ድምፀ መረዋው

0
188

በዜግነት እንግሊዛዊ በትውልድ ሕንዳዊ አባቱ እና ከኢትዮጵያዊት እናቱ በአዲስ አበባ ከተማ ራስ መኰንን ድልድይ አካባቢ በ1938 ዓ.ም ተወለደ:: በፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፎቶ ቤት ሞሪስ እልቪስን የከፈቱት የሚስተር ሞዲ ጉስታቭ ልጅ ነው፤ አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ::

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነበር:: በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል ቢጀምርም በወቅቱ በነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ሳቢያ የቅርብ ጓደኛው እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው መገደልን ተከትሎ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቱን አቋርጦ ወጣ:: የድርሰትና የግጥም ዝንባሌ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ማንበብ፣ ሁኔታዎችን በጥልቀት ማስተዋልና መመርመር የጀመረው ከልጅነቱ ጀምሮ ነው።

ትምህርቱን ካቆመ በኋላ በግሉ የትርጉም ሥራዎችን ይሠራ ስለነበር በ1964 ዓ.ም በብስራት ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ለመቀጠር ምክንያት ሆነው። ህይወቱ መስመር ያዘ። በመልካም ፀባይ እና ባህሪዋ የቁንጅና ጣሪያ ከሆነችው መሰረት ኃይሌ /መሳይ/ ጋር ትዳር መሰረተ። ትዳሩም ፀንቶ አራት ወንድ ልጆችን እና ሶስት ሴት ልጆችን አፈራ።

በመካነየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የነበረው እና በዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን በሚረዳው የዘመኑ ታዋቂ የሬዲዮ ጣቢያ ብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ በ1964 ዓ.ም በመቀጠር ጣቢያውን ደርግ እስከ ወረሰበት ጊዜ ድረስ ሠርቷል:: ድኅረ አብዮት በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅና በብሔራዊ ሬዲዮ እስከ 1980ዎቹ መገባደጃ ድረስ በዜና አንባቢነት፣ በፕሮግራም አዘጋጅነት ሠርቷል:: ጡረታ እስከወጣበት 1994 ዓ.ም ድረስ ያገለገለው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የውጭ ቋንቋ ዴስክ ነበር::

ዳሪዮስ ሞዲ ለሬዲዮ የተፈጠረ ምሉዕ በኩልዔ የሆነ ጋዜጠኛ ነበረ። ተሰምቶ የማይጠገብ፣ እያነበበ የሚስረቀረቅ የሬዲዮ ሞገድን የሚገዛ ባለግርማ ድምፅ የታደለው ዳሪዮስ ሞዲ፣ ከዜና ባህሪው ተነስቶ አነባነቡን የሚከተል እንከን አልባም ዜና አንባቢ ነበር።

መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የሚሉት ጎልቶ ይደመጥላቸው ዘንድ የሚዲያው ልሳንና የድምፅ ሞገድ ዳሪዮስ ነበር። እንደየጊዜው የአዳዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ ድምፅ ሆኖም አገልግሏል። እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ሚዲያ ሥራ ውስጥ እንደ ዳሪዮስ አይነት የትርጉም ጌታ አልተገኘም።

ዳሪዮስ ዘንድ በይመስለኛል እና ይሆናል በሚል አቻ ትርጉም አይገኝም። የቀደምት አባቶቹን መዝገብ እየፈተሸ፣ ለዘመናዊው ዓለምም እንዲስማማ የራሱንም የትርጉም መንገድ እየፈለገ የሚማስን የቃላት ዲታ እና ታላቅ ሙያተኛ ነበር።

የራሱን ትርጉም የሕዝብ ቋንቋ ማድረግ የቻለ፣ የቋንቋ ምሁራንም ደግመው ደጋግመው የሚመሰክሩለት የትርጉም መምህር ነበር። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያኒኛ የመተርጎም ብቃት የመነጨው ካልተቋረጠ የንባብ ብቃቱ ነው።

ኤች አይ ቪ (HUMAN IMMUNO DEFICIENCY VIRUS (HIV) የሚለውን ሀረግ ሕዝብ ሊረዳው በሚችለው ቃል በራሱ መንገድ ተርጉሞ “ቅስመ ተፈጥሮ መከላከያ ሰባሪ በሽታ” ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብን ስለ በሽታው ያስተማረውም ይሄው ሙያተኛ ነበር:: ለዚህ ውለታው ግን ሽልማት ወይም ምሥጋና ሊደርሠው ቀርቶ ይብሱን “ያልተገቡ ቃላትን በመጠቀም” በሚል ከደመወዙ 80 ብር ተቀጥቷል። ያለ ተፈጥሯዊ የግንኙነት በጽንሳቸው ልጅ የሚታቀፉ (ማሕጸን የሚያከራዩ ሴቶች) ጉዲፈቻ የሚል ኦሮምኛ ቃል እና ጽንስ የሚለውን የአማርኛ ቃል በማዋሃድ “ጽንሰ-ፈቻ” ብሎ የሰየመውም ዳርዮስ እንደነበር ታሪካዊ መዝገበ ሰብ መጽሐፍ ያትታል።

ዳርዮስ ከቀደሙ የሙያ አባቶቹ አሃዱ ሳቡሬ፣ አሠፋ ይርጉ እና ሌሎች ብዙ ተምሯል። በዚህም ለንደን ሳይሆን ሎንዶን፣ ዋሺንግተን ሳይሆን ዋሽንግቶን ብሎ በመዘገብም ይታወቅ ነበር። ጋዜጠኛው ከሙያ አባቶቹ ያገኘውን ለራሱ ሳያስቀር ለተተኪዎቹ በማስተማር ብንያም ከበደ፣ ነጋሽ መሃመድ፣ ብርቱኳን ሐረገወይን፣ ሳምሶን ማሞ እና ሌሎች ሙያተኞች ምሳሌ ሆኗቸዋል።

የመጨረሻዎቹ ሦስት ዓመታት ለዳሪዮስ ጥሩ አልነበሩም። ለዘመናት ማልዶ ከሥራ ገበታው የማይታጣው ዳሪዮስ ህመም ደጋገመው። እንደ ልብ መተንፈስ ተሳነው። በኦክሲጅን እየተረዳ ቆየ። ዳሪዮስ የልብ ትርታው ቀጥ የምትል የምትመስለው ኦክሲጅን ሲያጣ ብቻ አልነበረም። ካላነበበና ዜና ካልሰማ እስትንፋሱ ያለ አይመስለውም።

ጋዜጠኛ ዳርዮስ ሞዲ ሰኔ 13 ቀን 2007 ዓ.ም በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል:: ሰኔ 14 ቀን ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት  ጉራራ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ተፈጸሟል::

የሙያ ልጁ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ብንያም ከበደ የሕይወት ታሪኩን በአነበበ ጊዜ አንዲህ ብሏል፡- “ጋሽ ዳሪዮስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞች አባትም ነበረ። ይሄ ታሪክ ብቻ ሊሆን ይችላል። ነበር ቅርብ ነው። ነበር እያልን ዳርዮስን ብቻ ሳይሆን ሙያውንም አብረን እንቅበረው…”።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here