ድንበር ተሻጋሪዉ ጦርነት

0
162

ሂዝቦላ በሊባኖስ እና በእስራኤል ወሰን ውስጥ  የተነሳው ግጭት የሚቆምበት ብቸኛው መፍትሄ በጋዛ ያለው ጦርነት ሲቆም ብቻ እንደሆነ ገልጿል።

“በጋዛ ተኩስ አቁም ከተደረገ፣ ያለምንም ድርድር እኛም እናቆማለን፣” ያሉት የሂዝቦላ ምክትል አዛዥ ነይም ቃሲም ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል።

በእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ውስጥ የሂዝቤላ ተሳትፎ አጋሩን ሀማስን ለማገዝ ያለመ መሆኑን ቃሲም በማስረዳት፣ “ጦርነት ከቆመ፣ ወታደራዊ ድጋፋችንም ይቆማል” በማለት ለአሶሼትድ ፕሬስ ገልፀዋል።

ነገር ግን እስራኤል ወታደራዊ እርማጃዎቿን ያለምንም መደበኛ የሆነ የተኩስ ማቆም ስምምነት እና ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ጦሯን ሳታወጣ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማቆም እርምጃ ብትወስድ፣ ለሊባኖስ እስራኤል ድንበር ግጭት እንድምታው ግልፅ አይደለም።

ከሃማስ ጋር በተፈጠረው ግጭት እስራኤል ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ በጋዛ እየወሰደች ባለው እርምጃ አያሌ ኢሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት መስተናገዱን ቀጥሏል። በቅርቡም በአሜሪካ አቅራቢነት ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የቀረበው የተኩስ አቁም የመፍትሄ ሰነድ ፀድቆ ሁለቱም ወገኖች በሦስተኛ ወገን ድርድር ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ነገር ግን እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደችው ያለው ወታደራዊ እርምጃ በተለያዩ ወገኖች ውግዘት እያስተናገደ ቀጥሏል። ከሁሉ የባሰው ግን የግጭቱ አድማስ ቀጠናዊ መልክ እየያዘ መምጣቱ እና በሊባኖስ ድንበር ሂዝቦላ እያደረገው ያለው ወታደራዊ ጥቃት ዓለምን አሳስቧል።

ሂዝቦላ መሰረቱን በሊባኖስ ላይ ያደረገ ታጣቂ ሚሊሻ እና የፖለቲካ ፓርቲ ነው። በ1974 ዓ.ም በአስራ አምስት ዓመታቱ የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነቱ መካከል የተወለደው ሂዝቦላ “የአምላክ ፓርቲ” የሚል ትርጓሜ አለው። የድርጅቱ ዋና ዓላማ የምእራባውያን ኃይሎችን ከመካከለኛው ምስራቅ ማስወገድ እና የእስራኤልን የመኖር መብት መቃወም ነው።

ሂዝቦላ የተቋቋመው በ1974 ዓ.ም እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ባሉ ፍልስጤማውያን ለደረሰባት ጥቃት የበቀል ምላሽ የሆነ ጦርነት መውሰዷን ተከትሎ ሌባኖስን ከእስራኤል ነፃ ለማውጣት ሲሆን እስከዛሬ ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡

የሂዝቦላ ወታደራዊ ኃይል የሊባኖሱ የርስ በርስ ጦርነት ከተጠናቀቀበት ከ1982 ዓ.ም በኋላ መጠናከሩን ቀጥሏል። ቡድኑ ሊባኖስን ከእስራኤል ነፃ በማውጣት ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ቀጠለ፤ እና በደቡብ ሊባኖስ በወረረው የእስራኤል ኃይል ላይ የሽምቅ ውጊያ ለዓመታት በማካሄድ እስራኤል በ1992 ዓም ከሊባኖስ እስከወጣችበት ድረስ የሽምቅ ውጊያ አካሂዷል። ከዚያም ሂዝቦላ አወዛጋቢውን የሸቀጥ እርሻ የድንበር ስፍራ ለሊባኖስ በማስመለስ ጥረት ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጓል።

በ1998 ዓ.ም ላይ ሂዝቦላ ለአምስት ሳምንታት ያህል ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረ ሲሆን ይህም ፍልስጤምን ነፃ ለማውጣት ያለመ ሳይሆን ነጥብ የማስመዝገብ ጥረት እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ይጠቁማሉ።

 

የሂዝቦላ አቅም የበለጠ ማደጉ የታየው በ2007 ዓ.ም በሶርያውያን የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ወታደራዊ ኃይሉ ለሶሪያው ፕሬዚደንት በሽር አላሳድ ድጋፍ በሰጠበት ወቅት ነበር። በ2013 ዓ.ም ላይ ደግሞ የሂዝቦላው መሪ ሀሰን ነስራላህ ቡድኑ 100,000 ተዋጊዎች እንዳሉት ተናገሩ። ኢላማ በማይስቱ ሮኬቶች እና ድሮኖች የተደራጀ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንዳለውም አስጠነቀቀ።

ሂዝቦላህ በሊባኖስ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተጨማሪነት የሚያገለግል እና ከፍተኛ ተፅዕኖ የያዘ፣ ሁልጊዜ “በመንግሥት ላይ ሌላ መንግሥት” እየተባለ የሚገለፅ፣ ወሳኝ የሚባል ተሰሚነት ያገኘ ድርጅት ነው። በ1984 ዓ.ም ስምንት አባሎቹ ለሊባኖስ ፓርላማውን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው የነበረበት፣ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም ሂዝቦላ መር ጥምር መንግሥት መስርቶ እንደነበር ታሪኩ ያሳያል።

ሂዝቦላህ በ2012 ዓ.ም ምርጫ 13 መቀመጫዎችን አግኝቷል። ነገር ግን ጥምረቱ አብላጫ መቀመጫውን አጥቶ እና ሀገሪቱም በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅም የሚንቀሳቀስ መንግስት የላትም። ሌሎች የሌባኖስ ፓርቲዎችን መንግሥቱ እንዲሽመደመድ እና በማንኳሰስ እና ለሊባኖስ ለቀጠለው አለመረጋጋት አስተዋጽኦ በማበርከት ሂዝቦላን ይኮንኑታል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሂዝቦላ በኢራን ከፍተኛ እገዛ የሚደረግለት በሊባኖስ ማእከሉን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለ ከሀማስ ይልቅ ለእስራኤል ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።

በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ በዋናነት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው። ይሁን እንጅ፣ ሂዝቦላህ ለእስራኤል ሌላ ስጋት ሆኖ ተደቅኗል። ሀማስን ለመደገፍ በሚል ሽፋን በሊባኖስ አዲስ የግጭት ግንባር ከፍቶ የሮኬት፣ የሚሳይሎች እና የድሮን ጥቃት በእስራኤል ላይ እየሰነዘረ ይገኛል። በአነስተኛ የጦርነት ግጭት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሂዝቦላ የኢራንን ድጋፍ ካገኘ ወደ ሙሉ ጦርነት እንደሚገባ እና ይህም ሁኔታውን ወደ ቀጠናዊ ጦርነት እንደሚቀይረው አስግቷል።

 

የሂዝቦላው ምክትል አዛዥ ካሲም ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ እንደገለፁት እስራኤል አሁን ባለው ሁኔታ ሙሉ ጦርነት በሂዚቦላ ላይ የመክፈት  እቅም አላት ብለው አያምኑም። እስራኤል ሙሉ ጦርነት ባይሆንም እንኳ በሊባኖስ ላይ የተመጠነ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ለማድረግ ብትወስን፣ ጦርነቱ የተገደበ ሆኖ እንደሚቀር መጠበቅ እንደሌለባት  ምክትል አዛዡ አስጠንቅቀዋል።

“እስራኤል የፈለገችውን መወሰን ትችላለች፣ የተገደበ ጦርነት፣ ሙሉ ጦርነት፣ ከፊል ጦርነት፣ የወደደችውን መወሰን ትችላለች” ያሉት ቃሲም “ነገር ግን ምላሻችን እና ትግላችን እስራኤል በምታወጣው የፍልሚያ እቅድ መሰረት እንደማይከናወን መጠበቅ አለባት፤ እስራኤል ጦርነት ብትከፍት ጦርነቱን ወይም ማን እንደሚሳተፍበት የምትቆጣጠረውና አይሆንም” ብለዋል።

እንደ አጃንስ ፍራንስ ዘገባ በአሁኑ ወቅት ሃማስን በማገዝ በሚል ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ሂዝቦላ በሊባኖስ ያለውን ድንበር የጦርነት ቀጠና አድርጎታል፡፡

በአነስተኛ ደረጃ እየተከናወነ ያለው የሒዝቦላ እና  እስራኤል ጦርነት እተካሔደ ባለበት ከሂዝቦላ ጋር ቅርበት ያለው ምንጭን ጠቅሶ ፍራንስ 24 ሃወር እንደዘገበው እስራኤል የሂዝቦላን አንድ ከፍተኛ አመራር መገደሉን በይፋ ገልጿል፡፡ ይህን ተከትሎ ሂዝቦላ ወደ እስራአል 100 ሚሳየሎችን መተኮሱን አስታውቋል፡፡

ሃማስ በጋዛ ጦርነት እንዲያበቃ እንጂ የተኩስ ማቆም ፋታ እንደማይፈልግ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ይህ የተሰማው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያም ኔታንያሁ ሃማስን የማጥፋት አላማቸውን አውን እስካላደረጉ ድረስ እንደዚህ አይነት ስምምነት እንደማይፈጽሙ እየተናገሩ ባለበት ወቅት ነው፡፡

ሂዝቦላ በምክትል አዛዡ ለአሶሴትድ ፕሬስ እንዳስታወቀው እስራኤል የወደደችውን መወሰን እንደምትችል እና በሂዝቦላ ላይ ያወጀውን ጦርነት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ እስራኤል ጦርነት የምትከፍት ከሆነ የጦርነቱን መዘዝ መቆጣጠር እንደማትችል እና ማን ወደ ጦርነቱ እንደሚቀላቀል አንደማታውቅ አሳስበዋል፡

ከዚህ ባለፈ ጦርነቱ ከሊባኖስ ወደ የመን ተሻግሮ የየመኑ አማጺ በእስራኤል በተመረጡ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ይፋ ያደረገበትን መረጃ ፍራንስ 24 ሃወር ዘገግቧል፡፡

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here