ደስታ በቀጠሮ

0
181

ጀምስ አለን ሰው እና ሐሳቡ በሚለው መጽሐፉ “ሰው ደስታንም ኅዘንንም ይሰራል።የሚፈጥራቸውን ደስታና ኀዘን ቀጣይነትም የሚያረጋግጠው ራሱ ነው። ደስታ እና ኀዘን ከውጪ የሚመጡ ሳይሆን ከውስጥ የሚፈጠሩ ናቸው” በማለት ደስተኝነት ከውስጥ እንጂ ከውጪ ዓለም ሊመጣ እንደማይችል ይገልጻል። ደስታ የተግባር ውጤት ነው፤ ውጤት ደግሞ የሚታዩ የሐሳቦች ድምር ነው ይላል።

“ለደስታ እና ለማይናወጥ ጥልቅ ሰላም  መንስኤ የሆነውን እውነተኛውን ሀብታቸውን ያላወቁት እነሱ ለማኞች ናቸው። የበዛ ቁሳዊ ሀብት ቢኖራቸው እንኳን ደስታን ማግኘት ወይም ርካታን ለማጣጣም  ይሁንታን፤ ዋስትናን ወይም ፍቅርን ለማግኘት ውጪውን ይመለከታሉ። እነዚህ ሰዎች ውስጣቸው ብዙ ሀብት ተትረፍርፏል። ዓለም መስጠት የምትችለው ሀብት ሁሉ በእጃቸው አላቸው”  በማለት ኤኻርት ቶሌ ዘፖወር ኦፍ ናው በሚለው መጽሐፉ  አስፍሯል። በተመሳሳይ እንደ ጀምስ አለን ሁሉ ኤኻርት ቶሌም ደስታ በውጫዊ ሁኔታዎች የተወሰነ እንደሁ  የማይጨበጥ ስለመሆኑ ያስረዳል።

ኤኻርት አንድ መሰረታዊ ነገርን በመጽሐፉ አስፍሮ እንመለከታለን። ይህም የሰው ልጅ ከጊዜ ጋር ያለው መስተጋብር ነው። ጊዜውን ትናንት፣ አሁን እና ነገ በሚል ያስቀምጠው እና የሕይወት ጉዞ ሁሉ ዋና ማጠንጠኛው አሁን በሚለው የጊዜ ምዕራፍ ላይ መሆን አለበት ይላል። የትናንት ጊዜ ምዕራፍ ጸጸት የሚበዛበት፤ የነገ የጊዜ ምዕራፍ ደግሞ ይሆናል የሚል ቅዠት የሚያንዣብብበት እንዲሁም የአሁን ጊዜ ምዕራፍ ደግሞ የሰው ልጅ ከራሱ እውነተኛ ደስታ እና ምሉዕነት ጋር የሚገናኝበት ስለመሆኑ ጽፏል።

“የሰው ልጅ ትናንት የሆነውን በማሰብ ነገ ደግሞ ምን ይገጥመኝ ይሆን የሚል ፍርሀት ውስጥ ከገባ ፤አሁን ማሰብ እና ማድረግ የሚችልበትን አቅም ያጣል ሲል”  የ አውት  ኦፍ ዩር ኮምፎርት ዞን መጸሐፍ ደራሲ  ዶክተር ኤማ ማርድሊን ጽፏል።

አርማን ኤክስ ዋይ ዜድ ድረገጽ ላይ የሰው ልጆች የደስታ ስነ ልቦና ምን ይመስላል በሚል የተደረገ ጥናት ቀርቧል። ጥናቱ ስለ ደስተኝነት የተሞላነው መረጃ ትክክል አይደለም በማለት ይቀጥላል። ሁሉም የሰው ልጅ ደስታን ያሳድዳታል። ያገኛታልም፤ ግን ይዟት ማስቀጠል አይችልም። ለብዙዎች ደስታ ቅጽበታዊ ትመስላለች። ደስታ ስሜት ናት፤ ስሜት ደግሞ በቅጽበት ይቀያየራል። ያለማቋረጥ የሰው ልጅ ስሜት በለውጥ ውስጥ ያልፋል። ስሜታችንን መለወጥ እንችላለን። ችግሩ ያለው ያንን ስሜት ይዘን ማቆየት አለመቻላችን ላይ ነው። እንደ እሳት ለመጨበጥ ያስቸግራል። ወደ ጥናቱ ውጤት ስንመጣ ሦስት ሰዎችን እናገኛለን ዮናታን፣ራሔል እና ሪቻርዶ ይባላሉ።

ዮናታን በሄደበት፣ ሕይወት በመራቸው እግሩ ባደረሰው የሚኖር ሰው ነው። አርቆ ማሰብ እና ለነገ የሚሉ ጉዳዮች አይመቹትም። በእቅድ፣ በቀጠሮ መኖር አይወድም። ድንገት የፈለገውን፣ የሚወደውን ነገር ማድረግን ይመርጣል። ዮናታን አሁንን መኖርን የሚመርጥ ደስተኛ ሰው ነው። “በቃ ፈታ እላለሁ” እንደሚሉት ሰዎች። አሁን (ዛሬ የምንለውን ጊዜ) ይኖራል። ጸጸት የለበትም። ለነገ ብዙ የመስራት ትልቅ ሕልም ፣ትልቅ ራዕይ አለኝ ብሎ አይጓጓም። የለውምም። በሕይወቱ የሚገጥሙትን ነገሮች ሁሉ ተቀባይ ነው።አሁንን በመኖር ጠንክሮ ይሰራል።

ራሔል ሕልመኛ ናት። ለነገ በቀጠሮ የታቀዱ የሕይወት ግቦች አሏት። በስራ የምትባዝን ታታሪ ሴት ናት። አሁን ደስታ የሚባል ስሜትን አታስበውም። ነገ ሕልሜን አሳክቼ ከማንም በላይ ደስተኛ እሆናለሁ ብላ ታምናለች። ሁልጊዜ በመዋከብ እና ትርምስ ውስጥ ትሮጣለች፤ በጊዜ እጥረት ምክንያት አንዱን አንስታ ሌላውን ስትጥል ትስተዋላለች። አንድ ቀን በሚል ሕልሟን ለማሳካት ስለምትሮጥ ዛሬን አታውቀውም። ለነገ ስኬት በሚል ሁሉንም አጋጣሚዎችን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት ለጭንቀት ዳርጓታል።

ወደ ሪቻርዶ እንምጣ፤ ተሰላችቷል። ዓለም ፊቷን አዙራብኛለች ብሎ ራሱን በቁስለኛ እሳቤ የሚመለከት ሰው ነው። ደስተኛ አይደለም። ለደስታ እንጥፍጣፊ ተስፋ እንኳን የለውም። በሕይወት ተስፋ ያጣ፤ አንዳች እንኳን መልካም ነገር የማያስተውል ሰው ነው።በሕይወቱ ተስፋም ደስታም አያስተውልም። በሦስቱም ሰዎች ውስጥ የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን ተመለከትን። ዮናታን ደስተኛ እና በአሁን የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ የሚኖር ሰው ነው።ራሔል አልፎ አልፎ ደስተኛ እና በነገ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ናት።ሪቻርዶ በነገም ይሁን በአሁን ውስጥ የሌለ ተስፋ መቁረጥ የሚያሳድደው ሰው ነው። በትናንት ውስጥ ነው፡፡ ጉድለቱ፣ ማጣቱ፣ ችግር እና መከፋቱ ሕይወቱን እንዲቆጣጠር ፈቅዷል ወይም እጅ ሰጥቷል፡፡

የስነ ልቦና ባለሙያው  ዶክተር ሎራ ፓርክ ባደረጉት ምርምር የሰው ልጅ ሁለት የደስታ አረዳዶች አሉት። የዘገዬ ደስታ እና አሁንን መኖር ሲሉ ይከፍሏቸዋል። የመጀመሪያው (ዲሌይድ ሀፒነስ) ትላልቅ የሕይወት ዓላማቸውን ካሳኩ በኋላ እደሰታለሁ ብለው በነገ ቀጠሮ ደስታን የሚጠብቁበት ነው የዘገዬ ደስታ። ሁለተኛው ደግሞ እያንዳንዷን ቅጽበት በደስታ ኖሮ ማለፍ ነው። ሁለቱም ዕይታዎች የራሳቸው ጉዳት እና ጥቅም ቢኖራቸውም እንኳን ዓላማዬን አሳክቼ እደስታልሁ የሚለው የመጀመሪያው ግን ዛሬን በመንጠቅ ነገ ላይ እንዳንደርስ ሊያደርገን የሚችል ስለመሆኑ ዶክተር ሎራ ይናገራሉ።

ዜኒያ ኮሊ ሚዲየም ድረገጽ ላይ ባሰፈረችው ሐተታ ደስታን ለነገ ቀጠሮ በመስጠት ብዙዎች እንደተጎዱ ጽፋለች። “ተመርቄ ሥራ ስይዝ እደሰታለሁ፤ ሀብታም ስሆን ፤ ቆንጆ ሚስት ሳገባ፤ ልጆች ስወልድ፤ አገሬ ስመለስ፤ ሕልሜን ሳሳካ፤ ቤት ስስራ፤ ልጆቼን ስድር፤ ክብደት ስቀንስ ደስተኛ እሆናለሁ” በሚል ሰዎች ደስታቸውን አንድም ያዘገዩታል፤ሁለትም ዛሬ መስራት የሚገባቸውን ሳይሰሩ በጭንቀት ያልፋሉ ስትል ጽፋለች። ደስታ አንድን ጉዳይ ካሳካን በኋላ ሳይሆን ሁልጊዜም አብሮን መኖር ያለበት ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ የሰው ልጆች ሕይወትን የሚረዱበት መንገድም ጭምር  ነው። በዚህም ደስታ የዕለት ሁኔታን በመረዳት እና ምሉዕነትን በመምረጥ የሚገኝ ሐሴት ነው ትላለች።

“ዘከሬጅ ቱ ቢ ዲስላይክድ” በሚል መጽሐፋቸው ኢችሮ ኪሽሚ እና ፉሚቴክ ኮጋ ደስታ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ቢሆንም በአኗኗር ግን ኀዘን ምርጫ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች በዝተው ተስተውለዋል ይላሉ። ደስታ ምርጫ እንጂ እዳ አይደለም የሚለው ዋና ሐሳባቸው ነው።ለሌሎች ሰዎች ውለታ ሊመልሱበት በማይችሉበት ሁኔታ  አስተዋጽኦ ማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ደስታን የሚሰጥ ምርጫ ስለመሆኑ በመጽሐፉ ሰፍሯል።ብዙ  ሰዎች ደስታን መዳረሻ አድርገው ያስቡታል። አሜሪካ ብሄድ እደሰታለሁ እንደሚል ዲቪ ሎተሪ እስኪወጣለት የሚጠብቅ ኢትዮጵያዊ ወጣት፤ እውነታው ግን አሜሪካ ከሄደ በኋላ ደግሞ በሕይወቱ ጭንቀት ውስጥ የሚያስገቡት ችግሮች ሲገጥሙት እንደገና ኀዘን ውስጥ ይገባል። የልጆቼን የትምህርት ቤት ክፍያ የምሸፍንበት አሪፍ ስራ ባገኝ ደስተኛ እሆናለሁ ይላል። ይህ የተሳካለት ቀን ጀምሮ  ሌላ ጎደሎ ነገር ይፈልጋል። ደግሞ በእሱ ይጨነቃል። ኅዘን፣ ምኞት፣ ስኬት፣ ደስታ፣ ኀዘን እየተፈራረቁ በድግግሞሽ በሕይወቱ ይመጣሉ። ደስታንም ሆነ ኀዘንን በልኩ ተርጉሞ አዎንታዊ መልስ መስጠት ላይ ነው ቁልፉ ያለው። ካልተሳካልኝ አልደሰትም የሚለው ሐሳብ  ብዙዎችን በርካታ ጥማት ውስጥ ያስቀጠለ ነው። ደስታ መንገዱ ነው የመጨረሻው ግብ አይደለም የሚባለውም ለዚህ ነው። ወደ ግብህ ስትጓዝ ደስተኛ ካልሆንህ፤ ግብህ ላይ ለመድረስ ትቸገራለህ። ተሰላችተህ ብትደርስም ስኬትን አታጣጥመውም ነው ሐሳቡ።

ለረጅም ዓመታት ባለጸጋዎች  ደስተኞች እንደሆኑ ሲነገር  ኖሯል። እውነቱ ግን ይህን አያሳይም። እንዲያውም ሀብት እና ዝና በመጣ መጠን የበለጠ ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ጭንቀትን ይወልዳል። “ማይዝስ ኦፍ ሀፒነስ”  በሚለው መጽሐፏ ሶንጃ ሊቦምሪስኪ የሰው ልጅ እደሰትባቸዋለሁ በሚል ለዓመታት ያመነባቸውን ስሑት አፈታሪኮች አስቀምጣለች። ይህንን ሳሳካው እደሰታለሁ ለሚለው መልስ ካላችሁ፤ በአንጻሩ የማልደሰተው ምን ስሆን ነው ለሚለውም ምላሽ ስጡበትም ትላለች ሶንጃ።

በዚህም “ነገሮች መልካምም ይሁኑ መጥፎ እኛ  የምንሰጣቸው ትርጉም ለደስታ እና ለኀዘን ስሜቶቻችን ወሳኝ ነው” ስትል ታብራራለች። ደስታችን አንዳች የሆነ ነገር ከማግኘት፣ ከመቀበል፣ ከማሳካት እና እውን ሆኖ ከማየት ጋር የተያያዘ ሆኖ ለዓመታት ቢታሰብም እንኳን ነገሩ እንዳለፈ በቅጽበት ውስጥ ጨፍጋጋ ማንነታችን ውስጥ እንድንሆን ያደርገናል ትላለች ሶንጃ። “ባል ማግባት ለእኔ ከየትኛውም ጊዜ የበለጠ ውስጣዊ  ደስታ የፈጠረልኝ ነገር ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ደስታ ከሁለት ዓመታት በላይ አብሮ አልዘለቀም ነበር” የምትለው ሶንጃ ደስታችንን ዘላቂ ለማድረግ መከወን የሚጠበቁብኝ ተግባራት ነበሩ፤ ደስታን ከመጠበቅ ባለፈ እንዴት ልፈጥረው እችላለሁ የሚልውን ዘንግቸው ነበር” ስትል ጽፋለች።

“ሳይኮሎጂ ቱ ዴይ” ድረገጽ ሰዎች ደስተኛች ማይሆኑባቸውን ምክንያቶች ሲዘረዝር ራስን ከሰዎች አኗኗር ጋር ማነጻጸር ቀድሞ ይጠቀሳል። ይህ ልምምድ የራስን ሀብት እና ስጦታ ከመቁጠር ይልቅ የሰዎችን በማየት ኪስ እና ጎተራን ባዶ የሚያደርግ አደገኛ የደስታ ጸር ነው። ሁለተኛው ጥፋትን በሌሎች ማሳበብ ነው። እነዚህ ሰዎች ከደሙ ንጹህ ናቸው፤ ሕይወታቸው ደስታ ያጣው የትዳር አጋራቸው፣ቤተሰብ፣ ፈጣሪ፣ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው ጥሩ ስላልሆነ ነው ብለው ያስባሉ። ሁሉም ነገር ከውጪ በመጣ ጫና እንደተፈጠረ ያምናሉ። እነሱ ከመማረር በቀር መቀየር የሚችሉት ጉዳይ የላቸውም።

አፍሪካን ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ “ትናንት ስለሆነው እና ነገ ስለሚሆነው አብዝቶ በማሰብ ዛሬን አለመኖር ደስታን የሚያሳጣው ዋናው አደገኛ ልምምድ ነው” ይላል። “ሳር በልታ ወደ ጨጓራዋ የምትልክ ላም፤አሁንም እንደገና መልሳ ልታመነዥከው ወደ አፏ መልሳ እንደምታመጣ ሁሉ የሰው ልጅ የአሁንን ጊዜ ካልኖረ እንደዚያ ነው” በማለት አፍሪካን ቢዝነስ ኢንሳይደር “ማስታወክ እንደገና መልሶ ማኘክን ይመስላል” ብሏል።  ቀጥሎም ራስን በተጠቂነት ስሜት “ለምን እኔ ላይ ብቻ ፈተና በዛብኝ፤ እድሌ ነው፤ የእኔ ይለያል” በሚሉ ሐሳቦች መመልከት ደስታን ያሳጣል ብሏል። ስሜታችሁ የሚቆጣጠራችሁ ከሆነ አሁንም ደስታ የላችሁም። “የሰው ልጆች አዕምሯቸው እነሱ እንዲያስቡበት፤ እንዲመሩት የተሰጣቸው እቃ ነው” የሚለው ቢዝነስ ኢንሳይደር ይሁን እንጂ አዕምሯቸው ሰዎችን ሲጠቀምባቸው፤ ስሜታቸው አሸንፎ እነሱ የስሜት ባሪያ ሲሆኑ ደስታ ይርቃቸዋል ይላል። አዕምሮ የሚረዳቸውን አሉታዊ ስሜቶች መቀየር ካልቻለ የሰው ልጅ ራሱን፤ አዕምሮው በሚረዳው የውጪ ስሜት እንዲመራው ፈቅዷልና ደስታ የለውም በሚል የዛሬውን ጽሑፍ ቋጨሁ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here