ምጣኔ ሀብቷንም ሆነ የምግብ ፍጆታዋን በግብርናው ዘርፍ የመሠረተችው ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ድጎማ ከማድረግ ጀምሮ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት በሀገር ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እንደሚገነባም በይፋ ማብሰሩ ነው፡፡
የሰብል ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ፣ በፍጥነት ማሰራጨት እና መጠቀም ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በመሆኑም ዘርፉን ማዘመን፣ በአግባቡ መምራት እና መሠረታዊ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከዚህ መካከልም ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አንዱ ነው።
ባለፉት ዓመታት በየጊዜው ከሚነሱ የአርሶ አደሮች ቅሬታ መካከል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በዋናነት የሚጠቀስ ነው። በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ወቅቶች ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና መጓተት ጋር ተያይዞ ለአሚኮ (ለበኩር ጋዜጣ) ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የአቅርቦት መጠኑ እየተሻሻለ ቢመጣም የዋጋዉ ጉዳይ ግን ዛሬም ድረስ ቅሬታን ሲያስነሳ ይስተዋላል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አየለ ዓለሙ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት እና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በግብርና ሥራ መሆኑን በስልክ ነግረውናል። በ2017/18 የምርት ዘመን በአራት ሔክታር መሬታቸው የተለያዩ ሰብሎችን ዘርተው እየተንከባከቡ ነው። አሁን ላይ በቆሎ፣ በርበሬ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ በዋናነት የዘሯቸው ሰብሎች ናቸው፡፡ የእርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ያለው የሰብል ቡቃያ በእጅጉ ያማረ መሆኑን ነው ለበኩር ጋዜጣ የተናገሩት፡፡
አርሶ አደር አየለ እንደተናገሩት በግብርና ሥራቸው ላይ ዋናው ፈተና የሆነባቸው የአፈር ማዳበሪያ በበቂ፣ በወቅቱ እና በተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘታቸው መሆኑን አስረድተዋል። በየዓመቱ ቢያንስ እስከ 30 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል። አርሶ አደሩ እንደገለፁት የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ቢመጣም በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ እንዳለበት አመላክተዋል። በተለይም በዚህ ዓመት የታየው የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ጭማሪ የግብርና ሥራቸውን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን አባክኗል። ለከፍተኛ ወጪም መዳረጋቸውን አስረድተዋል።
እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሬቱ የአፈር ማዳበሪያ ሳይጨመርበት ማብቀል ባለመቻሉ የአፈር ማዳበሪያ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዘር ወቅት በቂ የአፈር ማዳበሪያ ካልተደረገበት ከፍተኛ የምርት መቀነስን ያስከትላል። በቅርቡ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው በሀገር ውስጥ ገንብቶ ለማምረት መታቀዱ ይፋ ሲሆን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። ይህም የአርሶ አደሩን የረጅም ጊዜ ችግር ይፈታል የሚል ተስፋ አሳድሮባቸዋል፡፡ አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ፣ በፍጥነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ካገኘ በቂ ምርት ያመርታል፤ ቤተሰቡንም በበቂ ሁኔታ ይመግባል፤ ለገበያም ያቀርባል።
ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ሳንኪት ልደታ ቀበሌ ነዋሪው ቄስ ዜናው ወርቁ ናቸው። በ2017/18 የምርት ዘመን በሁለት ሔክታር ተኩል መሬት ላይ ስንዴ፣ ጤፍ እና ገብስ ዘርተዋል። ቤተሰብን በአግባቡ ለማስተዳደር በቂ ምርት ማምረት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ በቂ ግብዓት ማቅረብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ባለፉት ዓመታት ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በሚፈልጉት መጠን እና ዋጋ ባለማግኘታቸው በግብርና ሥራቸው ላይ ጫና አሳድሮባቸው እንደነበር ሐሳባቸውን አጋርተውናል። ለዚህም የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ መገንባት ባለበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑን ነው በደስታ የተናገሩት።
በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባቱ በወረዳው የሚስተዋለውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንደሚፈታ የተናገሩት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ ሙላት አዲስ ናቸው። ፋብሪካው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።
የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን አንስተው፤ ይህንን ፍላጎት በሀገር ውስጥ ለመሸፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል። ለአብነትም በወረዳው ከሦስት ዓመት በፊት ይቀርብ የነበረው የአፈር ማዳበሪያ 60 ሺህ ኩንታል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ የይቅረብልን ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ወደ 130 ሺህ ኩንታል ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ ግምት ውስጥ አስገብቶ የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት መታሰቡ የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች መሠረታዊ ችግር የሚፈታ ዉሳኔ ነው፡፡
ፋብሪካዉ ተጠናቆ ወደ ምርት ሲገባ አርሶ አደሮች ያለምንም እንግልት፣ መጉላላት እና የጊዜ ብክነት የፈለጉትን ያህል የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ገዝተው ምርት ለማምረት እንደ ሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ምርት እና ምርታማነትን ያሳድጋል፤ ላልተገባ ወጪ እንዳይዳረጉ ያደርጋል። ሌላው የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል። አጓጉዞ ወደ ሀገር ቤት ለማስገባት የሚደረገውን ከፍተኛ ውጣ ውረድም ያስቀራል ብለዋል።
ሊገነባ የታሰበው የማዳበሪያ ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን ሊያሳድግ እንደሚችል ያስታወቁት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ናቸው። ፋብሪካው ከፍተኛን ወጪ እና የውጭ ምንዛሬን እንደሚያስቀርም አብራርተዋል። በአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ክልሉ በዕቅዱ መሠረት ጥቅም ላይ እያዋለ ያለው በቂ አለመሆኑን አንስተዋል። በአማራ ክልል ከሚለማው መሬት አኳያ በአንድ የምርት ዘመን ብቻ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልገው ያስረዱት ኃላፊው ሆኖም እስካሁን ድረስ ክልሉ የተጠቀመው የአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛው ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለመገንባት የታቀደው የማዳበሪያ ፋብሪካ ለክልሉ አርሶ አደር ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነውም ብለዋል። በዋጋ እና በአቅርቦት በኩል ይገጥም የነበረውን ችግር የሚያቃልል ይሆናል ነው ያሉት።
የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አመላክተዋል። የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው ሲገነባ አርሶ አደሩ በፈለገው ጊዜ፣ በሚፈልገው መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዳንጎቴ ግሩፕ የ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ነሐሴ 22 ቀን 2017 ዓ.ም መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ስምምነቱ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችል ነው። ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ አህጉር የግብርናን ምርታማነት ከፍ ለማድረግ እና ለማሳደግ ሚና ይኖረዋልም ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ መሆኑንም አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ፈርመናል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ከመላው አህጉር ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል ብለዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች እየወጡበት ተጓጉዞ ወደ ሀገር ቤት የሚገባው የአፈር ማዳበሪያ ሂደቱ እጅግ አድካሚ ስለመሆኑም አንስተዋል። ይህንን ችግር ለመሻገር ነው የኢትዮጵያ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው እንዲገነባ የተወሰነው። የግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ዋናው ግብዓት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ መሆኑን አስገንዝበበዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ስለሚገባ ማጓጓዙ እና ማድረሱ በጣም ከፍተኛ ችግር ስላለበት ማምረት በሚገባን ልክ ምርት እንዳናመርት ጫና እንደነበረው አብራርተዋል። የአፈር ማዳበሪያን በራስ አቅም ማምረት መቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ40 ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል፡፡ አንኳር ስትራቴጂክ ፕሮጀክት በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ትጋት መምራት የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስገንዝበዋል። በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል ብለዋል።
ፋብሪካው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በጥራት እና በፍጥነት ለመገንባት በቁርጠኝነት ይሠራል ያሉት ደግሞ የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ ናቸው።
ስምምነቱን ተከትሎ አሊኮ ዳንጎቴ እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ማዳበሪያ ከውጭ ታስገባ ለነበረችው ኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ እና መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለውን ውጤት ይበልጥ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለውን ውጤት ይበልጥ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በጥራት እና በፍጥነት ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተገልጿል።
መረጃ
የግብርና ግብዓቶች፦
ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ፣
የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣
ምርጥ ዘር፣
የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካሎች፣
ትራክተር፣
ኮምባይነር፣
ትሬሸር… እና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካትታል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም