ድንግሏ ደሴት

0
20

ከሰባት ሺህ 600 በላይ ደሴቶች ድምር ውጤት የሆነች፣ በሰላማዊ ውቅያኖስ ውስጥ በውቂያኖስ ውኃ ዙሪያዋን ተከባ የምትገኝ ከደቡብ ምስራቅ እስያ ክልል ሀገራት አንዷ ናት። በተፈጥሮ ውበቷ፣ በውኃ ሀብቷ፣ በባሕላዊ ብዝኃነቷ እና በታሪካዊ ቅርሶቿ ትታወቃለች። በፀአዳ የባሕር ዳርቻዎቿ፣ በአረንጓዴ ጫካዎቿ፣ በሰማይ ጠቀስ ተራሮቿ እና በበርካታ ደሴቶች የተዋበች ድንቅ ሀገር መሆኗ ከሌሎች ሀገሮች ልዩ ያደርጋታል – ፊሊፒንስ።

የፊሊፒንስ ኢኮኖሚ በቱሪዝም፣ በዓሣ ሀብት እና በባሕላዊ እሴቶች የተመሠረተ ነው። በተፈጥሮ ጥበቃ እና በዘላቂ ልማት ዙሪያ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉባት መሆኗ እንዳለ ሆኖ  ይህቺ ውብ ሀገር በአጭሩ ተፈጥሮና የሰው ልጅ ሕይወት የሚጣመሩበት ልዩ አካባቢ ተደርጋ ትቆጠራለች። የሺዎች ደሴቶች መናኸሪያ፣ በእልፍ ደሴቶች፣ በተፈጥሮ ውበት እና በስነ ምሕዳር ዕሴት እንዲሁም የዓለም እንቁ ደሴት እየተባለች የምትሞካሸውን ፓላዋን ደሴትን በኩር በሽርሽር አምዷ እንካችሁ ብላለች።

ፓላዋን በፊሊፒንስ ምዕራብ ክፍል፣ በደቡብ ቻይና ባሕር እና በሱሉ ባሕር መካከል ትገኛለች። ደሴቷ ረጅም የባሕር ዳርቻ፣ ከፍተኛ ተራሮች፣ አረንጓዴ ዱር እና የተወለወለ መስታዎት ውስጡ የሚንቀሳቀሱ የሚመስሉ የውኃ እንስሳትን የሚያሳይ ንጹሕ የባሕር ውኃ ባለቤት የሆነች አማላይ ደሴት ናት።

የደሴቷ የተፈጥሮ ውበት እስካሁን በውል ወይም በደንብ ተጠብቆ የሚገኝ አስገራሚ ስፍራ መሆኑን ለማሳየት “የፊሊፒንስ መጨረሻ ድንግል ደሴት” ብለው ይጠሯታል። በዚህ አካባቢ የሚገኙ ረዣዥም ቋጥኞች፣ የባሕር እና የዱር እንስሳት ብዛት ከፍተኛ ሲሆን ብዙዎቹ ዝርያዎች በፓላዋን ብቻ የሚገኙ ናቸው።

ፓላዋንን ስናስብ በመጀመሪያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ጥርት ያለው ባሕር እና በነጭ አሸዋ የተዋቡ የባሕር ዳርቻዎች ናቸው። በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁት የደሴቷ የባሕር ዳርቻዎች የተለያዩ የዓለት ቋጥኞችን ይይዛል፣ እነርሱም በሺዎች ለሚቆጠሩ የባሕር እንስሳት መኖሪያ ሆነዋል። ኤል ኒዶ እና ኮሮን የተባሉ አካባቢዎች በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ ዝና አግኝተዋል።

የፓላዋን የተፈጥሮ ውበት በባሕር ብቻ አይገደብም። ከባሕር ውስጥ የሚነሱ  ተራሮች፣ ጥልቅ ሐይቆችና አረንጓዴ ጫካዎች የደሴቷን ገፅታ ዕፁብ ድንቅ ያድርጉታል። በኮሮን ያለው ካያንጋን ሐይቅ ከዓለም በጣም ንጹሕ ሐይቆች አንዱ ሲሆን ይህም የፓላዋን ተፈጥሮ ምን ያህል ያልተበከለ እንደሆነ ያሳያል።

በደሴቷ መዲና ፖርቶ ፕሪንሰሳ የሚገኘው የመሬት ስር ወንዝ ደግሞ ሌላው የፓላዋን ተፈጥሮ አስደማሚው ገፅ ነው። በመሬት ስር በኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ርቀት የሚፈሰው ይህ ወንዝ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ ተመዝግቦ መገኘቱ የቦታውን ዓለም አቀፍ ዕሴትነት ያሳያል።

የፓላዋን ስነ ምሕዳራዊ ብዝኃነት ከብዙ ደሴቶች የሚበልጥ ነው። በዚህ ክልል የሚገኙ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ብዙዎቹ በፓላዋን ብቻ የሚገኙ ናቸው። ይህ ደሴቷን ከሥነ ምሕዳር አንጻር እጅግ ዋጋ ያላት ያደርጋታል።

የፓላዋን ልዩ መሬት አቀማመጥ የደሴቷ ሌላው የውበት ማዕከል ነው።

ከባሕር ውስጥ የሚነሱ ድንጋያማ ተራሮች፣ ጥልቅ ሐይቆችና የመሬት ስር ወንዞች በሌሎች ደሴቶች ላይ በአንድ ስፍራ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው። በፓላዋን ደሴት ግን እነዚህ ሁሉ በአንድ ተጣምረው ይገኛሉ፤ በተለይ የፖርቶ ፕሪንሰሳ የመሬት ስር ወንዝ የፓላዋንን ብርቅዬነት የሚያረጋግጥ ዓለም አቀፍ ምልክት ነው።

ፓላዋን የቱሪዝም ልምዷ ከሌሎች ደሴቶች ይለያል። በብዛት በኢኮ – ቱሪዝም ላይ ያተኮረ ነው። ይህም ጎብኚዎች ተፈጥሮን ሳይጎዱ እንዲጎበኙ የሚያስችል ሥርዓት ነው።

የፓላዋን ሕዝብ  ባህልና ሕይወት ልዩ ነው። ባሕላዊ ማሕበረሰቦች ከተፈጥሮ ጋር ተስማሚ ሕይወት በመኖር ደሴቷን እስከዛሬ ለመጠበቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ምንም እንኳን ፓላዋን በተፈጥሮ ሀብቷ የበለፀገች ብትሆንም ቅሉ የደኖች መጨፍጨፍ እና የአካባቢ ብክለት እንደ ዋና ተግዳሮት ይነሳሉ። ችግሮቹን ለመፍታት ደግሞ መንግሥት፣ የአካባቢው ማሕበረሰቦች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመተባበር የተፈጥሮ ሀብቱን ለመጠበቅ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ ፓላዋን የአንድ ሀገር ብቻ ሀብት ሳትሆን፣ የሰው ልጆች የጋራ የተፈጥሮ ቅርስ ናት። ይህን ውበት መጠበቅ ማለት ለመጪው ትውልድ ተፈጥሮን ከእነ ውበቱና ከእነ ወዙ ማስረከብ ማለት ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፣ ናሽናል ጅኦግራፊን፣ ትራቭል ፓላዋን እና ቪዚት ፊሊፒንስ የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።

አጫር እዉነታ

 

ስለ ፊሊፒንስ አጫጭር እውነታዎች

 

ከሰባት ሺህ 600 በላይ አሏት (ሉዞን፣ ቪሳያስ፣ ሚንዳናኦ ዋናዎቹ ናቸው)፣

ዋና ከተማ፡- ማኒላ

የሕዝብ ብዛት፡- 115 ሚሊዮን

ቋንቋዎች፡- ፊሊፒኖ (ታጋሎግ) እና እንግሊዝኛ

ሃይማኖት፡- ብዙዎቹ ካቶሊክ

ባሕል፡- የስፔንና የአሜሪካ ከአህጉራዊ ባሕሎች ጋር የተቀላቀለ

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here