ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ልጆች የክረምቱን የእረፍት ጊዜ እያሳለፋችሁባቸው ካሉት የጨዋታ አይነቶች በተለይም ስለ ድብብቆሽ ጠቀሜታ እንንገራችሁ፡፡
ጨዋታ በልጆች ሕይወት ውስጥ ብዙ ፍላጎቶችን ያሟላል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ብንመለከት የመነሳሳትና የትኩረት፣ ተፈጥሯዊ የመናገር ነፃነት፣ ለውጥን የማወቅና የመከተል፣ መሻትን የማርካት ፍላጎት፣ እንዲሁም ከባድና አደጋ የሌላቸውን ነገሮችን በመሞከር ፍላጎታቸሁን ያሟላል፡፡
ድብብቆሽ ጨዋታ ቢያንስ ሁለት ተጫዋቾች የሚኖሩበት በአንድ በተወሰነ አካባቢ አንድ ሰው ሲቆጥር ሌሎች ራሳቸውን የሚደብቁበት የጨዋታ አይነት ነው፡፡ ጨዋታውን ከሚጫወቱት ውስጥ የተመረጠው ተጫዋች ዐይኖቹን ጨፍኖ ሌሎች ተጫዋቾች እስኪደበቁ ድረስ ይቆጥራል፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች የተስማሙበት የቁጥር ገደብ ላይ ሲደርስ አይኑን ይገልጣል፡፡ በየቦታው የተደበቁ ልጆችንም ለማግኘት ይሞክራል፡፡
ድብብቆሽ ጨዋታ ለልጆች የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
የልጆችን የሥራ ተነሳሽነትን ያዳብራሉ፡፡ የራሳቸውን ግብ ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ለመደበቅ በጣም ጥሩውን ቦታ ይመርጣሉ፡፡ መወሰንንም ይማራሉ፡፡
የራሳቸውን እቅድ ማውጣት እና ቅድሚያ በመስጠት ማስፈጸምን ይለማመዳሉ፡፡ ልጆች ድብብቆሽን በሚጫወቱ ጊዜ ራሳቸውን በሌላ ሰው ቦታ ማስቀመጥ እና የሌሎችን ስሜት መረዳት እንዲችሉ ያስተምራል፡፡ የተለያዩ እይታዎችንም ይገነዘባሉ፡፡ ከተለያዩ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች ጋርም ይተዋወቃሉ፡፡ ስሜትን መቆጣጠር ያዳብራሉ፡፡ ስሜታዊ ብልህነትን ማሳደግን ይማራሉ፡፡ ልጆች በድብብቆሽ ጨዋታ ድፍረትንም ይማራሉ፡፡ ልጆች የሚደበቁበትን ቦታ ሲመርጡ ነጻነትንም እየተለማመዱ ነው፡፡ በጋራ ጨዋታ በቅንጅት መሥራትን ይማራሉ፤ እንዲሁም የጨዋታውን ሕግ በማክበር ሚዛናዊነትን እና እውነትን ይቀስማሉ፡፡
ምንጭ፡- EPL.Ca
ተረት
የሾላ ፍሬዋ
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ ማሳውን ሲያርስ ውሎ ከአንድ ዋርካ ዛፍ ሥር ሊያርፍ ቁጭ አለ፡፡ በዋርካው ሥርም ቁጭ ብሎ ምሳውን እየተመገበ እያለ ቀና ሲል ትንንሽ የሾላ ፍሬዎችን ዋርካው ላይ ተንጠልጥለው አየ፡፡
ትንሽ ቆይቶ ወደ ጎን ዞር ሲል አንድ የዱባ ሀረግ ተመለከተ፡፡ ከትንሹ ሀረግ ጎን ትልልቅ ዱባዎች መሬት ላይ ወድቀው አየ፡፡ ትልቁ የዋርካ ዛፍ ትንሽ የሾላ ፍሬ፣ ትንሹ የዱባ ሀረግ ትልቅ ዱባ መያዙ አስገረመው፡፡ ልክ ያልሆነ ነገር እንደሆነ እያሰበም ምሳውን በልቶ ጨረሰ፡፡
ወዲያውም ድካም ስለጠናበት ዋርካው ሥር እንቅልፍ አሸለበው፡፡ ጥልቅ እንቅልፍ ወስዶት እያለ አንድ የሾላ ፍሬ ከዛፉ ወድቃ ግንባሩን መታችው፡፡ ገበሬውም ግንባሩን በጣም አሞት ከእንቅልፉ ተነሳ፡፡ ሲያስተውል የሾላ ፍሬ ወድቃ ግንባሩን እንደመታችው አወቀ፡፡ ከዛፉ ላይ ቢሆንና ቢወድቅበት ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል እያሰበ “ይቅር በለኝ ጌታየ፤ በረቂቁ ሥራህ ጣልቃ ገብቻለሁና” አለ ይባላል፡፡ ተፈጥሮ ሁሉን ነገር አስተካክላ መሥራቷን እና በተፈጥሮ ሥራ ጣልቃ መግባት እንደሌለብን ከተረቱ እንማራለን፡፡
ምንጭ፡- የሕዝብ ተረት
ሞክሩ
- ከዓለም በቆዳ ስፋት ሁለተኛው አህጉር ማን ይባላል?
- ረጅም እድሜ ያስቆጠረችው ቅድመ ሰው ማን ትባላለች?
- ውሻ የቤት እንስሳ ነው። ለምንድን ነው?
መልስ
- አፍሪካ
- ሉሲ
- “ለ” ፊደልነው፡፡
ነገር በምሳሌ
- ለሆዴ ጠግቤ ለልብሴ አንግቤ፤- ሁሉ ሞልቶ ሁሉ ተርፎ፡፡
- ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ፡- አጉል ቃል መግባት አያስፈልግም (መዋሸት አይጠቅምም)፡፡
- አስር ያባረረ አንድም አይዝም፡- ሁሉን የተመኘ ባዶ እጁን ይቀራል፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም