ድልድይን ለጥገና

0
154

በፈራረሰ አውራ ጐዳና ላይ ጊዜያዊ ድልድይ በመገጣጠም የተሽከርካሪዎች ፍሰት ሳይገታ በላዩ ላይ በመጓዝ ከስር ጥገና ማካሄድ መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

የስዊዘርላንድ የመንገዶች ጥገና ባለስልጣን 257 ሜትር ርዝመት፣ አምስት ሜትር ስፋት እንዲሁም ሦስት ሜትር ከፍታ ያለው “አስትራ” የተሰኘ ድልድይን አስተዋውቋል:: ድልድዩ የትራፊክ እንቅስቃሴን ሳይገታ ጥገናን ማካሄድ የሚያስችል ነው።

በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2024 መጀመሪያ ላይ የተዋወቀው “አስትራ” የተሰኘው የተሽከርካሪዎች ፍሰትን ሳይገታ የጐዳና ጥገናን አስቻዩ ድልድይ በከፊል አውራ ጐዳና ላይ ነው የሚገጣጠመው::

ድልድዩ በዓይነቱ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት የ “አስትራ” ድልድይ ኘሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ዩርግ ሜሪያን ቀደም ብሎ ተገጣጣሚ ድልድይ ሰርተው መሞከራቸውንም አብራርተዋል::

ቀደም ብሎ በጐዳና ላይ ለሙከራ የተሰራው “አስትራ” ድልድይ በመውጫው  እና መውረጃው ጫፍ ከፍታ ስለነበረው የተሽከርካሪዎችን መጨናነቅ ፈጥሮ ነበር።

አዲሱ “አስትራ” ድልድይ ቀድም ብሎ ከተሰራው የተሻሻለ መሆኑን ያብራሩት ስራ አሰኪያጁ አሽከርካሪዎች 60 ኪሎ ሜትር በሰዓት እንዲከንፉበት ያስችላል።

አዲሱ “አስትራ” ተገጣጣሚ ድልድይ ለአውራ ጐዳናዎች ጥገና ሌሊት ይደረግ የነበረውን ጥድፊያ የሚያስቀር መሆኑም  ተገልጿል።

ድልድዩ ከስር በሥራ ላይ ያሉ ሰራተኞችን ከዝናብ እና ከፀሐይ  ይጠብቃል፤ ከላይም የተሽከርካሪ ፍሰቱን ያሳልጣል።

“አስትራ” ድልድይ በስዊዘርላንድ የባለቤትነት መብት ተመርቶ ስራ ላይ ከዋለ  ገና ጥቂት ጊዜያት ቢቆጠሩም ኖርወይ፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድ በጥምረት ለማምረት ፍላጐታቸውን የገለጹ ሃገራት ናቸው።

 

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here