ዳንዴዉ

0
75

አጭር ልቦለድ

ከንጋት እስከ ምሽት ጃምቦ እንደ ጅረት ከሚፈስባቸው፣ ጠርሙስና ብርጭቆ ከሚቃጭባቸው፣ ጮማ እንደ ጎመን ከሚቆረጥባቸው ሰፈሮች ባንዱ አስፋልት መንገድ ዳር ቁጭ ብየ ጫማ እያስጠረግሁ ነው፡፡ ድንገት ወፍራም፣ ረዥም፣ ፀጉረ ሉጫ ጎልማሳ እያዛጋ መጥቶ ከተቀመጥሁበት አግዳሚ ወንበር ጠርዝ ላይ ተቀመጠ፡፡ ጎልማሳው ቁጭ እንዳለ ከፊት ለፊታችን ጃምቦ እንዲሁም ቢራ ባይነት የሚጠጣባቸውን፣ ጮማ የሚቆረጥባቸውን… ቤቶች እየተመለከተ ደጋግሞ አዛጋ፤ መልከት አደረግሁት፡፡ ዓይኖቹ ቀልተዋል፤ ጉንጮቹ ሙልት ያሉ ናቸው፤ አንገቱ ረዥም፣ ደረቱ ያበጠ፣ ጡንቻው የፈረጠመ ነው፡፡  የለበሰው እጅጌ ጉርድ ጥቁር ሸሚዝ በወጉ ስላልተቆለፈ ደረቱ ተራቁቷል፡፡

ረዥም ወፍራም እጁን አወናጨፈና በረዣዥም ጣቶቹ ፀጉሩን እያከከ እንዳፈጠጠ፣ “ኧረ ጨለጠው! ኧረ ቆረጠው! እሄ ሆዳም!” አለና ደጋግሞ አዛጋ፤ የፈረደበትን ፀጉሩን ሳይበላው ደጋግሞ አከከው፡፡

ዓይኖቼ ዓይኖቹን ተከትለው ሄዱና፣ ያስፋልት መንገዱን በከፊል፣ የእግረኛውን መንገድ ሙሉ በሙሉ ዘግቶ፣ በጅምር ላይ ያለ ህንጻ ሰፊ አዳራሽ እንዲሁም በረንዳ ሞልቶ እየተንጫጫ ጮማ ከሚቆርጠው፣መጠጥ ከሚጨልጠው ምድረ በላተኛና ጠጪ ላይ አረፉ፡፡  ቤቱ ገበያ ደርቶለታል፤  “ጃምቦ!” ፣  “ቢራ!”  የሚሉ  ድምጾች  ከፍ  ብለው  ይሰማሉ፡፡

ነጭ ሸሚዝ እንዲሁም  ቀይ  ጉርድ  ቀሚስ የለበሱ አስተናጋጆች ፋታ  አጥተው  ይራወጣሉ፡፡ ቢራ እንዲሁም ጃምቦ ባይነት  ትሪ ሞልቶ ይቀርባል፡፡ ጮማ ሩብ፣ ግማሽ፣ አንድ ኪሎ… እየተባለ ይታዘዛል፤ እየተቆረጠ በጥሬው ይቀርባል፤ ወደ መጥበሻ ክፍል ይጋዛል፡፡

ዓይኖቼን ወደ ጎልማሳው መለስሁ፡፡ ባጋጣሚ እሱም ወደ እኔ በመዞሩ ዓይን ላይን ተጋጨን፡፡ ዓይኖቹ ቡጢ ቡጢ ያካክላሉ፤ ደግሞም ቀልተዋል፤ ከንፈሮቹ ደርቀዋል፤ ሰውነቱ የሚንቀጠቀጥ መሰለኝ፡፡ ‘ምን ታፈጥብኛለህ?!’ እንዳይለኝ ሰግቼ ዓይኖቼን መለስሁ፡፡

በዚህ ቅጽበት፣ “ጋሼ ከነጋ ጃምቦ አልቀመስሁም፤ ጠርሙስ አልጨበጥሁም፤ ሲጋራ ጠምቶኛል፤ እባክህ ትንሽ ገፍትር!” አለኝ፡፡

“የለኝም!” አልሁት ኮስተር ብየ፤ አባሮ መሥራት ለሚችል ወጠምሻ ሱስ ማስታገሻ የእኔ ኪስ  የሚራቆትበት  ምክንያት አልታይህ ስላለኝ፡፡

“ዳንዴው ደንበኞቼን ባታስቸግርብኝ ጥሩ ነው” አለ ጫማ ጠራጊው፤ በትህትና፡፡

ዳንዴው አካፋ በሚያክል እጁ ፊቱን እየሞዠቀ  ደጋግሞ አዛጋና ፀጉሩን አከከ፡፡

ከዚያም ከተቀመጠበት ተነሳና ተመልሶ ተቀመጠ፡፡ እንደተቀመጠ በድጋሜ አከታትሎ አዛጋና ወገቡን በሁለት እጆቹ ይዞ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡ እንደ ቆመ ወደ ሕዝቡ ይመለከት ጀመር፡፡

 

ዳንዴው ቆሞ ከጮማና መጠጥ  ጋር በሚፋለመው ሕዝብ ላይ አፈጠጠ፡፡ እንዲህ አፍጥጦ እንደቆመ ጃምቦ እንዲሁም ቢራ ሲጠጡ፣ ቁርጥ ሲቆርጡ የነበሩ አምስት ሰዎች ጠረጴዛቸው በጃምቦ ብርጭቆ እንዲሁም በቢራ ጠርሙስ እንደተሞላ ተነስተው ሲሄዱ አየ፡፡ የሰዎቹን መሄድ እንዳየ አይጥ እንዳየች ድመት ተወረወረና ጠረጴዛውን ወደ ሞላው የጃምቦ ብርጭቆ እንዲሁም የቢራ ጠርሙስ ሄደ፡፡ እንደ ደረሰ የጃምቦ ብርጭቆዎችን እንዲሁም የቢራ ጠርሙሶችን እያነሳ ትርፍራፊ መጠጥ ያንጫልጥ ገባ፡፡

በዚህ ቅጽበት ዝሆን የሚያክል ጎልማሳ፣ “ዳንዴው አትወጣም?! አንተ ልክስክስ! ውጣ!” እያለ ከህንጻው ወጣና እየገፈታተረ አባረረው፡፡

ዳንዴው ያንን መከረኛ ፀጉሩን እያከከ መጥቶ አጠገቤ ቆሞ፣ “ይሄ አሳማ እኮ ልክስክስ አለኝ! እሱ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የሚሠራውን ወንጀል የማናውቅ መሠለው፤ እያንዳንዷን እንቅስቃሴውን ጠንቅቀን እናውቃለን! ይሄ ልክስክስ!” አለ፤ በንዴት ተቀጣጥሎ፡፡

እንዲህ በንዴት እንደተቀጣጠለ ወደ እኔ እየተመለከተ፣ “ጋሼ እስኪ ሳትፈራ፣ ሳታዳላ እውነት ተናገር! እውነት መስክር! ማነው ልክስክስ? እኔ ወይስ ሥራ ሣይሠራ ከማለዳ እስከ ማታ እዚህ ቁጭ ብሎ ጮማ የሚቆርጠው፣ ቢራና ጃምቦ የሚጨልጠው?” ዳንዴው የተቀቀለ ጎመን የመሰለ ጥርሱን አግጥጦ፣ ቡጢ የሚያካክሉ ዓይኖቹን አፍጥጦ ጠየቀኝ፡፡

የምመልስለት ጠፍቶኝ ስመለከተው ወደ እኔ ተጠጋና፣ “ምስጢር ልንገርህ?” እንዳፈጠጠብኝ ጠየቀኝ፡፡

“እሽ ንገረኝ” አልሁት፤ በልቤ ዛሬ ይሄ ሰውየ አልለቀቀኝም እያልሁ፡፡

“እኔ እንደዚህ እንደምታየው መንጋ ሆዳም ሆዴን አስፍቼ ጮማ ምቆርጠጠው፣ ጃምቦና  ቢራ  የምጨልጠው ሥራ  ሥሠራ ነው፡፡ ባለፈው ምሽት አንድ ሥራ ሠርቼ ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኜሁ፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ጮማየን ስቆርጥ፣ ያላበው ቢራና ጃምቦ ስጨልጥ ሰነበትሁ፡፡ ከዚህ ከምታየው ምድረ ጠጪ አብዛኛው መጠጥ የሚያንጫልጠው እንደ እኔ ሥራ ስለሠራ ነው፡፡ ይሄንን እያውቀ ዛሬ ኪሴ ቢራቆት ይሄ አሳማ አባረረኝ፡፡ ነገ የተለመደውን ሥራ ሠርቼ  ከዚህ ሕዝብ መሀል ቁጭ ብየ ጠርቼው ጮማ ባላስቆርጠው፣  ጎንበስ ቀና ብሎ ቢራ እንዲከፍትልኝ ባላረገው ዳንዴው ብለህ አትጠራኝ!” አለኝና አስተያየት ለመስጠትም ሆነ ያልገባኝን ለመጠየቅ ዕድል ሳይሰጠኝ እጆቹን እያወራጨ ሄደ፡፡

ጫማ ጠራጊው አንደኛውን ጫማየን ጠርጎ በማጠናቀቁ ሁለተኛውን እንዳቀርብለት የሊስትሮ ዕቃውን በብሩሹ “ቋ!…ቋ!…” አደረገና ጫማየን ሳጥኑ ላይ ሳስቀምጥለት፣ “ጋሼ ግን የተናገረውን  ነገር ተረድተኸዋል?” ሲል ጠየቀኝ፡፡

“የተለመደውን ሥራ ሠርቼ ያለውን ነው?”  እየጠረገልኝ ያለውን ጫማ እየተመለከትሁ ጠየቅሁት፡፡

“የተለመደውን ሥራ ሠርቼ ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶሀል?”

“ሥራ ያው ሥራ ነው፤ ሌላ ምን ትርጉም አለው…”  በማለት የዳንዴው አባባል ግልጽ እንደሆነልኝ ገለጽሁለት፡፡

“የተለመደ ሥራ የሚለው ሀንግ ማድረጉን ነው “  አለኝ፡፡

የጫማ ጠራጊው ምላሽ አስደነገጠኝ፡፡ በድንጋጤ ውስጥ ሆኜ፣ “እውነትህን ነው?!” ስል ጠየቅሁት፤ በዚያ አካፋ በሚያክል እጁ የእኔ ቢጤውን ኮሳሳ አንቆ ላቡን ጠብ አድርጎ ያገኛትን ገንዘቡን፣ ስልኩን… ነጥቆ ሲወስድበት፣ የተነጠቀው ምስኪንም ቀልቡ ሲገፈፍ፣ ቀኑ ሲጨልምበት ባይነ ኅሊናየ እየታየኝ፡፡

“እውነቴን ነው፤ አሁን የሄደውም አሳቻ ቦታ ላይ ደፈጣ ለመጣል ነው፡፡ ጫካ ለብሶ፣ ድንጋይ ተንተርሶ ሲያደባ ይቆይና ብቸኛ ሰው፣ በተለይም ሴት ስትመጣ ጩቤውን መዝዞ በማውጣት እያስፈራራ  የያዘውን ወይም የያዘችውን አራግፎ ይወስዳል፤ ጮማውን ይቆርጣል፤ ጃምቦውንና ቢራውን ይጨልጣል” በማለት የዳንዴውን ሥራ ምንነትና ግቡን አብራራልኝ፡፡

“እኔ ልክስክስ አይደለሁም፤ ልክስክስ ሥራ ሣይሠራ ከማለዳ እስከ ማታ እዚህ ቁጭ ብሎ ጮማ የሚቆርጠው፣ ጃንቦና ቢራ የሚጨልጠው ነው ለማለት የደፈረው ታዲያ በየትኛው ንጹህ ኅሊናው ነው?” ዳንዴው የለየለት ቀማኛ ሆኖ ሳለ ሌሎችን ልክስክስ ማለቱ አናዶኝ ጫማ ጠራጊውን ጠየቅሁት፡፡

“የዳንዴው አባባል በከፊልም ቢሆን እውነት አለው፤ ጥሮ ግሮ፣በላቡ በወዙ ገንዘብ የሚያገኝ ሰው ከሥራ መልስ እንዳቅሙ ይዝናናል እንጂ ቀኑን ሙሉ በየቁርጥ ቤቱና በየጃምቦ ቤቱ ቁጭ ብሎ ጮማ ሲቆርጥ፣ መጠጥ ሲጨልጥ አይውልም፡፡ በሕይዎቱ ሊያሳካው  የሚፈልገው ዓላማም አለው፡፡ ያንን ዓላማውን የሚያሳካውም ጥሮ ግሮ የሚያገኛትን ገንዘብ በቁጠባ በመጠቀም ነው” አለኝ፤ ጫማ ጠራጊው፡፡

ጫማ ጠራጊው ዓላማ ያለው ሰው በየቀኑ ቁርጥ በመቁረጥ፣ ጃምቦና ቢራ በመጨለጥ ገንዘቡን እንደማያጠፋ ሲነግረኝ ከተማችንን ባራቱም ማዕዘን፣ በየጓዳ ጎድጓዳው፣  በያውራ ጎዳናው ዳር … የወረራትን ለቁጥር የሚታክት ቁርጥና ጃምቦ ቤት እንዲሁም ግሮሰሪ በእግረ ኅሊና እየተጓዝሁ እመለከት ጀመር፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለውን ቁርጥና ጃምቦ ቤት እንዲሁም ግሮሰሪ በእግረ ኅሊና ስመለከት በያንዳንዱ ቁርጥና ጃምቦ ቤት እንዲሁም ግሮሰሪ አዳራሽ፣ ሳሎንና በረንዳ፣ የእግረኛ እንዲሁም የመኪና መንገድ…  ሁለት፣ ሦሥት፣ አራት፣ አምስት… እየሆነ ጠረጴዛ ሞልቶ ጮማ የሚቆርጠው፣ ጃምቦ እንዲሁም ቢራ እያማረጠ የሚጠጣው ሕዝበ አዳም ጠረጴዛ ከሞላው ብርጭቆና ጠርሙሱ ጋር ታየኝ፡፡

ይህ ለማመን የሚከብድ ዘመን አመጣሽ ወረርሽኝ ባይነ ኅሊናየ ሲታየኝ፣ ‘በየዕለቱ እንዲህ ጮማ የሚቆረጥበት፣ ጃምቦና ቢራ በያይነቱ የሚጠጣበት ገንዘብ ከየት ነው የሚመጣው?’ የሚል ጥያቄ አጫረብኝ፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሳላገኝለት፣ “የእገታ፣ የቅሚያ፣ የግድያ… ወንጀልስ ይህን ያህል ለምን ተስፋፋ?’ የሚል ጥያቄ በአእምሮየ ጓዳ ያቃጭል ያዘ፡፡

በዚህ ቅጽበት ጫማ ጠራጊው የሊስትሮ ሳጥኑን አንኳኳ፡፡ ኳኳታውን ተከትሎ ሲያስጨንቀኝ የነበረው ጥያቄ ለጊዜውም  ቢሆን እልም ብሎ ጠፋ፡፡ የሊስትሮ ሳጥኑን በማንኳኳት መልስ ላገኝለት ከማልችለው ሞጋች ጥያቄ የገላገለኝን ጫማ ጠራጊ በልቤ እያመሰገንሁ የጠረገበትን ሂሳብ ጉርሻ ጨምሬ ከፍየ፣ “በል አሥራ ሁለት ሰዓት ሆኗል፤ አንተም በጊዜ ብትገባ ይሻላል” እያልሁት ተነሳሁ፡፡

እሱም ቀለሙን፣ ቡሩሹን፣ ስትራሾውን… ሳጥኑ ውስጥ እየከተተ፣ “ለማንኛውም ነገ ብቅ በል፤ ዳንዴውን እንደፎከረው ሥራውን ሠርቶ ከዚህ ሕዝብ መሀል ጉብ ብሎ ጮማ ሲቆርጥ፣ ጃምቦ ወይም ቢራ ሲጨልጥ ታገኜዋለህ” አለኝ፤ አሻግሮ ቁጥሩ በየደቂቃው እየጨመረ ሄዶ አስፋልት መንገዱን የዘጋውን በላተኛ እንዲሁም ጠጪ እየተመለከተ፡፡

“ነገ ማክሰኞ ስለሆነ እንደዛሬው  ከሥራ ስመለስ በዚህ በኩል ጎራ ለማለት እሞክራለሁ” አልሁትና ዳንዴው የሄደበትን የቤቴን ጎዳና ይዤ  ጉዞ ጀመርሁ፡፡

“ጋሼ ዳንዴው በሄደበት መንገድ የምትሄድ ከሆነ ለማንኛውም ጠንቀቅ በል!” ሲል ጫማ ጠራጊው አስጠነቀቀኝ፡፡

ጫማ ጠራጊው እንድጠነቀቅ ሲመክረኝ የእጅ ሰዓቴን መልከት አደረግሁ፤ ከቀኑ 12፡10 ይላል፡፡ የሚጠብቀኝ የግማሽ ሰዓት የውስጥ ለውስጥ ጠመዝማዛ መንገድ ነበር፡፡ እናም ለማስጠንቀቂያው አመስግኜው ወደ ቤቴ ጉዞየን ቀጠልሁ፡፡

አምስት ደቂቃ ያህል እንደተጓዝሁ ከኋላየ፣ “ጋሼ!” የሚል ድምጽ ሰማሁ፤ ዞር ስል ካንድ ወር በፊት ያሥራ ዘጠኝ ዓመት ልጁ  ስልክ፣ ሰዓት፣ ብር…  በጠራራ ፀሐይ መንደር መሀል በቀማኞች የተወሰደበት ጎረቤቴ ሆኖ አገኜሁት፡፡

ጎን ለጎን ሆነን እያወጋን እየሄድን እያለ  የባሕር ዛፍ ተክል እጅብ ብሎ ከሚገኝበት መሿለኪያ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን፣ “ድረሱልኝ! ኡ! ኡ!” የሚል የሴት ድምጽ ሰማን፡፡ ድምጹን ወደ ሰማንበት አካባቢ እየተሯሯጥን ስንሄድ ዳንዴው መንገደኛውን እየገፈታተረ ሲሮጥ ተመለከትን፡፡

ባካባቢው የነበርን መንገደኞች ዳንዴውን ለመከተል ብንሞክርም በጠመዝማዛው  መንገድ ታጥፎ ካይናችን ተሰወረ፡፡ ሴትዮዋ የነጣቂውን ማምለጥ ስታይ፣ “ደመወዝ ተቀብየ ምኗን ከምን ነው የማረጋት? እያልሁ እያሰላሰልሁ ስጓዝ ደመወዜን፣ ስልኬንም… ነጥቆኝ ሮጠ፡፡ አሁን ልጆቼን ምንድነው የማደርጋቸው? የቤት ኪራይስ ከምን አምጥቼ ነው የምከፍለው?” እያለች ጩኸቷን ለቃ ለቃ ተወችው፡፡

“ዳንዴው እንደፎከረው ሥራውን ሠራ ማለት ነው…’ እያልሁ ራሴ ለራሴ ወግ ጀመርሁ፡፡ በዚህ መሀል፣ “ይሄ ሰውየ የዚህን ሰፈር ሕዝብ ግጦ በላው!” የጎረቤቴ ንግግር አባነነኝ፡፡

“ታውቀዋለህ እንዴ?!” ስል በመገረም ጠየቅሁት፤ ዳንዴውን ጎረቤቴ ካወቀው እኔ እስከ ዛሬ እንዴት ሳላውቀው ቀረሁ በሚል፡፡

“እሱን የማያውቅ ማን አለ ብለህ ነው!” ሲል መለሰልኝ፡፡

“ከታወቀ ታዲያ እንዴት ሰው አድፍጦ አይዘውም?” ስል ጥያቄ አስከተልሁ፡፡

“ይያዛል፤ ተመልሶ ይለቀቃል” በማለት መለሰልኝ፡፡

“ከተያዘ ለምንድነው የሚለቀቀው?” ግራ ተጋብቼ ጠየቅሁት፡፡

“እሱ የሁላችንም ጥያቄ ነው” በማለት መለሰልኝ፡፡

***

በማግስቱ የዳንዴውን መጨረሻ ለማየት ወደ ጫማ ጠራጊው ሄድሁ፡፡ ጫማ ጠራጊው፣ አግዳሚ ወንበሩ ላይ እንድቀመጥ ጋበዘኝ፤ በእጁ አግዳሚውን መታ መታ እያደረገ፡፡

ቁጭ እንዳልሁ ትናንት ከእሱ እንደተለየሁ ዳንዴው እሠራዋለሁ ያለውን ሥራ ሠርቶ ሲሮጥ እንዳየሁት ነገርሁት፡፡ በዚህ ጊዜ ጫማ ጠራጊው ፈገግ እያለ፣ “እንደ እሱ ከሆነማ አሁን ይመጣል” አለኝ፡፡

ጫማ ጠራጊው ይሄን ተናግሮ አሥር ደቂቃ ሳይሞላ ዳንዴው እንደፎከረው ካራት ጓደኞቹ ጋር እየተጀነነ ሄዶ ትናንት ትርፍራፊ መጠጥ ሲያንጫልጥ ከተባረረበት ቁርጥና ጃምቦ ቤት ሄዶ ቁጭ አለ፡፡ ቁጭ ከማለቱ አስተናጋጆች እሱንና ጓደኞቹን ሊታዘዙ እየተሯሯጡ መጡ፡፡ ዳንዴውና መሰሎቹ ቁርጣቸውን ሲቆርጡ፣ ጃምቧቸውንና ቢራቸውን ሲጨልጡ ዳንዴው ትናንት ማታ ደመወዟን እንዲሁም ስልኳን የቀማት ምስኪን የልጆች እናት ባይነ ኅሊናየ መጣችብኝና፣ ‘ምስኪን እንዴት ሆና ይሆን?’ ስል ራሴ ለራሴ መልስ አልባ ጥያቄ አቀረብሁ፡፡

***

ዳንዴው የሰፈራችንን ሴት ስልክ እንዲሁም ደመወዝ ከነጠቀ በኋላ የሰፈሩ ሰዎች ተሰብስበን “እስከ መቼ ነው የቀማኛ መጫዎቻ የምንሆነው?” በሚል አካባቢያችንን በጋራ ለመጠበቅና ዳንዴውን አድፍጠን ይዘን ለሕግ ለማቅረብ መከርን፡፡ መክረንም ባሳቻ ሰዓት ቦታ ቦታ  እየያዝን ዳንዴውን ለመጠባበቅ ተስማማን፡፡

 

በስምምነታችን መሠረት  ዳንዴውን ለመያዝ ማድፈጥ በጀመርን በሦሥተኛው ቀን ምሽት 12፡30 ላይ አንድ ጎልማሳ ተፍ ተፍ እያለ በዚያ ጠመዝማዛ መንገድ ሲሄድ ዳንዴው ከተደበቀበት ሮጦ በመውጣት ስልኩን፣ ገንዘቡን… ሲረከበው ቦታ ቦታ ይዘን ስንጠባበቅ የነበርን ያካባቢው ሰዎች ከብበን ለመያዝ ከተደበቅንበት እየተሯሯጥን  ወጥተን  ወደ ዳንዴው ሮጥን፡፡ ሆኖም ዳንዴውን ከበን ልንይዘው ስንል ስልኩንም ገንዘቡንም እንደያዘ ገፈታትሮን ሮጠ፤ ተከትለነው ሮጥን፡፡ ዳንዴው ከፊት እኛ ከኋላ እየተሯሯጥን አስፋልት መንገዱ ላይ ስንደርስ ሦሥት የፀጥታ አካላትን አገኜን፡፡

የፀጥታ አካላቱ፣ “ምንድነው?! ምንድነው?” እያሉ ሲጠጉን፣ “እሱ ሰርቆ ሊያመልጠን እየሮጠ  ነው” አልናቸው ወደ ዳንዴው እየጠቆምን፡፡ እነሱም ወደ ዳንዴው እየተመለከቱ፣ “ሊጎዳችሁ ስለሚችል ተመለሱ!! እኛ እንይዘዋለን!” አሉንና  ተከትለውት ሮጡ፡፡

(አባትሁን ዘገየ)

በኲር የግንቦት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here