ከስድስት መቶ ዓመታት በፊት አጼ ዘርዓያዕቆብ እንደቆረቆሯት ታሪክ ያስረዳል፤ ከተማዋ ቀድሞ የነበራት መጠሪያም ደብረ ኤባ ነበር – ደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር:: የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ደብረ ብርሐን የዛሬ መጠሪያዋን ያገኘችው አፄ ዘርዓያዕቆብ በሰጡት ትክክለኛ ፍርድ የተነሳ ከሰማይ ብርሐን በመውረዱ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ::
ከተማዋ ስትቆረቆርም ሆነ ከዚያ በኋላ የነበሩ የተለያዩ ነገሥታት በከተማዋ እና በዙሪያዋ ቀላል የማይባሉ ታሪኮችን አሳርፈው አልፈዋል:: ይህም ለአስተዳደራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መነቃቃት የነበረው አበርክቶ የጎላ ነው::
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ስምምነት የፈፀሙበት የልቼ ጥንታዊ ቤተመንግሥት፣ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤተ መንግሥትን ጨምሮ የከተማዋ መስራች አፄ ዘርዓያዕቆብ የከተሙባት መሆኗ ደብረብርሐን በዙሪያዋ እና በውስጧ ምን ያህል የፖለቲካ ማዕከል እንደነበረች አስረጂ ይሆናሉ።
ታሪካዊ እና የዕድሜ ባለፀጋዋ ደብረ ብርሐን ከተማ መነቃቃት የጀመረችው ከኢትዮጵያ 2000 ዓ.ም ሚሊኒየም ወዲህ እንደሆነ ነባር የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሱት ሀቅ ነው:: በዚህም አንዳንዶች “ከእንቅልፏ የነቃችው ከተማĺ” እያሉ ሲሳለቁባት መስማት የቅርብ ትዝታ ነው::
የከተማዋ ቀዝቃዛ አየር ንብረት ለነዋሪዎች ጤንነት እና ለሌሎች ከተሞች ያላት ማዕከላዊነት ደግሞ ለሥራ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል:: ከተማዋ የሰሜን ሸዋ ዞን ማዕከል በመሆን ከማገልገሏ በተጨማሪ በ1986 ዓ/ም ወደ ከተማ አስተዳደርነት አድጋለች:: በዚያን ጊዜ የነበራት የሕዝብ ቁጥርም 26 ሺህ 935 እንደሆነ ከከተማ አስተዳደሩ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በተለያዩ የሥራ ተቋማት ለሚሰማሩ አልሚዎች በሚሰጡት ቀልጣፋ አገልግሎት ወደ ከተማዋ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማስቻሉን የገለፁት በከተማ አስተዳደሩ የመሬት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እታለማሁ ይምታቱ ናቸው:: ይህን ተከትሎም ከተማዋ በ2014 ዓ.ም ወደ ሪጂዮ ፖሊታን አድጋለች::
ፈጣን የኢንቨስትመንት ፍሰት ማዕከል እየሆነች የመጣችው ደብረብርሐን ከተማ አሁን ላይ 621 ኢንዱስትሪዎች በተለያየ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ:: ከእነዚህ ውስጥ 98ቱ ወደ ምርት ገብተዋል:: ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞም ከ11 ሺ በላይ ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንደሆኑ ከመምሪያው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል::
አሁን ላይ በዘርፉ በተደረገ ጥናት ከ2 ሽህ 50 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለባለሃብቶች ርክክብ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን መምሪያ ኃላፊዋ ጠቁመዋል::
የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለእንጨት እና ብረታ ብረት፣ ለጨርቃጨርቅ፣ ለቆዳ እና አልባሳት፣ ለኬሚካል እና ኮንስትራክሽን እንዲሁም ለምግብ እና መድኀኒት በሚል የቦታ ንድፍ መሠራቱንም አክለው ተናግረዋል::
በ2016 ዓ.ም ብቻ ከተማ አስተዳደሩ 24 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ለማስገባት አቅዶ እስካሁን 17ቱ መግባታቸውን መምሪያ ኃላፊዋ አረጋግጠዋል::
በቅርቡ ከተማ አስተዳደሩ አራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውን ተከትሎ ምረቃ ባካሄደበት ወቅት ሌሎች 18 ፋብሪካዎችም ማሽን የማስገባት ሥራ ስለማከናወናቸው ተገልጿል:: በከተማዋ ወደ ሥራ የገቡትም ሆኑ በተለያየ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች ከአካባቢያዊ ምርት እስከ ውጭ ምንዛሬ ድረስ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተጠቁሟል::
ታዲያ የእነዚህ ሁሉ ድርጅት መረጃዎች ግን የተያዘው በወረቀት ነው:: እናም ለማክሮ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና ያላቸው ኢንዱስትሪዎችን አሁን ካለው አገልግሎት በላቀ እና በአግባቡ ለማስተናገድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን መረጃዎች በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር እንዲሁም የሚሰጠውን አገልግሎት የተሳለጠ ለማድረግ ዘመናዊ የመረጃ ቋት መጠቀም አስፈላጊ ሆኗል::
የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲሁም ከተማዋ የብዙዎች ምርጫ እየሆነች ስትመጣ ይህንን ሊመጥን የሚችል የአገልግሎት አሰጣጥ ሊኖር እንደሚገባ ታምኖበት መረጃዎችን ወደ ዲጂታል ስርዓት የማስገባት ሂደት ውስጥ ተገብቷል::
ኤሌክትሮኒክስ የመሬት አስተዳደር እና የመረጃ ስርዓት (ELMIS – Electronic Land Management Information System) ለመጠቀም ከፌዴራል ከተማ ልማት ሚኒስቴር እና ከክልሉ መሰረተ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ከተማ አስተዳደሩ ወደ ሥራ ገብቷል:: የመረጃ ስርዓቱን በስምንት ከተሞች ወደ ሥራ ለማስገባት በፌዴራል መንግሥት በኩል በትኩረት እየተሠራ ሲሆን እስካሁን ወደ ሥራ የገባው የደብረ ብርሐን ከተማ ስለመሆኑ ተጠቁሟል:: የፌዴራል ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ደግሞ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ ስለማድረጉ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል::
እንደ ወይዘሮ እታለማሁ ማብራሪያ የደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር ዲጂታል የመረጃ ስርዓቱ ለመጠቀም ሲነሳ የመሬት ዘርፍ አገልግሎትን ከወረቀት ንክኪ ነጻ በማድረግ የመረጃዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል:: በሌላ በኩል ወቅቱ የሚፈልገውን ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በመሰረታዊ ምክንያትነት ተጠቃሽ ስለመሆናቸው በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል::
የኤሌክትሮኒክ መሬት አስተዳደር እና መረጃ ስርዓት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚያደርግላቸው ተቋማት መካከል የከተማ መሬት ዝግጅት ፣ ይዞታ አስተዳደርና ፕላን አፈጻጸም፣ ሕንጻ ሹም ተጠሪ ጽ/ቤት እና የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው:: በከተማ አስተዳደሩ አስካሁን ከ38 ሺህ 500 በላይ መረጃዎች ወደ ሲስተሙ ገብተዋል:: ከዚህ ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት የባለይዞታ መረጃዎች ወደ መረጃ ቋቱ ገብተዋል::
አሠራሩ በመዘመኑም ተገልጋዮች ከዚህ በፊት ይዘው እንዲቀርቡ ከሚገደዱባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የባለይዞታ ማመልከቻ አንዱ እንደነበር ወ/ሮ እታለማሁ አስታውሰዋል:: አሁን ላይ ግን የባለ ይዞታ መረጃዎቻቸው ወደ ዲጂታል ስርዓት ስለገቡ በቀላሉ በማየት ወደ ሚቀጥለው ክፍል እንዲተላለፍ ይደረጋል:: አገልግሎቱ ባለጉዳዮች ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንደደረሱ ጉዳያቸውን ከመቀበል ጀምሮ ወደ ሚመለከተው አካል እንዲሄዱ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው::
ወደ ስራ የገባው የመረጃ ስርዓት መረጃዎችን በአግባቡ ለመያዝና የሚፈለገውን አገልግሎት በአግባቡ ለመስጠት እንደሚያስችልም የከተማ አስተዳደሩ ወ/ሮ እታለማሁ ተናግረዋል:: በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሺህ በላይ የባለይዞታ መረጃዎች ትክክለኛነት ተረጋግጦ ወደ ዲጂታል የመረጃ ስርዓት ለማስገባት እየተሠራ ስለመሆኑም አክለዋል:: ከዚህ በኋላም የሚመዘገቡ መረጃዎችን በቀጥታ ወደ መረጃ ቋቱ ያስገባል:: ይህም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንሚያስችል ገልጸዋል::
(በላይ ተስፋዬ)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም