ከመዝናኛው ዘርፉ ከፊልሙ ኢንዱስትሪ ቀጥሎ የእግር ኳስ ስፖርት ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ መሆኑን የፎርብስ መጽሔት መረጃ ያስነብባል። በዚህ ተወዳጅ ስፖርት ባለ ተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ድንቅ አቋም ከተመልካች እና ከደጋፊ ብዙ ተከታይ እና አድናቆትን ያገኛሉ::ከሜዳ ውጪም የተሟላ ስብዕና ያላቸው ከሆኑ ደግሞ እንደ ንጉሥ ክብር እና ሞገስን ያገኛሉ::
ሙያቸውን የሚያከብሩ፣ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ፣ በወጣው ሕግ የሚተዳደሩ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ፣ በአዕምሯቸው የማሸነፍ ሥነ ልቦናን የተላበሱ፣ ድክመታቸውን ለማሻሻል የሚተጉ እና ዝግጁ የሆኑ ተጨዋቾች እንዳሉ ሁሉ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ያልተገራ ባህሪ ያላቸው የእግር ኳስ ተጨዋቾችን መመልከት እንግዳ አይደለም::
ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በሚፈስበት የእግር ኳስ ስፖርት ተጫዋቾቹም በብዙ ተቋዳሽ መሆናቸው ይታወቃል:: በዚህ ሳቢያም በየጊዜው ጥቂት የማይባሉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሙያቸው ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ገንዘባቸውን እንደመሣሪያ ተጠቅመው አልባሌ ሥራ ሲሠሩ ማየት የተለመደ ነው።
በስካር መንፈስ ማሽከርከር፣ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸም፣ ሴቶችን መደባደብ በአጠቃላይ በክለቡ የተከለከሉ ሕጎችን መጣስ እና የመሳሰሉት በተደጋጋሚ በተጫዋቾች ከሜዳ ውጪ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ግድፈቶች ናቸው።
በተለይ ስመ ጥር ተጫዋቾች ስሜት አሸንፏቸው ከተሰቀሉበት የዝና ማማ የተፈጠፈጡ፣ ከሚሊየነርነት በአንድ ጀምበር ወደ ድህነት የተቀላቀሉ በርካቶች ናቸው።
በቅርቡም ሁለት የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከቦች በፈፀሙት ወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን የዓለም የስፖርት የመገናኛ አውታሮች በስፋት ሲዘግቡት ሰምተናል፤አንብበናል። ይሄንን ነውር ድርጊት የፈጸሙት ደግሞ ብራዚላውያኑ ዳኒ አልቬዝ እና ሮቢንሆ ናቸው።
በዚህ ሳምንት የበኩር ስፖርት አምዳችን በአንድ ወቅት በእግር ኳስ ስፖርት ከፍ ብለው የተቀመጡትን ነገር ግን ምግባራቸው፣ ተግባራቸው ለወጣቶቹ አርዓያ የማይሆን እና ስማቸውን የሚያጎድፍ አስነዋሪ ወንጀል የሠሩትን የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንዳስሳለን።
ይህ ስም ባለፉት 20 ዓመታት በዓለማችን እግር ኳስ ከፍ ብሎ ተወድሷል። በትውልዱ ካሉ ምርጥ የቀኝ መስመር ተከላካዮች ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋል።በእግር ኳስ ህይወቱ በርካታ ዋንጫዎችን ያሳካ ቀዳሚው ተጫዋች ነው – የቀደሞው የባርሰሎና ኮከብ ዳኒ አልቬዝ። ብራዚላዊው የቀድሞ ተከላካይ ለዓመታት የገነባውን ስም እና ዝና በአንድ ጀምበር ንዶታል።
በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሶ ወራት በማረሚያ ቤት አሳልፏል። የ40 ዓመቱ ብራዚላዊ በ2022 እ.አ.አ በስፔን ባርሰሎና ከተማ በምሽት ክለብ ውስጥ አንዲትን ሴት አስገድዶ በመድፈሩ ነው የተከሰሰው። የስፔን ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ለሁለት ዓመታት ሲያጣራ ቆይቶ ዳኒ አልቬዝ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የአራት ዓመት ከስድስት ወር የእስር ፍርድ እንደፈረደበት ቢቢሲ አስነብቧል። እስሩ ግን ወደ ገንዘብ እንደተቀየረለት መረጃዎች አመልክተዋል::
የባንክ ሂሳቡ በመታገዱ የተጠየቀውን አንድ ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብም የቀድሞው የቡድን አጋሩ ኔዘርላንዳዊው ሜፕስ ዴፓይ እንደከፈለለት መረጃዎች ወጥተዋል። ዳኒ አልቬዝ ማረሚያ ቤት በነበረባቸው ወራቶች ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ እንደነበር ስፔናዊው ጋዜጠኛ ፓውሎ አልቡኩራኪ በቅርቡ ተናግሯል።
አልቬዝ በባርሰሎና በቆየባቸው ስምንት ዓመታት የላሊጋ፣ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎችንም በርካታ ዋንጫዎች አሳክቷል። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ዘመኑ 42 ዋንጫዋችን በማንሳት ከሜሲ ቀጥሎ ሁለተኛው ተጫዋች ለመሆንም በቅቷል። ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ 3ኛው ተጫዋች የሆነው ዳኒ አልቬዝ፣ የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ በ2009 እና 2017 እ.አ.አ ከብራዚል ጋር አሳክቷል።
ሌላኛው ብራዚላዊ የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ፣ የሪያል ማድሪድ እና የኤስሚላን ተጫዋች ሮቢንሆ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሶ በቅርቡ ዘጠኝ ዓመት እንደተፈረደበት ይታወሳል።በ2013 እ.አ.አ ኤስሚላን በነበረበት ወቅት በሚላን ከተማ በሚገኘው የምሽት ክለብ ውስጥ አንዲት አልባኒያዊትን ሴት በመድፈር ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ተብሎ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። ከድርጊቱ በኋላ ሮቢንሆ ወደ አገሩ ብራዚል በመመለሱ ቅጣቱ አልተጣለበትም ነበር::
በወቅቱ ለጣሊያን መንግሥትም ተላልፎ ባለመሰጠቱ በአገሩ ሆኖ የሚጣልበትን የፍርድ ቅጣት እንዲቀበል የጣሊያን መንግሥት መጠየቁን መረጃዎች አመልክተዋል። ታዲያ የብራዚል መንግሥትም ውሳኔውን በመቀበል ዘጠኝ ዓመት በእስር ቤት እንዲያሳልፍ ወስኖበታል። በርካታ የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከቦች ይህንን ዜና ከሰሙ በኋላ በዳኒ አልቬዝ እና በሮቢንሆ ላይ የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
ብርዚላዊው የቀድሞ ተጫዋች ፊሊፔ ሜሎ ዳኒ አልቬዝ እና ሮቢንሆ በፈጸሙት ፆታዊ ጥቃት ለሌሎቹ ማስተማሪያ እንዲሆን ሊቀጡ ይገባል ሲል ተናግሯል። ታዳጊ ሴት ልጅ እንዳለችው የገለጸው ፊሊፔ ሜሎ “ እነሱ በልጄ ላይ ይህንን ቢያደርጉ ለቃለ ምልልስ ከዚህ አልመጣም ነበር፣ ላደርጉት ነገር ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ እንጂ” ሲል መናገሩን ቢቢሲ አስነብቧል።
ሮቢንሆ በዓለም እግር ኳስ የት ይደርሳሉ ? ከተባሉ እና ድንገት ደግሞ ታይተው ከጠፉ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
ፍራንክ ሪቤሪ እና ካሪም ቤንዜማም ሴተኛ አዳሪን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥረው እንደነበር የሚታወስ ነው። ሁለቱ የእግር ኳስ ኮከቦች አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላትን አልባኒያዊት ታዳጊ በተለያየ ጊዜ አስገድደው በመድፈራቸው ክስ ቀርቦባቸው ነበር። በዚህ ወንጀልም ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሦስት ዓመታት እስር እና የሞራል ካሳ ደግሞ ከ45 እስከ 55 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው የክስ ሂደቱ ያትት ነበር።
ይሁን እንጂ ሪቤሪ እና ቤንዜማ እስሩም ቅጣቱም ሳይጣልባቸው በነፃ ተለቀዋል። ምክንያቱ ደግሞ በፈረንሳይ ሕግ 18 ዓመት ያልሞላት ታዳጊ ሴተኛ አዳሪ መሆን ሰለሚከለከል ነው። ይህ አሳፋሪ ድርጊትም በቀድሞው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ካሪም ቤንዜማ የእግር ኳስ ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ አልፏል። በወቅቱ ጉዳዩን ኃያሉ ክለብ ሪያል ማድሪድ ትኩረት ባይሰጠውም የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ግን ተጫዋቹን ለሦስት ዓመታት አግዶት እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ ምክንያትም የ2016 የአውሮፓ ዋንጫ እና የ2018 የዓለም ዋንጫ ላይ መካፈል አልቻለም። ቤንዜማ ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት ሪያል ማድሪድን በመልቀቅ ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጉዞ አል አህሊን መቀላቀሉ ይታወቃል።
ፈረንሳዊው ተከላካይ ቤንጃሚን ሜንዲ በፕሪሚየር ሊጉ እንደ አጀማመሩ መጨረሻው ሳያምር ወደ አገሩ የተመለሰ ተጫዋች ነው:: የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲው ተከላካይ ለዓመታት በእግር ኳሱ የገነባውን ስም እና ዝና በፆታዊ ትንኮሳ ምክንያት ንዶታል:: በ2017 እ.አ.አ ከፈረንሳዩ ሞናኮ ኢትሀድ የደረሰው ሜንዲ በኋላ ክፍሉ ፔፕ ጓርዲዮላ ከሚተማመንባቸው ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነበር::
በ2022/23 የውድድር ዘመን በአራት ሴቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ፈፅሟል በሚል ተከሶ ለአራት ወራት በማረሚያ ቤት የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል ቆይቷል:: ተከላካዩ በመጨረሻ ጥፋተኛ አይደለህም ተብሎ በነፃ ቢለቀቅም ብዙ የሞራል እና የገንዘብ ኪሳራ እንደ ደረሰበት ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል::
በፆታዊ ትንኮሳ ተጠርጥሮ ማረሚያ ቤት ከገባ በኋላ ክለቡ ማንቸስተር ሲቲ ከተጫዋቹ ጋር የነበረውን የውል ስምምነት ማቋረጡ ተጫዋቹ የገንዘብ ችግር እንዲገጥመው አድርጎታል:: ለጠበቃ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ያደረገው ሜንዲ የእጅ ስዓቱን ሳይቀር ሸጦ ነው ወደ ሀገሩ ፈረንሳይ የተመለሰው:: አሁን በፈረንሳይ ሊግ አንድ በሚሳተፈው ክለብ ሎረንቴ እየተጫወተም ይገኛል::
በተመሳሳይ የቀድሞዎቹ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾቹ ሮይ ኪን፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ዴቪድ ዲህያ ፣ የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች አዳም ጆንሰን እና የመሳሰሉት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ተጫዋቾች ናቸው። እኛም በመልካም ብቻ ሳይሆን በአስነዋሪ ድርጊታቸው ጭምር ዓለም ከሚያስታውሳቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች የግል ታሪክ ታዳጊዎቹ ይማሩበታል በሚል ታሪካቸውን እንዲህ አስነብበናል።
ቢቢሲ ስፖርትን እና ዘ ኢንድፔንደንትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፥፣
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም