ዳይሴቱሱዛን ብሔራዊ ፓርክ በሰሜናዊ ጃፓን በሆካይዶ ደሴት ነው የሚገኘው::
የፓርኩ ስፋት 2267 ኪሎ ሜትር ስኬዌር ተለክቷል:: ፓርኩ ታህሳስ 4/1934 እ.አ.አ ነው የተቋቋመው:: በ2024 እ.አ.አ የሂዳካ ሳንያኩ ኤሪሞ ቶካቺ ብሔራዊ ፓርክ እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ በስፋቱ የቀዳሚነትን መንበር ተቆናጦ ቆይቷል::
ዳይሴቱሱዛን የሚለው ቃል ትርጉሙ ታላላቅ በረዷማ ተራራዎች ማለት ሲሆን በፓርኩ ቀጣናም ከ2000 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው 16 ቁንጮ ወይም የአቀበት ጫፎች አሉት- ከነዚህም መካከል 2290 ሜትር የተለካው አሳሂዳክ የተሰኘው በከፍታው ቀዳሚነትን ይዟል::
በፓርኩ ቀጣና ከሚገኘው ኢሻካሪ ተራራ ስር ተነስቶ 208 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚፈሰው ኢሻካሪ ወንዝን ከሆካይዶ ግዛት አንደኛ፣ ከጃፓን በሦስተኛ ደረጃነት አስቀምጦታል::
የፓርኩ ከፍተኛ ቦታዎች ወይም ተራራማ ቀጣናዎች ቀዝቃዛ አልፎ ተርፎም በበረዶ የተሸፈኑ ናቸው:: ዝቅተኛ ቦታዎቹ ደግሞ በአበባ የደመቁ በአንፃራዊነት ሞቃታማ አየር ይሰፍንባቸዋል::
በፓርኩ 225 የደጋማ እፅዋት ዝርያዎች መገኘታቸው ተመዝግቧል:: ዝቅተኛ ቦታዎችን ያለበሰው ሳር በሀምሌ ወር የሚያብብ በመሆኑ የቀጣናውን ሳቢ እና ማራኪነት በእጅጉ ያጐላዋል::
በፓርኩ በርካታ የዱር እንስሳት የተጠለሉ ቢሆንም ከሁሉም በላይ በረዷማው ቀጣና የሚመቸው ቡናማ ቀለም ያለው ግዙፉ የድብ ዝርያ በብዛት የሚገኝ መሆኑ ነው በድረ ገፆች የሰፈረው::
የፓርኩ ገፅታ የተመሰረተው በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ሦስት የተራራዎች ስብስብ ነው:: የተራራ ስብስቦቹ አንዱ ከአንዱ በረድፍ የተሰደሩ እና ተዛዝለው የተከመሩ ይመስላሉ- አፈጣጠራቸው::
በፓርኩ ሰሜናዊ ቀጣና ከሚገኙት ረዢሙ የአሳሂ ተራራ ነው:: ሌላኛው በእሳተ ገሞራ የተፈጠረ የተራራ ስብስብ በማእከላዊ ዳጋማ ቀጣና የሚገኘው ነው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቪዚት ሆካይዶ፤ ኢኤንቪ ዶት ኦርግ እና ዊኪፒዲያን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም