ድርድር የተሻለው መውጫ መንገድ ነው

0
202

የአማራ ክልል ሰላም ከራቀው ሰባት ወራትን ተሻግሯል። ይህ ግጭት ታዲያ በሚሊዮን የሚቆሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ አድርጓል። ሌሎች አገልግሎቶችም እንዲቋረጡ አድርጓል። በአጠቃላይ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ማሕበራዊ ችግርን አስከትሏል። ከጉዳዩ ጋር ከሰሚኑ በነበረ ውይይት ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ግጨቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል።

ክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ፈታኝ፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስተማሪ የኾነ ውስብስብ ፈተናዎችን ማስተናገዱን አቶ አረጋ አንስተዋል፡፡ ተፈጥሮ የነበረው ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግር ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማሕበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል። ይህም ከምንም በላይ ለአማራ ሕዝብ ነባር እሴት እና ማንነት የሚመጥን አልነበረም ብለዋል።

በሰሜኑ ጦርነት የአማራ ክልል ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን በጥናት መረጋገጡ ይታወሳል። በዚህ የከፋ ችግር ውስጥ የነበረው ክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት በውይይት መጠናቀቅ ማግስት ወደ ሌላ ግጭት መግባቱ ታዲያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ግጭቱ በውይይት እልባት እንዲያገኝ በርካቶች ጥሪ አቅርበዋል። ዳሩ ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ እስካሁን የተግባር ምላሽ ባይታይም። ይሁን እንጂ ለሰላም ጊዜም መቼም ረፍዶ አያውቅም በሚል የሰላም ጥሪው አሁንም ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ እየተስተጋባ ነው።

ለአብነትም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ (IMF) በተለይ በአማራ ክልል ያለው ግጭት እንደሚያሳስበው አስታውቋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ድርጅት ብድር ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርባለች። ድርጅቱ ታዲያ ጥያቄውን መነሻ አድርጎ፣ በሀገሪቱ የሚታዩት ግጭቶች (ለአብነትም በአማራ ክልል ያለው ግጭት) እንደሚያሳስበው ጠቁሟል። ግጭቱም በውይይት እንዲፈታ ጠይቋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት አሜሪካን አንሚያሳስባት ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ በኩል አስታውቃለች። ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር ለግጭቱን ለማስቀረት አዋጩ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን አሳታውቀዋል። ሁሉም ወገኖች ውይይትን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ኋላቀር የፖለቲካ ባሕል አሁንም እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ገልጸዋል። ይህ የፖለቲካ ባሕል ከሥረ መሠረቱ መቀየር እንዳለበትም አንስተዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን አዲሱ ትርክት ብዝኃነትን እና አብሮነትን መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃኘው በመጠፋፋት መንገድ ነው ያሉት አቶ ብናልፍ፣ ይህም እስካሁን ድረስ እየተንከባለለ የመጣ የፖለቲካ ባሕል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ውይይት ካልዳበረ የቱንም ያህል ግጭትን ማስቆም ቢቻል ነገ ላይ ግጭት እንደማይፈጠር ዋስትና እንደማይሆን አቶ ብናልፍ አስረድተዋል።

በመሆኑም ውይይትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፤ ጎን ለጎንም ብዝኃነትን እና አብሮነትን መሰረት ያደረገ ትርክት ማጎልበት ይገባል ብለዋል። ገዥ ትርክቱም ቀደም ሲል የነበሩ ትርክቶች ያስከተሉትን ጉዳት በአግባቡ የፈተሸ እና ያንን ሊያርም የሚችል መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “የሃይማኖት አባቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ” ነው ያሉት። ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች ጋር መወያየታቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስታወቁት።

የሰላም እና የመልሶ ግንባታን በተመለከተ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው። ለአብነትም በሰሜን ጎንደር ዞን በአዲአርቃይ ወረዳ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ መገንባትን እንዲሁም ሰላምን ማስጠበቅን ያለመ ውይይት ከሰሞኑ ተካሂዶ ነበር። በውይይቱ የተገኙት የሶማሊ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹእ አቡነ መቃሪዮስ እርስ በእርስ መገዳደል እንዲቆም እና ማኅበረሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here