ጀስቲን ቢበርን ምን ነካው?

0
104

የፖፕ ኮከቡ መንገዱን ስቷል።  በልጅነቱ የገነባው ዝናው እና ሀብቱ ማሽቆልቆል ጀምሯል።  በይፋዊ መድረኮች ከሕዝብ ጋር አይገናኝም። በለጋ እድሜው ያገኘው ከፍተኛ ዝና ስላጨናነቀው ከቁጥጥር ውጭ መሆን ጀመረ፡፡

ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በሎስ አንጀለስ ከተማ በሕዝባዊ መድረኮች ከታዬ በኋላ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። የ31 ዓመቱ ጀስቲን ቢበር በህይወቱ ውስጥ ከባዱን ጊዜ እያሳለፈ ለመሆኑ የተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ዋቢ ሆነው ይጠቀሳሉ።

በወጣትነት እድሜው ብዙዎች ለስልሳ እና ከዚያ በላይ ዓመታት ሰርተው ያገኙትን (ብዙዎችም ያላገኙትን) የግራሚ ሽልማት ሁለት ጊዜ ወስዷል። ሰባት የስቱዲዬ የሙዚቃ አልበሞችን ሰርቷል። በብዙ ሚሊዮን ቅጂዎች ሸጧል። ከ150 በላይ ኮንሰርቶችን አቅርቧል። ወጣቶች ከፍቅራቸው የተነሳ  እሱን ለማግኘት ግርግር ፈጥረው ዝግጅት ተሰርዞ ያውቃል።  ትኩሳታችን ብለው ይጠሩታል- አድናቂዎቹ።

ቢበር ወጣት ነው። ሀብታም ነበር። ትዳር አለው። እንዲሁም የመጀመሪያ ልጁን በቅርቡ አግኝቷል። ከሥራ እረፍት ላይ ነው። የሙዚቃ አልበም ካወጣ አራት ዓመት በኋላ ባለፈው ሐምሌ 7ኛ አልበሙን ለቋል።

እውነታው ግን ቢበር ደስተኛ፣ ጤነኛ፣ የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አይደለም። የቅርብ ጊዜ የአደባባይ ገጽታዎቹ  ይህን የሚያጠናክሩ ናቸው። ወርቃማው ፊቱ ገርጥቶ፣ ልብሱን እየጎተተ፣ በተሰላቸ ፊት ሲጓዝ ይታያል።

ራቁታቸውን በሚደንሱ ሴቶች እና በዳንሰኞች ተከቦ በመጠጥ ቤት ውስጥ ታይቷል። በካሊፎርኒያ በረሃ በተካሄደው ታላቅ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ጀስቲን ቲሸርት ሳያደርግ ሲደንስ እና ማሪዋና የሚያጨስ ተስተውሏል።

እንዲሁም ቢበር ፓልም ስፕሪንግስ ከተባለ ካፌ ሲወጣ በከፍተኛ ሁኔታ ተናዶ ፎቶ አንሺዎችን ሲጋፈጥ ተስተውሏል። “እናንተ የምታስቡት ስለ ገንዘብ ብቻ ነው፣ ስለ ሰው ልጆች አይደለም” ሲል ጮክ ብሎ ሲናገር ታይቷል። “ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ!” በማለት መጮኹን ይቀጥላል።

ፓፓራዚዎች (ድብቅ ፎቶ አንሺዎች) ሲያሳድዱት የሚያሳይ ቪዲዮ ለጥፎ “ይህ መቆም አለበት” ሲል ጽፏል። በመቀጠልም “ከሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እየደረሰብኝ ነው። እኔ ተጠቂ አይደለሁም፤ ሎስ አንጀለስ መጥፎ እንደሆነች እየተረዳሁ ነው” በማለት ይህን ሰውን የማሳደድ ችግር ሁሉም ሰው ሊታገለው እንደሚገባ ጽፎ ነበር ሲል ሲኤን ኤን ዘግቧል።

ዝነኞችን በማሳደድ ፎቶ የሚያነሱት ፓፓራዚዎችን በደል እያደረሱብኝ ነው፤ መተባበር አለብን ሲል ድምጹን አሰምቷል። “በዚህ ምክንያት ሰዎች ሞተዋል፤ ልዕልት ዳያና ወዲያው ወደ አእምሮዬ የምትመጣው ናት” በማለት የሚዲያውን ክትትል አውግዟል።

ፒፕል  መጽሔት “ቢበር በአሁኑ ሰዓት ብዙ የተለያዩ ውስጣዊ ችግሮችን እየተጋፈጠ ነው” ብሏል። “በቅርቡ በጣም መጥፎ ውሳኔዎችን እየወሰነ ነው፤ ይህም ጓደኝነቱን፣ ገንዘቡን እና ንግዱን የበለጠ እየጎዳው ነው። ሰዎች ስለ እሱ ተጨንቀዋል” በማለት ጽፏል። ጂስቲን በዚህ ደረጃ እንዴት ሕይወቱ ተቃወሰ? ምንድን ነው የገጠመው የሚለው ቁልፉ ጥያቄ ነው። የጥያቄው መልስ ያለው ቀጥሎ በተናገረው ሐሳቡ ውስጥ ነው። እንዲህም ይላል “አንዳንድ ጊዜ ራሴን እጠላለሁ፤ ቁጣ ቁጣ ይለኛል፤ የአስመሳይነት ስሜት ይሰማኛል። በአብዛኛዎቹ ቀናት ብቃት እንደሌለኝ እና ብቁ እንዳልሆንኩ ይሰማኛል” ሲል አሁን ያለበትን ሁኔታ ተናግሯል።

ዝና በልጅነቱ የተጫነው ቢበር ዝናውን መሸከም ከብዶታል። በአስር ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ ዝና ማግኘቱ ቢጠቅመውም እንኳን ሕይወቱ ቀውስ እና ትርምስ የበዛበት ነው። እንደ ቢበር  በአጭር ጊዜ የተሳካላቸው  አርቲስቶች ጥቂት ናቸው።

ጀስቲን ቢበር  መጋቢት አንድ ቀን 1994 እ.አ.አ  በኦንታሪዮ፣ ካናዳ ነው የተወለደው። እናቱ  ፓትሪሺያ ማሌት ትባላለች። በ2018 እ.አ.አ ካገባት ሚስቱ ሃይሊ ባልድዊን ጃክ ብሉዝ የተባለ ልጅ ወልዷል። እናቱ ፓትሪሽያ ማሌት ልጇ ኮከብ ከመሆኑ በፊት ቤተሰቡን ለመደገፍ ዝቅተኛ ክፍያ በሚያስገኙ ሥራዎች የምትተዳደር ሴት ነበረች። ብቻዋን የምትኖር በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝም ነበረች። በልጅነቱ ጊታር እና ፒያኖ በመጫወት ራሱን አስተምሯል። ድጋፍ የምታደርግለት ደግሞ እናቱ ነበረች።

ባዮግራፊ ገጽ ጀስቲን ቢበር ልጅነቱ ላይ የተቆለለበት ዝና እንዳጠፋው ጽፏል። አነሳሱን መለስ ብለን እናስታውሰው እስኪ። ሁሉንም የጊዜ አቆጣጠሮች በአውሮፓዊያን አድርገን የሙዚቃ ጅማሮውን እንመርምረው። ከ2007-2008 ባሉት ዓመታት  የቢበር እናት የልጇን የሙዚቃ ትርኢቶች ቪዲዮዎች ዩቱዩብ ላይ መለጠፍ የጀመረችበት ጊዜ ነው። የሪከርድ ሥራ አስፈጻሚ ስኩተር ብራውን ቪዲዮዎቹን አይቶ ቢበርን እና እናቱን ወደ አትላንታ በማምጣት ከታዳጊው ጋር ውል ተፈራረመ። በ2008 ለድምጻዊ  አሸር ሙከራ ሰጥቶ በአይስላንድ  ሪከርድስ ስር ውል ተፈራረመ።

በግንቦት ወር 2009 ዋን ታይም የተሰኘውን ነጠላ ዜማውን ለቀቀ። ይህም በአሜሪካ እና በካናዳ ተወዳጅ ሆነለት። በህዳር 2009 ሰባት ዘፈኖችን የያዘው ኢፒ ማይ ወርልድ አልበም ሲለቀቅ መላው አሜሪካን አስደሰተ።

በህዳር 2009  በኒው ዮርክ በሚገኘው ሩዝቬልት ፊልድ ሞል ሊደረግ በነበረው ኮንሰርት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶች  ተሰባስበው ነበር። የቢበር ኮንሰርት ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ ምክንያት ተሰረዘ።

መጋቢት 2010 የመጀመሪያው ሙሉ አልበሙ ማይ ወርልድ 2 ነጥብ 0 ተለቀቀ። በቢልቦርድ ሰንጠረዥ ላይ ቁጥር አንድ ሆኖ ተመዘገበ።  አምስት ሚሊዮን ኮፒዎችም ተሸጧል።

ቢበር መልከ መልካም ታዳጊ ነበር። ውብ የልጅነት መልክ አለው። አማላዩ ወጣት አርቲስት በሚልም ስሙ ሰፍሯል። ጥሩ ዘፋኝ ነው።  ኮንሰርቶችን ሲያዘጋጅ ወጣት ልጃገረዶች ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ብዙ ጊዜ መድረኩ ታውኮ ያውቃል። በተደጋጋሚ  ትርኢቶችም ተሰርዘውበታል። አስገድዶ ደፍሮኛል፣ ጥቃት ፈጽሞብኛል፣ ልጅ ወልዶልኛል የሚሉ ብዙ ክሶች ገና በ17 ዓመቱ ፍርድ ቤት አቅርበውታል።

በህዳር 2011 ሁለተኛው የስቱዲዮ አልበም አንደር ዘ  ሚስልቶ ሲለቀቅ ወደ ሁለት ሚሊዮን ቅጅዎች ተሸጧል። በሰኔ 2012  ሦስተኛው የስቱዲዮ አልበሙ ብሊቭ የተለቀቀበት ጊዜ ነበር። ከ 2.7 ሚሊዮን ቅጅዎች በላይ  ተሸጧል።

መጋቢት ስምንት ቀን  2013  ለረጂም ሰዓታት በመዝፈን ትንፋሽ ካጠረው በኋላ ለንደን ውስጥ ለአጭር ጊዜ ሆስፒታል ገብቶ ነበር።

በሐምሌ 2013 ቢበር በባልዲ ውስጥ ሲሸና እና የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተንን ፎቶ ሲያበላሽ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ። ቢበር በኋላ  ክሊንተንን ይቅርታ ጠየቀ። በ2014  የሎስ አንጀለስ የጎረቤቱን ቤት በእንቁላል በመደብደቡ ተከሰሰ። ሰክሮ በማሽከርከር እና በማያሚ የሐይቅ ዳርቻ የመኪና ውድድር በማድረግ ተጠርጥሮ ታሰረ። በቶሮንቶ ከተማ የሊሞዚን ሹፌርን በመደብደብ ተከሰሰ።

ካናዳ ውስጥ  መኪናውን ካጋጨ   በኋላ በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በጥቃት እና በአደገኛ አሽከርካሪነት ክስ ታሰረ። ሰኔ አራት 2015 ቢበር በስትራትፎርድ፣ ኦንታሪዮ በጥቃት እና ጥንቃቄ የጎደለው አሽከርካሪነት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ።

በየካቲት 15 ቀን 2016  ዌየር አር  ዩ ናው በሚለው ምርጥ የዳንስ ሙዚቃ ቀረጻ የግራሚ ሽልማት አሸነፈ። ህዳር 22 ቀን 2018 ቢበር ከሞዴል ሃይሊ ባልድዊን ጋር ጋብቻውን በኢንስታግራም አረጋገጠ።

በመጋቢት 25 ቀን 2019 በኢንስታግራም ልጥፍ (ፖስት) ላይ ቢበር በአእምሮ ጤንነቱ ላይ ለማተኮር ከሙዚቃ ሥራ ለጊዜው ፋታ  እንደሚወስድ አስታወቀ። በጥር 8 ቀን 2020 ነበር ቢበር ላይም የሚባል  በሽታ እንዳለበት የገለጸው። ቦርሬሊዎሲስ ወይም የላይም በሽታ የሚከሰተው በቦረሊያ ቡርዶርፌሪ ባክቴሪያ ሲሆን በተበከለ መዥገሮች ንክሻ ወደ ሰው ይተላለፋል።

በመጋቢት 14 ቀን  2021 ከዳን እና  ሼይ ጋር በሠራው 10 ሺህ ሀወርስ ዘፈን ምርጥ የሀገር ውስጥ ሙዚቃ ቡድን (ጥንድ አፈጻጸም) የግራሚ ሽልማት አሸነፈ።

ሰኔ 10 ቀን  2022 ቢበር የራምሴይ ሃንት ሲንድሮም ስላጋጠመው ከኮንሰርት እረፍት እንደሚወስድ አስታወቀ። ሕመሙ ግማሽ ፊቱን ማንቀሳቀስ እንዳይችል እና መድረክ ላይ መውጣት እንዳይችል አድርጎታል። ይህ የፊት ሽባነት  በሽታ ሰውነቱን ማንቀሳቀስ እንዳይችል ክለከለው። ይህም ከፍተኛ ጭንቀት እና ድብርት ውስጥ አስገብቶታል።

ነሐሴ 23 ቀን 2024 ሃይሊ እና ጀስቲን ቢበር የመጀመሪያ ልጃቸውን ጃክ ብሉዝ ቢበር መወለዱን አስታወቁ።

ሐምሌ 11 2025 ሰባተኛው የስቱዲዮ አልበሙ “SWAG” ተለቀቀ። ይህ ከአራት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው አዲስ የስቱዲዮ አልበሙ ነው። 21 ሙዚቃዎችን ያካተተው አልበሙ የግሉን ሕይወት የሚያሳይ ነው።

አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት አለው ተብሎ በሚወራበት ዘመን በ2022 ከሁለት መቶ ዘጠና ሁለት በላይ ሙዚቃዎች ያሉትን የሙዚቃ ካታሎግ በገንዘብ ችግር ምክንያት ለሂፕኖሲስ ሶንግስ ካፒታል በ200 ሚሊዮን ዶላር ሸጧል። በዩቱዩብም ይሁን በሌላ ማንኛውም አማራጭ ገንዘብ ሊሰራባቸው አይችልም። የሙዚቃ ባለቤትም አይደለም። ይህን ያደረገው ደግሞ እዳ ውስጥ በመግባቱ እና ገንዘብ በማጣቱ ነው።

ሚስቱ ሃይሊ ሮድ የተሰኘውን የቆዳ እንክብካቤ ብራንዷን  እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ በሚችል ስምምነት በመሸጥ ባለቤቷን ከገንዘብ ውድቀት ለማዳን እንደሞከረች  የሚገልጹ ምንጮች አሉ።

አሁንም የፊት ሽባነት ሕመም እና የአዕምሮ ጤንነት ችግር ገጥሞታል። የአደንዛዥ እጽ ሱስ እና ሌሎች የስነ ልቦና ችግሮች አሉበት።

ስኩተር ብራውን የተባለው ማናጀሩ ነው የሚሰራውን ሁሉ ገንዘብ የወሰደበት፤ አደንዛዥ እጽ እና ሌሎች ችግሮች ውስጥ የከተተው ብለው የሚጽፉ ብዙ አሉ።

አሁን ጀስቲን ቢበር የክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ገብቶ መጽናናት እያገኘ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። ጨርሶ እንዲጽናና እመኛለሁ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here