“ልቤ መንታ ሆኖ እንደ ፍየል ቆለ’
አንዱ እንሂድ ይላል አንዱ አርፈህ ተቀመጥ”
እያለ ባላገሩ ሲያቅራራ ውስጡ ሁለት ምርጫዎች አሉ። ጨለማ እና ብርሃን እንበላቸው። የሚጠቅመንን ለይቶ ማወቅ ነው የዛሬ ሐሳባችን። ዲሲፕሊን ጨለማውን የውስጥ ሰብዕና ታግሎ የሚበጀው ላይ ማተኮር ነው። ራስን መቆጣጠር ሌሎችን ከመቆጣጠር ይበልጣል። ሁለት የውስጥ ሰብዕናዎች የሚያደርጉትን ጦርነት ማሸነፍ ሰውን ከማሸነፍ ይበልጣል።
ብሪያን ትሬሲ “ኖ ኤክስኪዩዝ” በሚል መጽሐፉ ስለ ዲሲፕሊን ኀይል በስፋት አብራርቷል:: “አንዳንድ ሰዎች ለምን በጣም ስኬታማዎች ሆኑ፤ ለምን ብዙ ገንዘብ ይሰራሉ፤ ለምን ከሌሎች ተለይተው ደስተኞች ሆኑ፤ ትክክለኛው የስኬት ምስጢርስ ምንድን ነው? ሲል ይጠይቃል:: ብሪያን በሚሰጣቸው የንግድ እና ስራ ስልጠናዎች ሰዎችን “እስኪ ከእናንተ መሀል ሀብታም መሆን የማይፈልግ ማነው?” ሲል ይጠይቃቸዋል፤ ሁሉም ይስቃሉ:: ምን ያህል ሰዎች ክብደት መቀነስ እንደሚፈልጉ፤ ከብድር እዳ ነጻ መሆን የሚፈልጉትንም ጭምር ይጠይቃቸዋል:: ሁሉም ይስቃሉ:: መልስ ለመስጠት ሁሉም እጃቸውን ያነሳሉ:: ሁሉም ሰው የተጠየቁትን ሐሳቦች ይፈልጋቸዋል:: ጥሩ አኗኗርን፡ስኬታማ መሆንን፤ ጥሩ ክብደት ላይ መድረስን፤ከብድር እዳ ነጻ መውጣትን የሚጠላ የለም::
ብሪያን ሁላችንም የሰው ልጆች ከመፈለግ ባለፈ ጥሩ ሕይወት ለመኖር እንዴት ማሳካት እንደምንችል እውቀቱ እና መረዳቱ አለን ይላል:: ወደ ስኬት መዳረሻ ለመጓዝም ፍላጎቱ አለን ይላል:: “ይሁን እንጂ የስኬት ጉዞው ከመጀመሩ በፊት አንድ ቀን የሚል ሰበብን በማስቀመጥ መነሳሳታችንን እንገድበዋለን፤ቆይተንም እንገድለዋለን” በማለት ያብራራል::
አንድ ቀን መጽሐፍ አነብባለሁ፤ አንድ ቀን የሰውነት እንቅስቃሴ እጀምራለሁ፤ አንድ ቀን ስልጠናዎችን ወስጄ ገቢየን ለማሳደግ እሰራለሁ፤ አንድ ቀን የገንዘብ ነጻነቴን አረጋግጣለሁ፤ አንድ ቀን ሕልሜን አሳካለሁ በሚል ብዙዎች ካሰቡት እንዳልደረሱ ያትታል:: እንዲያውም 80 በመቶ የሚሆነው ሰው አንድ ቀን እንዲህ አደርጋለሁ በሚል ሰበብ በመደርደር ይኖራሉ ይላል ብሪያን ትሬሲ::
ብሪያን እንደሚለው የመጀመሪያው የስኬት ምስጢር “አንድ ቀን ከሚለው ከመንጋው የደሴት እሳቤ መውጣት” ነው:: ህይወት ማድረግ ወይም መተው ነው:: መወላወል ወይም ነገ አደርገዋለሁ ማለት ተገቢ አይደለምና::
“ተሸናፊዎች ሰበብ ይደረድራሉ፤ አሸናፊዎች ደግሞ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ” የሚለው ብሪያን ሰበበኞች ሐሳባቸው ተመሳሳይነት ያለው ስለ መሆኑ ይናገራል:: “በአስተዳደጌ ተበድያለሁ፤ ጥሩ ትምህርት አላገኘሁም፤ ገንዘብ የለኝም፤ አለቃየ ነዝናዛ ነው፤ ትዳሬ መጥፎ ነው፤ የሚደግፈኝ ሰው የለም፤ ኢኮኖሚው አስከፊ ነው” የሚሉትን እንደ ማሳያነት ይጠቅሳል::
“በህይወቴ 999 የስኬት ምስጢሮችን እና መርሆችን አንብቤያለሁ፤ ግን ያለ ዲሲፕሊን አንዳቸውም አይሰሩም:: እሱ ሲኖር ሁሉም የስኬት ምስጢሮች ይሰራሉ” በማለት ብሪያን ጽፏል:: ዲሲፕሊን የሚለውን ቃል ብዙ ሰዎች ከህይወት ልምዳቸው ተነስተው ተናግረውታል::
አልበርት ሁባርድ “ዲስፕሊን መስራት ያለብህን ተግባር ለመከወን፤ ተገቢነቱን መረዳት እናም ወደድህም ጠላህም ማድረግ ነው” ይላል:: ጅም ሮን በበኩሉ “ዲሲፕሊን ማለት በግቦችህ እና በመሳካታቸው መካከል ያለ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው ” ይላል:: አብርሀም ሊንከን “ዲሲፕሊን አሁን የምትፈልገውን እና በጣም የሚያስፈልግህን መምረጥ ነው” ሲል ይገልጸዋል:: በአጠቃላይ ሲገለጽ ዲሲፕሊን ካሰቡት ለመድረስ በጊዜያዊ ነገሮች አለመያዝ፤ ፈተናዎችን መሻገር፤ ረሀብን፣ ጥማትን፣ ርዛትን፣ ሳቅና ጨዋታን ወደ ጎን ትቶ እንዲሁም ተቋቁሞ ትልቁ ግብ ላይ መድረስ ነው:: በአማርኛችን “ቆራጥነት” ብለን ልንተረጉመው እንችላለን:: ለስራ የሚከፈል ዋጋ፤ ባሉበት ቦታ መጽናት፤ ሳላሳካው አላርፍም፤ ቢደክመኝም አላርፍም፤ በችግሮች ውስጥ ማለፍ አለብኝ ማለት ነው:: ወደድንም ጠላንም ስራው መሰራት ስላለበት ለስራው ዋጋ መክፈል ነው:: ቴያትር መድረክ ላይ ሆነው የቤተሰቦቻቸውን ሞት ሰምተው የሚተውኑ፤ እናቷን አጥታ ኮንሰርት የምታቀርብ ሴት፤ ጓደኛው ከፊቱ በጠላት በመድፍ ሲወድቅ ወደ ጠላት እሳት የሚተኩስ ወታደር የቆራጥነት ምሳሌዎች ተደርገው ይወሰዳሉ:: በዲሲፕሊን የተካኑ ናቸውም ይባላሉ::
“ሰልፍ ዲሲፕሊን ኢን ቴን ዴይስ” በሚለው መጽሐፉ ቴዎዶር ብሪያንት ከሐሳብ ወደ ተግባር መግባት የሚቻልባቸውን ሐሳቦች አስቀምጧል። ቴዎዶር እንደሚለው የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ለማሳካት የሚፈልገውን ነገር እንዳያደርግ እና እንዲያደርግ ሁለት የሚፋተጉ ማንነቶች አሉት። አንደኛው ንግድ መጀመር፣ ቤት ማጽዳት፣ ስፖርት መስራት፣መማር እና ሌሎች ፍሬያማ ተግባራትን እንድንሠራ የሚፈልግ ነው።ሁለተኛው ደግሞ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን እያቀያየረ ፊልም መመልከት የሚወድ ፤መዝናኛ ቦታዎች ጊዜን ማሳለፍን የሚፈልግ ነው። ራሳችሁን እንዳትገዙት አዕምሯችሁ የሚላችሁን ብቻ እንድትሰሙ እናም እንድታደርጉት የሚፈልግ ድብቅ ማንነት በውስጣችሁ አለ። የሰው ልጅ ደግሞ የስኬቱም ይሁን የውድቀቱ መንስኤ ራሱን ምን ያህል ይገዛል? ምን ያህል ዋጋ ይከፍላል? የሚለው ነው።
ድብቁ ማንነት ራሴን አደራጅቼ፤ ዓላማ እና ግብ አስቀምጨ ብሠራ በየቀኑ ተመሳሳይ ተግባራትን ያለ ማቋረጥ እሠራለሁ፤ ነጻነቴን አጣለሁ፤ ተዝናንቼ መኖር አልችልም፤ ብዙ ኀላፊነቶች ይጠበቁብኛል እና በራሴ ላይ ጭንቀት እፈጥራለሁ ብሎ ያስባል” ሲል ቴዎዶር ይገልጸዋል። ሁሉም የሰው ልጆች በውስጣቸው ምቾቱን ፈልጎ የሚያምጽ፤ነገሮችን ለመፈጸም ጉጉት የሌለው ሰብዕና አላቸው የሚለው ጽሐፊው “አመጸኛው ማንነታችሁ ጥረታችሁን እንዲያበላሽ አትፍቀዱለት” ሲል ይመክራል። ይህ ሰብዕና በውስጣችን መሽጎ ወደ ግባችን እንዳንራመድ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማል። ይጠራጠራል፣ አሉታዊ ነው፤ ይሸነፋል፤ ያመልጣል እንዲሁም ሆን ብሎ ይዘገያል። ይህ ነገር የሚያዋጣ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ያኛው ይቅርብኝ ብሎ ያመልጣል።
ይህን ነገር ማሳካት አልችልም ይላል፤ ወቅቱ አይመችም ይላል ነገ እሰራዋለሁ ብሎ አውቆ ይዘገያል። ይህ በውስጣችን ያለ ጨለማ ሰብዕና ሁልጊዜ አሉታዊ ሐሶቦችን ደጋግሞ በመንገር ጠንካራውን ሰብዕና ያዳክመዋል። የዲሲፕሊን ጦርነቱ በውስጣችን ተጀምሮ በውስጣችን ያልቃል። ሻለቃ አትሌት ኀይሌ ገብረ ስላሴ የሲድኒ ኦሎምፒክን በዲሲፕሊን እንዳሸነፈ፤ የሕይወት ስኬቱ ምስጢራት በሙሉ ለሚፈልገው ነገር የሚከፍለው ዋጋ መሆኑን ተናግሯል።
በቴዎዶር ሐሳብ መሠረት ኀይሌ በሲድኒ ኦሎምፒክ ሲሮጥ ፖልቴርጋት ጋር ያን መሳይ ትንቅንቅ ሲገጥም ሁለቱ ሰብዕናዎች እርስ በርስ ይጨቃጨቁ ነበር። እሱኮ ዛሬ በጥሩ አቋም ላይ ነው፤ አንተ በቂ ልምምድ አላደረግህም፤ፖል ደግሞ ማንም ማይበልጠው ጀግና ነው የሚል ሐሳብ በአንዱ ሰብዕናው ወደ ኋላ እየጎተተው ይሮጣል። በአንጻሩ ደግሞ “ኀይሌ አንተ እኮ የበቆጂን ገብስ እየበላህ ያደግህ ብረት እንዴት ፖል ይበልጥሃል፤ አንተ እኮ ይቻላል በሚል ምታምን ጀግና ነህ፤ ዋንጫው ያንተ ነው አይዞህ ቅደመው፤ ኢትዮጵያዊያን ባንዲራ ይዘው በየቤታቸው በቴሌቪዥን እያጨበጨቡልህ ነው፤ አይዞህ ፖልን ቀድመኸዋል” እያለ ጭብጨባውን እና ድሉን እየነገረ ወደ ፊት የሚገፋው ሰብዕናው አለ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኀይሌ አብዝቶ የሰማው ጎበዝ የሚለውን የውስጡን ሹክሹክታ ነበር። በመጨረሻም አሸንፎ ለድል በቅቷል። ኀይሌ ሲናገር “በዝግጅት እና በወቅቱ ሁኔታ ፖል የበለጠ ነበር” ብሏል። ይሁን እንጂ ኀይሌ አሉታዊውን በአዎንታዊው በመተካት ለአሸናፊነት በቅቷል።
የሰብዕና እድገት እና አስተሳሰብ ለውጥ አሰልጣኙ ዶክተር ኢዮብ ማሞ ዲሲፕሊንን ሲተረጉሙው እንዲህ ይላል። “መደረግ ያለበትን ነገር ስሜቴ ቢፈቅድም ባይፈቅድም፣ መደረግ ስላለበት ብቻ ማድረግ ማለት ነው:: እንዲሁም መደረግ የሌለበትን ነገር ስሜቴ ቢፈቅድም ባይፈቅድም መደረግ ስለሌለበት አለማድረግ ነው:: ማንኛውም ችሎታና ብቃት ከዲሲፕሊን ውጪ ከንቱ ነው:: ምክንያቱም ዲሲፕሊን ከሌለኝ ምንም እንኳ የማድረጉ እምቅ ብቃት ቢኖረኝና በነገሩ ባምንበትም ያንን ነገር ማድረግ ስለሚያስቸግረኝ ነው:: በሌላ አባባል ዲሲፕሊን ከሌለኝ መልካም ልማድን ለማዳበር ፈጽሞ አልችልም::”
ዶክተር ኢዮብ ሕይወትን በዲሲፕሊን መምራት የማይቻል ከሆነ፤ ነገሮችን ለመከወን ያለንበት ጊዜ፣ ሁኔታ እና ቦታ እንዲያሸንፈን እንፈቅድልታለን በማለት ጽፏል። ዓላማችን በየትኛውም ሁኔታ፣ ጊዜ፣ ቦታ ሊወሰን አይገባውም። መደረግ አለበት ካልን ሰርተን ውጤቱን ማሳየት አለብን ብሏል። ዲሲፕሊን ጊዜያዊ ስሜቶችን አልፎ መሄድ ነው። ዓላማችን እስኪሳካ በየትኛውም ሰበብ ለመዘግየት አለመፍቀድ ነው።
በዓለማችን የተሳካላቸው ሰዎች ለስኬታቸው ምክንያት አድርገው የሚጠቅሱት ጉዳይ ዲሲፕሊንን ነው። አንድ ተማሪ ኳስ ይወዳል እንበል። የማጠቃለያ ፈተና ሰሞን ማየት የሚፈልጋቸው የኳስ ግጥሚያዎች አሉ ብለን እናስብ። ይህ ተማሪ መሆን የሚፈልገው ዶክተር ነው። ይህ ተማሪ መሆን የሚፈልገውን አውቋል። ያሰበውን ለማሳካት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አውቋል። ራሱን በዲሲፕሊን ማስገዛትም ይጠበቅበታል። ዓላማን ማወቅ፣ ዋጋ መክፈል እና ዲሲፕሊን ለዚህ ተማሪ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ይህ ተማሪ ማንበቡን ሲጀምር ጓደኞቹ “ና እንጂ የኳስ ሰዓት ደረሰ እኮ ስንመለስ እናጠናለን” እያሉት ጥናቱን ትቶ ኳስ ጨዋታዎችን የሚከታተል ከሆነ ዓላማውን ስቷል። ይበልጥ በሚያስፈልገው ነገር ላይ አላተኮረም። ኳስ ጨዋታ መውደዱን በንባብ አስበልጧል እና የዲሲፕሊን ችግር ገጥሞታል። “ዓላማዬ ዶክተር መሆን ስለሆነ ኳስ ማየት የጥናት ጊዜየን ይሻማብኛል። ስለዚህ ኳስ አላይም አጠናለሁ እንጂ” ብሎ ይህንን ልምምድ መደጋገም የጀመረ ቀን ራሱን በዲሲፕሊን አስገዝቷል ማለት ነው። ቢደክመው፣ ቢደብረው፣ ጓደኞቹ ጋር ሲኒማ ማየት ቢያምረው፣ ኳስ ጨዋታ ማየት ቢያጓጓው በዲሲፕሊን የተገዛ ተማሪ ዶክተር ለመሆን በሚያስችለው ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል። ዋናውን ምርጫውን በጊዜያዊ ጉዳዮች አያስበልጥም።
ዶክተር ኢዮብም ዲሲፕሊንን ለማዳበር የሚጠቅሙ ሐሳቦችን አስቀምጧል። አንደኛው ግልጽ የሕይወት ዓላማ ማስቀመጥ ነው። ይህም ከየት ተነስቼ የት መሄድ እፈልጋለሁ የሚለውን ለይታችሁ እወቁ የሚለው ነው። በመቀጠልም ሁለተኛው ዓላማህን ለማሳካት ተገቢ ልምምድ ገንባ የሚለው ነው። ክብደት መቀነስ የሚፈልግ ሰው እና ዶክተር መሆን የሚፈልግ ሰው በየቀኑ የሚያደርጋቸው ልምምዶች አሉት። ልምምዶችህ ዓላማህን እንድታሳካ የሚጠቅሙህ ብቻ መሆን አለባቸው ይላል ዶክተር ኢዮብ። በመጨረሻም “ጀምር፣ ከጀመርህ አታቁም” የሚለው ነው። አሁን ለማዳበር የምትፈልገውን ዲሲፕሊን መከወን ጀምር ይላል። የጀመርከውን ለነገ አትበል፤ መጀመርም ደግሞ በቂ አይደለም። የተጀመረ ተግባር እንዲቆም፣ እንዲቋረጥ ምንም ምክንያት አትስጥ ይላል። ውጤቱን ስታገኝም ረክተህ አትቁም። ጉዞህን ወደ ፊት ቀጥል ይላል። ይህ የተግባር ድግግሞሽ የማይቀየር መልካም ልማድ እንድትገነባ ያግዝሃል ሲል ዶክተር ኢዮብ ይመክራል።
በመጨረሻም ቴዎዶር ዲሲፕሊን ራስን የመግዛት ስነልቦናዊ ልምምድ ነው ይለዋል። ዋናው ጉዳይ በሰው ልጅ ውስጥ ያሉ ጨለማ እና ብርሃን መሰል ሰብዕናዎችን መግዛት መቻል ስለመሆኑ ይነግረናል። “መሥራት የምፈልገውን እንዴት መሥራት እችላለሁ ብላችሁ አትስጉ ይላል። ይልቅስ መስራት የማይፈልገውን የውስጥ ጨለማ ሰብዕናዬን እንዴት ላሰራው እችላለሁ” ብላችሁ አስቡ ይላል። የሰው ልጆች ስኬት እንዳይሠሩ ከውስጣቸው የሚታገላቸውን አሉታዊ ሰብዕና እንዲሠራ ማሸነፋቸው ነው። “ልጆች እያላችሁ ወላጆች፣ መምህራን እና ሌሎች ሰዎች በሚሏችሁ ትመሩ ነበር። ዩንቨርሲቲ ስትገቡ ደግሞ ፕሮፌሰሮች የሚሏችሁን ትሰሙ ነበር። ሥራ ስትጀምሩም አለቆቻችሁ ይመሯችኋል። ይህ የዲሲፕሊን መገለጫ ቢመስልም እንኳን ብንስማማም ባንስማማም የምናደርገው ነው” ይላል ቴዎዶር።
ምን ማድረግ እንዳለብን፣ እንዴት እንደምናደርገው እና መቼ እንደምናደርገው አለቆቻችን ይነግሩናል። በዚህ ጊዜ ቴዎዶር የሚለው ስነልቦናዊ የውስጥ ትግል አይገጥመንም። በዚህም ምክንያት የዲሲፕሊን አዕምራዊ ጡንቻዎቻችን ትግል ውስጥ አይገቡም። አይዳብሩምም።ልምምድ ከሌለው ደግሞ ቴዎዶር እንደሚለው ዲሲፕሊናችን ልፍስፍስ እና ደካማ ይሆናል። በዚህ ጊዜ መሥራት የማይወደው ጨለማው፣ ሰነፉ፣ እንቅልፋሙ ሰብዕናችን ማንነታችንን መቆጣጠር ይጀምራል።
በሌላ አባባል ይላል ቴዎዶር አለቃችሁን “ያዘዝኸኝን ሥራ አልሰራውም፣ቴሌቪዥን ማየት ይኖርብኛል” ማለት አትችሉም ይላል። የራሳችሁ አለቃ ብትሆኑ ግን “ዛሬ አልችልም ነገ እሰራዋለሁ” የሚል ሞጋችነትን ታዳብሩ ነበር በማለት ያብራራል። በዚህ ንግግር የቴዎዶር በሌሎች ሰዎች አዛዥነት ስንገዛ ስለኖርን በራሳችን፤ ራሳችንን መግዛት አልቻልንም የሚል ነው። ራሳችንን በዲሲፕሊን ውስጥ አላሰለፍንም። በራሳችን መተማመን አልጀመርንም። አድርጉ የምንባለውን ተከትለን ስለምንጓዝ አዕምሯዊ የዲሲፕሊን ጡንቻችን አልዳበረም የሚለው ነው። “ዲሲፕሊን እንደ ጡንቻ ነው፤ ልምምድ ባደረጉበት መጠን ይጠነክራል” ብሏል የሰልፍ ዲሲፕሊን ኢን ቴን ዴይስ መጽሐፍ ደራሲ ቴዎዶር ብሪያንት።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም