ዳውሌ – ተሞክሮ የሚወሰድበት

0
51

አቶ አበበ በላቸው በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ ዳውሌ ተፋሰስ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው። በአካባቢያቸው የሚገኘው ተራራ በደን፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ የተሸፈነ በመሆኑ ለእይታ የሚማርክ፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ጥቅም የሚሰጥ ነው ብለውታል። ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ያለማንም ጎትጓች ጥቅሙን ተረድተው እየሠሩ ነው። እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አርሶ አደሮችም የተሠሩ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን ደኅንነት እያስጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የለሙ ተፋሰሶችን ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ ዘላቂነታቸውን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውንም አርሶ አደሩ ገልጸዋል። ለሰብልም ሆነ ለከብት ሳር ማብቀል ተስኗቸው የነበሩ መሬቶች ዛሬ ተመልሰው ወደ እርሻ ገብተው የተሻለ ምርት እየተገኘባቸው መሆኑንም አክለዋል። ይህ የሆነውም በየጊዜው የሚሠራው የአፈር እና የውኃ ጥበቃ ሥራ በዝናብ እና ጎርፍ ታጥቦ ይወሰድ የነበረውን ደለል አፈር በመሬቱ ላይ በማስቀረቱ ነው ብለዋል። የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በመሠራቱም ከምርት ውጭ የነበሩ መሬቶች ላይ የሰብል፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርቶችን እያስገኙን ነው ብለዋል።

አትክልት እና ፍራፍሬ፣  ጌሾ፣ ጤና አዳም እና ሌሎች ለገበያ ሽያጭ የሚውሉ አትክልቶችን በማልማት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ አበበ ነግረውናል። የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ እና በማልማት አነስተኛ የገጠር ከተማ ላይ 128 ዚንጎ ቤትም ሠርተዋል፤  በተጨማሪም የእርሻ በሬዎች፣ የወተት ላሞች፣ የተሻሻሉ የበግ እና የፍየል ዝርያዎችን ገዝተው እያረቡ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ ድሮ ይኖሩ ከነበሩበት ሕይወት በእጅጉ የተሻለ፤ በሚያገኙት ጥቅምም ደስተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈርን ጤንነት በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወሰኔ አንበርብር ናቸው። የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ ለፍጡራን ሁሉ መኖሪያ ለሆነችው መሬት ዋና መሠረት እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው ለዚህም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሰው ልጅን ህልውና እና ቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የጎርፍ መቀልበሻ እና የውኃ ማፋሰሻ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ የሚገኝበት ወረዳ መሆኑን ጠቁመዋል። በወረዳው በየዓመቱ የሚከናወነውን የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ አርሶ አደሩ ጥቅሙን ተረድቶ ያለማንም አነሳሽነት እና ባለቤትነት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ከምርት ውጭ የነበሩ መሬቶች አገግመው ወደ ምርት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በዋናነት የአፈር ክለትን በመጠበቅ እና በጎርፍ እና በወንዞች ሙላት ታጥቦ የሚሄደውን ኬሚካላዊ ይዘት በመታደግ ምርታማነት እንዲያድግ ያደርጋል። በተሠራው ሥራም ጠፍተው የነበሩ ሀገር በቀል ችግኞች እና የዱር እንስሳት የተመለሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አርሶ አደሩም በሠራው ሥራ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡ አካባቢውን በስነ ህይወታዊ ዘዴ አጠናክሮ ባይሠራ ኖሮ ለስደት እና ለከፋ ችግር ይጋለጥ ነበር ብለዋል። በተለይም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ የኅብረተሰብ ንቅናቄ በማድረግ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በሰፊው የተከናወነበት ነው ብለዋል። በመሆኑም የአፈር ለምነቱ ጨምሯል፣ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውኃ በመበልፀጉ አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜም ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱን ያስረዱት ኃላፊዉ የዳውሌ ተፋሰስ ልማት በወረዳው ካሉ የተፋሰስ ልማት አንዱ ነው ብለውታል። በመሆኑም ከወረዳው አልፎ ለደቡብ ሱዳንም ተሞክሮውን ያካፈለ መሆኑን ነው የተናገሩት። ኃላፊው እንዳሉት በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በአንድ ሺህ 438 ሄክታር  የሚሸፍኑ 53 ተፋሰሶችን ለማልማት እና ለማጠናከር ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በትኩረት በተሠራባቸው የክልሉ አካባቢዎች የአፈር ክለቱ  ከሰባት እስከ 22 በመቶ ቀንሷል።

እየተሠራ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራም ለከብት ግጦሽ ሳር ማብቀል የማይችሉት እና ከምርት ውጪ የሆኑ መሬቶች ወደ ሰብል ልማት እየተሸጋገሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቃሚነት ያላቸውን እጽዋቶች በመትከል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ በይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ክትትል እና ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

የዚህ ዓመት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ከታኅሳስ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ነው። የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራው እስከ መጪው መጋቢት አጋማሽ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። ለአርሶ አደሩ ሰፊ ጊዜ እንዲሰጠው የተደረገውም ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንዲቻል መሆኑን አብራርተዋል።

በ2018 ዓ.ም ለሚከናወነው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ አስፈላጊው  ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን እና በዚህ መሰረትም በአማራ ክልል 456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን እቅድ መያዙን እንዲሁም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው ዘጠኝ ሺህ 206 ተፋሰሶች መለየታቸውን ነው ኃላፊዉ የገለጹት፡፡

በቀደሙት ዓመታት ቀድሞ የተሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በዘር ወቅት በዘር ለመሸፈን ሲባል ተመልሶ ይደፈን እና ይፈርስ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ችግሩ እንዳልተቀረፈ አመላክተዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ብርቱ ጥረት እና ከአርሶ አደሩ ጋር መግባባት መፍጠር እንደሚገባ አመላክተዋል። ከነበሩ ችግሮች መካከልም በቂ በጀት አለመመደብ፣ ኅብረተሰቡ ምን እንደሚሠራ፣ ለማን እንደሚሠራ እና ምን ጥቅም ሊያገኝ እንደሚሠራ አሳምኖ አለመሥራት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አድርጎ መመልከት አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ጉዳት ሳይደርስባቸው ቀድሞ መንከባከብ እና መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ የሚቆም አለመሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሆኑን አስረድተዋል። የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ማኅበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪው ኃይሉ ክንዴ (ዶ/ር) የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሲባል ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ እንደ አፈር፣ ውኃ፣ አየር፣ እፅዋት፣ ማዕድናትን… በአጠቃላይ የተፈጥሮ ስጦታዎችን በአግባቡ፣ በቁጠባ እና በጥንቃቄ መያዝ ወይም መጠቀም እንደሆነ ያብራራሉ። የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራው ለምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ትኩረት ተግባራዊ ያደረገችው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነት እንዲሻሻል ማድረጉን ጠቁመዋል። ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ የዳውሌ ተፋሰስ ልማትን አንስተዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የተናገሩት ተመራማሪው፤ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመስኖ ልማት ሥራ፣ የሰብል ምርታማነትን ለመጨመር፣ ለአፈር ማዳበሪያ የምናወጣው ወጭ (የውጭ ምንዛሬ) እንዲቀንስ፣ ከኬሚካል ነፃ የሆነ ምርት በማምረት የማኅበረሰቡ ጤናን በመጠበቅ ጥሩ ትውልድ እንዲገነባ ይረዳል።

ከቁጥር ሪፓርት በዘለለ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ጥራት እና ዘላቂነት ያለው ሥራ መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የተጠና አሠራርን መከተል፣ አደረጃጀትን ማጠናከር፣ በቂ ገንዘብ መመደብ፣ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ተግባብቶ እና ተማምኖ በዘላቂነት መሥራት፣ በንቅናቄ ማሠራት፣ አርሶ አደሩ ሀብት የሚያገኝበትን አሠራር መዘርጋት፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማሳተፍ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ምክረ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

መረጃ

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዋና ዋና ጥቅሞች ፡-

  • የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ፡፡
  • የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፡፡
  • የውኃ ሀብትን ለመጠበቅ እና ምንጮችን ለማጎልበት፡፡
  • የብዝኃ ሕይወትን (Biodiversity) ለመጠበቅ፡፡
  • ለኢኮኖሚ እድገት፡፡
  • ዘመናዊ እና ባህላዊ መድኃኒቶችን ለመቀመም እና ሌሎች ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡

የመረጃ ምንጭ፦ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP)፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታህሳስ 22 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here