ደብረ ታቦር የመጀመሪያዋ የኢንዱስትሪ ከተማ 

0
104

በሀገራችን ከሚገኙ ቀደምት ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ደብረታቦር ከተማ የበርካታ ፀጋዎች ባለቤትም ናት:: በአፍሪካ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር (ጋፋት) የተገነባባት ከተማም ናት::

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ ተራራዎች አንዱ የሆነው የጉና ተራራ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሲሆን  የአየር ንብረቷ ወይና ደጋ እና ቀዝቃዛ ነው:: የከተማዋ መቆርቆሪያ ከሆነው የታቦር ተራራ አናቱ ላይ ሆኖ የደብረታቦርን ከተማ እና የአካባቢዋን አረንጓዴ ተፈጥሮ ለመመልከት ምቹ ነው::

ደብረታቦር የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት እና የባሕል ታሪክ የሚያሳዩ እጅግ ተፈላጊ ቅርሶች ያሉባት ከተማም ናት:: 117 ነጥብ 13 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ከተማዋ የሕዝብ ቁጥሯም 206 ሺህ 949 እንደሆነ የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ መረጃ ያመላክታል፤ በመምሪያው የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኢንዱስትሪ ዞን ልማት ቡድን መሪ አቶ ዋለ ዓለሙ ከበኩር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ደብረታቦር በሦስት ክፍለ ከተማ፣ በዘጠኝ የከተማ እና በአራት የገጠር በድምሩ በ13 ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ናት::

በከተማዋ የሚገኙ ዋና ዋና ሀብቶች መካከል ለተለያዩ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት የሚያገለግል የሰብል ምርት፣ የእንስሳት፣ የማዕድን እና የደን ሀብት እንዲሁም የኃይል አማራጭ ይጠቀሳሉ፤ በቂ የሰው ኃይል የሚገኝባት ከተማ እንደሆነችም አብራርተዋል::

ሰፊ መሬት ያለበት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች የሚመረቱበት (የሚገኙበት) ያልተነካ እምቅ የጥቁር ድንጋይ እና ካወሊን ማዕድን ሀብት የሚገኝባት አካባቢም ናት፤  የከተማዋን ሀብቶች ለማስተዋወቅ ታዲያ “ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል የንቅናቄ መድረክ እየተከናወነ ነው::

 

በከተማዋ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በንብ ሀብት ልማት፣ በቢራ ገብስ፣ በእንስሳት መኖ፣  ፓስታና ማካሮኒ፣ ብስኩት፣ በምግብ ዘይት፣ በቲማቲም ድልህ፣ በስጋ እና የስጋ ውጤቶች፣ ወተት እና የወተት ውጤቶች፣ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ በጋርመንት (ልብስ ስፌት)፣ በቆዳ እና ጫማ፣ በሹራብ፣ በወረቀት፣ በችፑድ (ኤም ዲ ኤፍ)፣ በቀርቀሀ ማቀነባበሪያ፣ ያለቀለት ጣውላ ማምረቻ (ኮምፖርሳቶን)፣ በእንስሳት እርባታ እና ማድለብ፣ በጥራጥሬ እህል ምርት ውጤቶችን ማቀነባበር፣ የድንጋይ ውጤቶችን፣ በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ በፕላስቲክ ጫማ እና ሶል፣ በሳሙና፣ በዶሮ እርባታ እና በሌሎች ዘርፎች ቢሰማሩ  ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የቡድን መሪው አቶ ዋለ ዓለሙ ጠቅሰዋል::

ከተማዋ በአገልግሎት ዘርፉም በሆቴል እና ቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በዘመናዊ ሎጂዎች፣ በመዝናኛ እና መናፈሻ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ነው የተናገሩት::

በአጠቃላይ የከተማዋ ሕዝብ ሥራ ወዳድ፣ አካባቢዋም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ፀጋዎች  የታደለ እና ገና ያልተነካ እምቅ ሀብት (የሚዳሰስ እና የማይዳሰስ) ያለባት ናት፡፡

ይህን ሁሉ ሀብት በመጠቀም ከራስ ባለፈ የተቀዛቀዘውን የከተማዋን ኢንቨስትመንት ማጠናከር እና ከተማዋን ለማልማት ባለሀብቶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል::

እንደ አቶ ዋለ ገለጻ በከተማዋ 190 ባለሀብቶች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ከዚህ ውስጥ 138ቱ ሥራ ላይ ናቸው:: እነዚህም ለስድስት ሺህ 419 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል:: በተያዘው በጀት ዓመትም ለሦስት ፕሮጀክቶች ስምንት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ተሰጥቷል::

ቡድን መሪው እንዳሉት በሥራ ላይ የሚገኙት ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በተለይም የመብራት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው:: ግንባታቸውን ያቋረጡ ፕሮጀክቶች ደግሞ ግንባታቸውን እንዲያጠናቅቁ እየተሠራ ነው::

በሌላ በኩል በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ያልገቡትን አልሚዎችም ምክረ ሐሳቦችን እና ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ተግባራዊ ያላደረጉት ላይ መሬት እስከመንጠቅ ተደርሷል ብለዋል:: በበጀት ዓመቱ በ42 ባለሀብቶች ከቃል ማስጠንቀቂያ አስከ ፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል:: 26 ባለሀብቶችም መሬት እንዲመልሱ ተደርጓል::

 

በከተማዋ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች

ለተሻለ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ አቅርቦት መኖሩ፣ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመስማማት የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የሚያገለግሉ ምርቶችን በቀላሉ መጠቀም የሚቻል መሆኑ፣  የሰለጠነ እና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚቻል የሰው ኃይል መኖሩ፣ ለአምራች ኢንቨስትመንት ዘርፍ ግብዓት የሚሆን የደን፣ የስጋ፣ የወተት፣ የቆዳና ሌጦ እና ሌሎች ምርቶች በብዛት መገኘታቸው፣ ከከተማዋ ቅርብ ርቀት (ወረታ አካባቢ) የደረቅ ወደብ መኖሩ የዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው::

 

ኢንቨስትመንቱ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች

የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት፣ ባለሀብቶቹ ማስፋፊያ መሬት በሚጠይቁበት ጊዜ መሬቱን ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ አለማስረከብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የተበላሹ መንገዶችን በተገቢው መንገድ አለመጠገን ይህም ምርትን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ እንቅፋት መፍጠሩ፣ የሳይት ፕላን አለመስተካከል፣ ፈጣን ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ላይ የቅንጅታዊ አሠራር ክፍተት እና መገፋፋት መኖሩ፣ ባለሀብቱ የራሱን አቅም አሟጦ አለመሥራት፣ መሬትን አጥሮ ማስቀመጥ እና ግንባታዎችን ማቋረጥ ደግሞ በዘርፉ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ ዋለ ኣለሙ ጠቅሰዋል::

ችግሮቹን ለመፍታት ታዲያ መንግሥት እና ባለሀብቱ ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል:: ከተንዛዛ የቢሮክራሲ አሠራር መውጣት፣ ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የአጋር አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር እንዲሁም አመራሩ እና ሌሎች አካላት ርብርብ ማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት ያስችላል ሲሉ ያቀረቧቸው ናቸው::

ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር  ግንባታቸውን ያቋረጡ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሁሉ  ችግሩ ሳይበግራቸው በሥራ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች መኖራቸውን የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን ገልጸዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የአካባቢውን የባሕር ዛፍ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም “ፕለይውድ” ማምረት ላይ የሚገኘው ፋብሪካ አንዱ መሆኑን አንስተዋል:: ፋብሪካው ውጤታማ በመሆኑ ተረፈ ምርቱን  ወደ ሌላ ምርት መቀየር የሚችል ፋብሪካ እንዲገነባ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል:: ፋብሪካዎቹ ከአካባቢው ባለፈ ለሀገርም የጎላ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል::

ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል:: ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ማነቆዎችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስተመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አዲሴ መብራቴ እንደተናገሩት ቢሮው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ነዉ:: ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል:: በተለይ ደግሞ መሠረተ ልማት የማሟላት እና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት:: በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ይታይ የነበረውን የኃይል አቅርቦት መፍታት መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል::

 

ዜና

 

ፋብሪካው ሥራ ጀመረ

 

በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የሚገኘው የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወደ ሥራ ገብቷል። ፋብሪካው በ2010 ዓ.ም በ170 ሚሊዮን ብር ወደ ግንባታ መግባቱን የ”ውከሶንክ እና የጀወከሹ” ፋብሪካ ምክትል አሥተባባሪ አበበ ተስፋዬ ተናግረዋል። ፋብሪካው የአካባቢውን ባሕር ዛፋ በመጠቀም ለኮንስትራክሽን አገልግሎት የሚውል ፕላይውድ እያመረተ ይገኛል።

ከሰሞኑ ደግሞ እህት ኩባንያ የሆነው የ”ጀወከሹ ላሚኔት ፈርኒቸር” ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ  አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀ ወደ ሥራ መግባቱን ነው  ምክትል አሥተባባሪው የገለጹት።  ፋብሪካው የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ተረፈ ምርትን በመጠቀም የ”ላሚኔቲንግ” ሥራ የሚሠራ ነው።

ፕለይውድ ማምረት ላይ የሚገኘው ፋብሪካው ለ234 ሠራተኞች በቋሚነት እና ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት። አሁን ላይ የተጠናቀቀው እህት ኩባንያም ተመሳሳይ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን የሥራ እንቅስቃሴ ከሰሞኑ ተመልክተዋል። በአዲስ የተገነባው እና እህት ኩባንያ የሆነውን የ”ጀወከሹ ላሚኔት ፈርኒቸር” ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ሥራም  አስጀምረዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here