በዓለማችን ላይ ብቸኛዋ ሦስት ርዕሰ መዲናዎች ያሏት አፍሪካዊት ሀገር ናት::ሀገሪቱ 11 ይፋዊ የሥራ ቋንቋዎች አሏት::በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራ እና ያደገ ኢኮኖሚ ካላቸው ውስጥ በቀዳሚነት ከሚነሱት ውስጥ ናት::በተፈጥሮ ሀብትም እጀግ የታደለች ናት::በዚህም ቢዝነስ ኢንሳይደር ባወጣው መረጃ እ.አ.አ 2025 ከሞሮኮ፣ ግብጽ እና ቱኒዚያ ቀጥሎ በአፍሪካ አራተኛዋ የጎብኝዎች መዳረሻ ሲል አስቀምጧታል፡- ደቡብ አፍሪካ፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ አህጉር ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኝ፣ በተለያዩ ስነ-ምህዳሮች የምትታወቅ ሀገር ናት። አፍሪካ ሲባልም አብዛኟው የዓለም ሕዝብ ደቡብ አፍሪካን ነው የሚያስበው ተብሎ ይነገርላታል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአጠቃላይ የሚነገሩ ቋንቋዎች ብዛት 35 ነው::ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሥራ ቋንቋዋ የመሆን እድሉን አግኘተዋል::ደቡብ አፍሪካ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር ትሰፋለች:: የሕዝብ ቁጥሯም 65 ሚሊዮን ይጠጋል::አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷም 420 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው::የነብስ ወከፍ ገቢዋም 6670 ዶላር ነው፡፡
ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ አርኪኦሎጂያዊ እና የሰው-ቅሪተ አካል መገኛ ቦታዎች አንዷ ናት። አርኪኦሎጂስቶች በጋውቴንግ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ተከታታይ ዋሻዎች ሰፊ ቅሪተ አካላትን አግኝተዋል። ይህም ደቡብ አፍሪካ ጥንታዊው ሰው ይኖርባቸው ከነበሩት ስፍራዎች ውስጥ አንዷ ያደርጋታል::ኮሂሳን የሚለው ስም ጥንታዊ የሀገሬው ተወላጆችን ያመለክታል::በተለይም ሳን እና ክሆክሆን የተሰኙት ጎሳዎች ኮሂሳን ናቸው። ሳን በአብዛኛው አዳኝ እና ሰብሳቢዎች ሲሆኑ ክሆክሆክን ደግሞ አርብቶ አደርነትን ይለማመዱ ነበር። የኮሂሳን ህዝቦች ከ150,000 ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ የተበተኑ የሰው ልጅ ቀደምት ዘሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ከ1,500 እስከ 2,000 ዓመታት በፊት በባንቱ ሕዝቦች መስፋፋት በአብዛኛው የተፈናቀሉ ወይም የተዋጡ ነበሩ።
ደቡብ አፍሪካ በአጠቃላይ ሞቃታማ የአየር ጠባይ አላት፤ ምክንያቱም በሦስት ጎን በአትላንቲክ እና በህንድ ውቅያኖሶች የተከበበች በመሆኗ፣ በአየር ጠባዩ መለስተኛ በሆነው ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ስለምትገኝ እና አማካኝ ከፍታዋ ወደ ሰሜን (ወደ ወገብ አካባቢ) እና ወደ ሌላ መሀል ላይ ቀጥ ብሎ ስለሚወጣ ነው። ይህ የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የውቅያኖስ ተጽእኖ እጅግ በጣም ብዙ የአየር ንብረት ዞኖችን እንዲኖሩ አድርጓል::የአየር ንብረት ቀጠናዎቿ ከደቡባዊ ናሚብያ ጽንፍ በረሃ በሰሜን ምዕራብ ራቅ ወዳለው እስከ ሞዛምቢክ እና ህንድ ውቅያኖስ ድንበር ጋር በምስራቅ ወደሚገኝ ለምለሙ የአየር ንብረት ያዋስናል።
ሀገሪቱ ከዓለም አስራ ሰባት ሜጋዳይቨርሲቲ (የተለያዩ ብዝሃ ሕይወት ካለባቸው) ሀገራት በስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በደቡብ አፍሪካ ያለው ኢኮቱሪዝም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተስፋፋ መጥቷል፤ ይህም የብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅ እና ለማሻሻል የሚያስችል ዘዴ ነው። ቡሽቬልድ በተሰኘው ጫካማ እና ቁጥቶዋጦዋማ ቦታ ውስጥ አንበሶች፣ የአፍሪካ ነብሮች፣ የደቡብ አፍሪካ አቦሸማኔዎች፣ ደቡባዊ ነጭ አውራሪስ፣ ሰማያዊ የዱር አራዊት፣ ኩዱስ አጋዘን፣ ኢምፓላ አንቲሎፕ፣ ጅቦች፣ ጉማሬዎች እና የደቡብ አፍሪካ ቀጭኔዎች እና ሌሎች በርካታ አጥቢ እንስሳት ይገኛሉ።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ስትሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እስከ ግንቦት 2025 ድረስ የሀገሪቱን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ሦስት ነጥብ ሦሰት ከመቶ ይይዛል ሲል የደቡብ አፍሪካ ስታትስቲክስ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል። በ2024 ደቡብ አፍሪካ በጎብኝዎች ቁጥር እድገት አሳይታለች፤ በተለያዩ የመግቢያ ወደቦቿ በኩል የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር ወደ 8 ነጥብ 92 ሚሊዮን አድጓል። በ2025 ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ለቱሪዝም ምቹ ከሆኑ ሀገራት አራተኛዋ እንዲሁም ከአፍሪካ እና በህንድ ውቅያኖስ ክልል ውስጥ ካሉ ሀገራት አንደኛዋ ሲል ዘ ቴሌግራፍ ደረጃ ሰጥቷታል::
በዓለም የጉዞ እና የቱሪዝም ምክር ቤት (WTTC) መሠረት፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በ2012 ለደቡብ አፍሪካ 102 ቢሊዮን ራንድ አስገኝቶላታል::የሀገሪቱን የሥራ እድል ስምሪት 10 ነጥብ ሦስት በመቶ ይደግፋል።
ደቡብ አፍሪካ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የተለያዩ አማራጮችን ታቀርባለች፤ ከእነዚህም መካከል ውብ የተፈጥሮ መልክዓ ምድርና የእንስሳት ክምችት፣ የተለያዩ የባህል ቅርሶችና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የወይን መጠጦች ይገኙበታል። በጣም ተወዳጅ ከሆኑት መዳረሻዎች መካከል በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ሰፊው የክሩገር ብሔራዊ ፓርክ፣ የክዋዙሉ-ናታል እና የዌስተርን ኬፕ ግዛቶች የባህር ዳርቻዎችና እንዲሁም ውቦቹ በአውሮፓዊያን ስነ ሕንጻ ጥበቦች እንዲሁም በዘመናዊ ስነ ሕንጻ ያሸበረቁት የኬፕ ታውን፣ ደርባን እና ጆሃንስበርግ ዋና ከተሞች ይገኙበታል። በ2017 እ.አ.አ ደቡብ አፍሪካን በብዛት የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና የፈረንሳይ ዜጎች ናቸው።
የሮቢን ደሴት በዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥፍራ ነው::ምክንያቱም የቀድሞው የነጻነት ታጋይ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት የታሰሩበት ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ነው፡፡
ደቡብ አፍሪካ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በማዕድን፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር በቴሌኮም በሚዲያ፣ በቱሪዝም እና በመሠረተ ልማት በተለይ ከሳህራ በታች ያሉ ሀገራትን ልቃ ሄዳለች::ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎቿ ደግሞ ከአፍሪካ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ተቆናጠዋል። እነዚህ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ፣ ስቴሌንቦሽ ዩኒቨርሲቲ እና ዊትዋተርስራንድ ዩኒኒቨርሲቲ የተሰኙት ተቋማት በትምህርት ጥራት አፍሪካ ውስጥ ማንም ደርሶባቸው አያውቅም፡፡
ሀገሪቱ በአህጉሪቱ ትልቁ የመንገድ አውታር አላት- በአጠቃላይ 750,000 ኪ.ሜ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ 10ኛው ትልቁን መንገድ ያየዘች ያደርጋታል። ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ትልቁ እና በጣም የዳበረ የባቡር መስመር አላት፤ ይህም በዓለም ላይ ዘጠነኛው ትልቁ የባቡር መስመር ያላት ሀገር ያደርጋታል፤ በ2025 እ.አ.አ አጠቃላይ የሀዲዷ ርዝመት 36,000 ኪ.ሜ ነው።
ደቡብ አፍሪካ በኢትየጵያ የምትታወቀው የበርካታ ወገኖቻችን መኖሪያ በመሆኗ ነው::በተለያዩ ጊዜያት ወገኖቻችን በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸውን ሲያጡ እንሰማለን፤ ደቡብ አፍሪካዊያን የውጭ ሀገራት ዜጎች ጥላቻ እንዳለባቸውም ይነገራል::እስከነ የተለያዩ ችግሮቿም ቢሆን ብዙዎች ሀብት እና ንብረት እንዲያፈሩ፣ ወገኖቻቸውን እንዲረዱ የሀገራቸውን ኢኮኖሚም እንዲያግዙ ምክንያት ሆናለች፡፡
አጫር እዉነታ
ደቡብ አፍሪካ
- በዓለማችን ላይ ብቸኛዋ ሦስት ርዕሰ መዲናዎች ያሏት አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡
- ሀገሪቱ 11 ይፋዊ የሥራ ቋንቋዎች አሏት፡፡
- በአፍሪካ አራተኛዋ የጎብኝዎች መዳረሻ ናት፡፡
- ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ አህጉር ደቡባዊ ጫፍ ትገኛለች፡፡
- በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአጠቃላይ የሚነገሩ ቋንቋዎች ብዛት 35 ነው፡፡
- ደቡብ አፍሪካ በአጠቃላይ ሞቃታማ የአየር ጠባይ አላት፡፡
- የሕዝብ ቁጥሯ 65 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡
- ደቡብ አፍሪካ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር ትሰፋለች፡፡
- አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ 420 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡
- የነብስ ወከፍ ገቢዋ 6670 ዶላር ነው፡፡::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


