መቶኝ ወንድ ሌጄ ጠፋብኝ፡፡ (ወ/ሮ ታንጉት የወግነህ፡ ቃለ መጠይቅ፣ መጋቢት 2011 ዓ.ም)
በተጠኚው ማህበረሰብ ውስጥ ስሞችም መልካም እና መጥፎ ውክልና አላቸው። መልካም የሚባሉ ስሞች አሉ። ተመስገን፣ ሙሉቀን፣ ዘውዲቱ፣ ብዙነህ፣ በላይነህ፣ ጌታቸው፣ ሰናይት፣ ጸጋ፣ ሸጋሰው፣ ደስታ፣ ሐረግነሽ፣ ቢያግድልኝ እና ሌሎችም ስሞች መልካም ነገሮችን ወክለው በሕልም ውስጥ ይታያሉ።
በአንጻሩ በሕልም ውስጥ መጥፎ የሚባሉ ስሞችም አሉ። እምቢ አለ፣ ሽብሩ፣ ከበደ፣ ጫኔ፣ ጓዴ፣ ያሳብ፣ አሸብር፣ ትዕዛዙ፣ እራቤ፣ በአንች አይሞሉ፣ እና ሌሎችም ስሞች በሕልም ሲመጡ መጥፎ ትርጉም አላቸው።
በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ሕልምን ማንም አይፈታም። የተመረጡ ሰዎችም አሉ። በእድሜ ገፋ ያሉ ታላላቆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በሕይወት ዘመናቸው የተፈተኑ ሰዎች፣ የሕይወት ውጣ ውረድ አይተው ያለፉ ሰዎች፣ የኑሮን የተለያዬ አቅጣጫ የመረመሩ፣ አግኝተው ያጡ፣ ኀዘን እና ደስታ የተፈራረቀባቸው ሰዎች፣ በሃይማኖታቸው የበቁ ሰዎች ሕልሞችን ይፈታሉ።
በስለናት ተላይነህ ጥናት መሰረት ሕልም የሚያልመውን ሰው ማንነት ለማወቅ ያግዛል። ኢ-ንቁው (ድብቁ) የአዕምሮ ክፍል ውስጥ የተደበቁ አዎንታዊ እና አሉታዊ ፍላጎቶችና ስሜቶች መግለጫ ነው። በዚህም መጪው ዘመን ምን እንደሚመስል ለሰው ልጆች የሚተነብይ ሕልም ነው። የሰዎችን የወደፊት እጣ ፋንታም ይነግራል። ከልዩ ልዩ ጉዳዮች የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲጠብቁም ያግዛል።
ሕልም እንደፈቺው ነው እንደሚባለው በእናርጅ እናውጋ ማህበረሰብ ውስጥ ሕልም ፋይዳው እና ፍቺው ምን ይመስላል የሚለውን በዚህ መልኩ የቀረበውን ጥናት መሰረት አድርገን ተመልክተነዋል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሕልም ሌላ ፋይዳ፣ ትርጉም እና ፍቺ ሊኖረው ይችላል።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም