ድካም አቅላዩ ፈጠራ

0
123

“ከምወደው የሕይወት ትምህርት ጥቅሶች አንዱ ‘ሥራህን የመወጣት መብት አለህ፣ ነገር ግን ለድርጊትህ (ለሥራህ  ውጤት) ፍሬ የማግኘት  መብት  ግን የለህም’ የሚለውን ነው፡፡ ጥቅሱ በተለይ  በሥራ ፈጠራ ጉዞዬ ሁሉ ጠቃሚ ነበር::”  በማለት አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዳበቃው የተናገረው ወጣቱ ራግሃቭ ጉፕታ ነው።

ራግሃቭ ጉፕታ  እ.አ.አ በሕንድ  ኒውደልሂ ግዛት ጥር 03 ቀን 1999 ነው የተወለደው፡፡

ወጣቱ ከህንድ ሥራ ፈጣሪ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችመካከል አንዱ ነው። በንግድ ሥራ ከተሰማሩት ቤተሰብ የተገኘው ራግሃቭ እሱ እና ወንድሙ ተምረው ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ በአካባቢው የተሻለ በሚባል  ትምህርት ቤት እንደተማሩ ያስታውሳል፡፡

የወላጆቻቸው እገዛ በዚህ ብቻ ሳይገደብ  ወደ ግል ቤተ መጻሕፍት  በመሄድ  ለእርሱ እና ለወንድሙ ለትምህርታቸው አጋዥ  እና በተጓዳኝ ዕውቀት ይጨምሩላቸዋል  የሚሏቸውን መጻሕፍት ይገዙላቸው እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የንባብ ልምድ የራግሃቭን የማወቅ  እና የመማር ፍላጎት የበለጠ አሳደገለት፡፡

በቀለም ትምህርቱ እና በስፖርት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ቻለ፡፡ ይህም ራግሃቭ ሙሉ ጊዜውን በትምህርት ቤቱ እንዲያሳልፍ እና ከትምህርቱ ውጪ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሞክር በቂ ጊዜ እንዲያገኝ አስቻለው። ይህ ጥረቱም ራግሃቭ ጉፕታ  ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ በበይነ መረብ በግብይት  ሥርዓት መሳተፍ የሚያስችለውን መረጃ መሰብሰብ ጀመረ፡፡

ይህ ጥረቱ ኮሌጅ ሲገባም ቀጥሎ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ ዕድል ፈጠረለት። ራግሃቭ ከካርኔጊ ሜሎን ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ እና የድህረ ምረቃ ዲግሪዎችን እንዲሁም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ (MBA) አግኝቷል።

ለቤተሰቡ  ምስጋና ይግባውና የእነራግሃቭ ቤተሰብ እራት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ሲመገቡ  የማያቋርጥ የውይይት ርዕስ ስለሆነው የምግብ አሠራር   እንዲሁም አቀራረብ ያገኘው ግንዛቤ   ለፈጠራ ሥራው በር ከፈተለት፡፡  በተለይም በሕይወቱ ሴቶች  ምግብ አዘጋጅተዉ ለማቅረብ ድካማቸውን በመመልከት ስላደገ ለሥራው ትኩረት እንዲሰጠው  አድርጎታል፡፡

“ምግብ አዘጋጅቶ  መመገብ  የሰው ልጅ የዕለት ከዕለት ኑሮ ዋነኛ ተግባር ነው፤ ዝግጅቱ ደግሞ በተለይ ለሴቶች አድካሚ፣ ብዙ ጊዜ የሚወስድ እና ምስጋና የለሽ ሥራ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ይህን መሰረት ያደረገ ጊዜን እና ጉልበታቸውን ሳያባክኑ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ምግቦች የአካባቢያቸውን አሠራር እና ወግ ሳይለቁ በቀላሉ ወደ ሥራ የሚቀየርበትን  መንገድ ለመፍጠር አሰብኩ” በማለት ወጣቱ ቀላል እና ቀልጣፋ የምግብ መሥሪያ (ኒምብል) ይፋ አደረገ፡፡ በዚህም የህንድ መንደሮችን በንፋስ  ኀይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከማድረግ ጀምሮ ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥቡ  ሮቦቶችን ለመሥራት አሰበ፡፡

ሀሳቡንም ዕውን አደረገ፤ ባደረገው ጉዞም ለፈጠራ እና ለአዎንታዊ ለውጥ ያላሰለሰ ቁርጠኝነቱን አሳይቶበታል፡፡

“የምንሠራው የፈጠራ ሥራ ቀጣይ ለሚያመጡት ውጤት እርግጠኛ አለመሆን በቀላሉ ወደ ጥርጣሬ ወይም ተስፋ ወደመቁረጥ የሚያመሩባቸው ጊዜያት  ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ሆኖም እኔ የተነሳሁበትን  ጥቅስ ሳስብ ስለ ውጤቶቹ ከመጨነቅ ይልቅ መቆጣጠር በምችለው ነገር ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል፡፡ ለዚህ ነው ጥረቶቼ በሙሉ ድርጊቶች ላይ አተኩረው ለውጤት የበቃሁት” ይላል፡፡

ወደ ፊት ያለው መንገድ ፈታኝ በሚመስለው ጊዜም ቢሆን በቆመበት መሰረት ላይ በመመሥረት እና በቁርጠኝነት ለመቆየት የሚረዳው መመሪያ ይሄው እንደነበር ባለታሪካችን ያነሳል ። ከውጤቱ ይልቅ በሂደቱ ላይ በማተኮር ምግብ ለማዘጋጀት በተለይ ሴቶች ያባክኑት የነበረውን ጉልበት የሚተካ ሮቦት  ለመሥራት ያሳለፈውን ውጣ ውረድ በዓላማ እና በጥንካሬ ስሜት ማስኬድ እንደቻለ ራግሃቭ ያስታውሳል።

ራግሃቭ ለብዙ ሥራ ፈጣሪዎች ትክክለኛውን  መንገድ በማስገንዘብ  በንግድ ሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት እና ለፈጠራ ሀሳባቸው ዕውን መሆን በገንዘብ መደገፍም ይወዳል።

በኢንስታግራም፣ ለፌስቡክ እና  ለጎግል ማስታወቂያዎች፣ ለማህበራዊ ሚዲያ አስተዳደርእና ለመዝናኛ ኢንዱስትሪዎች…በርካታ የዲጂታል ግብይት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ቀኑን ሙሉ የድረ-ገጽ ዲዛይን  የፍለጋ መንገድ ማሻሻልን ጨምሮ ሌሎች ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ይሠራል፡፡

የራግሃቭ መነሻ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የቴክኖሎጂ ጅምሮችን በህንድ መገንባት ነበር። ዋና ትኩረቱ በኢንተርፕራይዝ ቴክኖሎጂ እና ጥልቅ ቴክኖሎጅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ነው።

ራግሃቭ በህንድ ኢንቨስትመንት፣ በብሔራዊ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የኤሌክትሮኒክስ ኢንቨስትመንቶች እና ፖሊሲ ኃላፊም ሆኖ አገልግሏል። በሥራ ቆይታውም ለሀገራዊ የኢንቨስትመንት  ዘርፍ እድገት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

በህንድ ኢንቨስትመንት ላይ የቦርድ አማካሪ ሆኖ በማገልገል በፕሉማጅ (Plumage)፣ የህንድ ብቸኛ ማሳያ ኦዲኤም (ODM) የመስራች ቡድን አባልም ነበር።

በ”Qualcomm”ላይ በ”Snapdragon Datacenter Platform” ላይ የሃርድዌር መሐንዲስ ሆኖም ሠርቷል።

በህንድ ካሉ በርካታ ድርጅቶች ጋር በበጎ ፈቃደኝነት የታገዘ ለማህበራዊ ተፅእኖ ባለው ፍቅር ይመራቸዋል።  ከሥራ ውጭ ግጥም ማንበብ እና በሂንዱስታኒ በመሣሪያ የተቀነባበረ /ክላሲካል/ ሙዚቃ ማድመጥ  እንዲሁም የእግር ጉዞ እና የታሪክ መጽሐፍት ማንበብ  ያስደስተዋል።

ራግሃቭ ለሌሎች ሥራ ፈጣሪዎች የሚመክረው “የመጀመሪያው ነገር ለራስ የስነ-ልቦና እንክብካቤ ማድረግን ነው፡፡ ራስን መንከባከብ እና እይታን ማግኘት መቻል ቁልፍ ነገር ነው። አንዳንድ ሥራ ፈጣሪዎች የማይቀሩ ውጣ ውረዶችን ለመቋቋም የሚያስችል መሣሪያ የላቸውም፤ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ እይታ ከተለካ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ትግል አለው፡፡ ለእንደዚህ አይነት ቲያትር አትውደቁ፣ ጠቃሚ ምክር ከሥራ ቦታ ውጭ የሆኑ ጥቂት አማካሪዎችን ወይም ሌሎችን  ማፍራት አለባችሁ” በማለት ይመክራል።

ሚየም ዶት ኮም (medium.com)እና ኢንዲያን ኤክስኘረስ (indian express) የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው፡፡::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here