የተለያዩ ማርሻል አርቶች ቅልቅል በሆነው ጂት ኩንዶ አራተኛ ዳን ደረጃ ደርሷል፤ በወጣትነት እድሜው የላቀ የአሰልጣኝነት ደረጃ ለደረሱ የሚሰጠውን የማስተርነት ማዕረግም አግኝቷል:: በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል:: ጂት ኩንዶ ማርሻል አርትንም ለመጀመሪያ ጊዜ ለክልላችን አስተዋውቋል:: በአማራ ክልል ብቸኛ የሆኑትን ማዕከሎች በወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍቷል:: አሰልጥኖ ያበቃቸው ሰልጣኞቹ በ2015 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ክልላችንን ወክለው የሁለተኛ ደረጃን ይዘው ተመልሰዋል:: በተለይ ወጣቱ አልባሌ ስፍራ እንዳይውል እና ሀገር ተረካቢ እንዲሆን የበኩሉን እየሠራ ይገኛል፡– ማስተር ሳዳም ሀብታሙ:: ማስተር ሳዳምን የበኩር እንግዳችን አድርገነዋል፤ መልካም ንባብ::
የት ተወለድክ? የት ተማርክ? የልጅነት ጊዜስ እንዴት ነበር?
የተወለድኩት በናዝሬት (አዳማ) ከተማ ነው:: ቤተሰቦቼ ለሥራ ምክንያት ከመካነሰላም ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደው ነበር:: በሁለት ዓመቴ ተመልሰን ወደ መካነሰላም መጣን፤ እስከ ሦስተኛ ክፍል እዛው መካነሰላም ከተማርኩ በኋላ እንደገና ወላጆቼ ወደ ናዝሬት ይዘውኝ ተመለሱ:: ትምህርቴንም እንደገና ሀ ብየ እዛው ናዝሬት ጀመርኩ:: አሥረኛ ክፍል የመሰናዶ መግቢያ ፈተና ውጤት እንደጠበኩት አልመጣልኝም፤ በመሆኑም ቴክኒክ እና ሙያ ገብቼ ሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ጀመርኩ:: ነገር ግን ስፖርቱን ጀምሬ ስለነበር ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደድኩ::
ጂት ኩንዶ ምንድን ነው?
ጂት ኩንዶ ማርሻል አርት በታዋቂው የቻይና እና አሜሪካ ዜግነት በነበረው ብሩስ ሊ (በህይወት የለም) ነበር የተጠነሰሰው:: ጂት ማለት መከላከል ሲሆን ኩንዶ ደግሞ ማጥቃት ማለት ነው:: ብሩስ ሊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው ይሄን ስፖርት የፈጠረው:: በመጀመሪያ ጓደኞቹን ሰብስቦ ነበር የሚያሠራው፤ በኋላ አስፋፍቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስፋፋት ቻለ:: ስፖርቱም ወደ ፊልሙ ዓለም እንዲገባ እና ዝነኛ እንዲሆን አግዞታል:: ኩን ፉ የቻይና፣ ቴኳንዶ የኮሪያ፣ ካራቴ የጃፓን እንደሚባለው ሳይሆን ጂት ኩንዶ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ሃብት እንዲሆን ብሩስ ሊ ጽኑ ፍላጎት ነበረው:: በዚህም ምክንያት ከሀገሩ ቻይና የተወሰነ ውግዘት ደርሶበታል::
ጂት ኩንዶ የተለያዩ የማርሻል አርት አይነቶች ድብልቅ ውጤት ነው:: ከሁሉም አይነቶች የተለያዩ ስልቶች እና ትምህርቶች ተለቅመዉ ተካተውበታል:: በዚህም ተቀናቃኝ የሚያውቀውን እና የሚችለውን በማወቅ ከተቀናቃኝ በልጦ መገኘትን ሲያስተምር፣ በተወሰነ መርህ እና ህግ ብቻ መታጠርን የማይፈቅድ ነው:: በዚህ መሠረት በጂት ኩንዶ ጥበብ ከወገብ በታች ይሄን ያክል በመቶ፣ ከወገብ በላይ ይሄን ያክል በመቶ መጠቀም የሚል ህግ የለም፤ በነጻነት ማስኬድ ይቻላል:: ምቶች፣ አርቶች (ጥበቦች) እና የሰርከስ አይነቶችም እንዲሁ ወሰን የላቸውም:: በዚህ ምክንያት ሰልጣኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ያገኛሉ::
የጂት ኩን ዶ መሰረታዊ መመሪያዎች ቀላልነት (simplicity)፣ ቀጥተኛነት (directness) እና ነጻነት (freedom) ናቸው:: “ቅርጽ የሌለው ቅርጽ” ሲልም ብሩስ ሊ በፍልስፍና ሀረጋቱ ይገልጸዋል:: ቴክኒኮቹ እና ፍልስፍናዎቹ በእውነተኛ ፍልሚያዎች እና በፈታኝ የህይወት ገጠመኞች ውስጥ ቢተገበሩ ውጤታማ ያደርጋሉ::
ወደ ማርሻል አርት በተለይም ወደ ጂት ኩንዶ እንዴት ገባህ?
በልጅነቴ ቤተሰቦቼ ስፖርት እንድሰራ ይፈልጉ ነበር፤ ያበረታቱኛልም:: በዚህ ምክንያት የስፖርት ፍቅር ከህጻንነቴ ጀምሮ በውስጤ አድሯል:: እያደኩ ስመጣ በቋሚነት የምሰለጥነውን የስፖርት አይነት እፈልግ ነበር:: የተለያዩ ስፖርቶችን እየተዘዋወርኩ ለማየት ሞክሬያለሁ:: ጓደኞቼን እና ሌሎች ሰዎችንም በየትኛው የስፖርት ዘርፍ ብሰማራ ውጤታማ እሆናለሁ? እያልኩ አማክር ነበር:: በዚህ ሁኔታ እያለሁ አንድ ጓደኛየ ጂት ኩንዶ የሚባል አዲስ የስፖርት ዓይነት ለመሥራት እንደተመዘገበ ይነግረኛል:: በማግስቱ ተያይዘን ወደ ስፖርት ቤቱ ሄድን:: በስፖርት ቤቱ ያየሁት እጅግ ደስ የሚል ነበር:: ወዲያዉኑ ይሄን ስፖርት ነው የምሠራው ብየ ወሰንኩ:: በዚሁም ቀጥየ የማስተርነት ማዕረግ አግኝቻለሁ::
የራስክን ማሰልጠኛ እንዴት ከፈትክ?
ናዝሬት እያለሁ በስፖርቱ በመግፋት አንጋፋ ኪሚባሉት ደረጃ ደረስኩ፤ አሰልጣኝም መሆን የሚያስችለኝን ትምህርት አገባደድኩ:: አማራ ክልል ውስጥ ጂት ኩንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል አለመኖሩ ይቆጨኝ ነበር:: የተለያዩ ውድድሮች ሲኖሩ እኔ ኦሮሚያ ክልልን ወክየ ነበር የምወዳደረው:: ይህንን የመሰለ ጥበብ ለምንድን ነው ክልላችን ውስጥ የማይኖረው የሚለው ሃሳብ ውስጤ ነበረ፤ ነገር ግን አሰልጣኝ የመሆን እና የራሴን ማዕከል የመክፈት ሃሳቡም ሆነ ፍላጎቱ አልነበረኝም::
አሰልጣኜ ማስተር የሱፍ “አማራ ክልል ስፖርት ቤት መክፈት አለብህ” እያለ ብዙ ጊዜ ይገፋፋኝ ነበር:: ሃሳቡን እምብዛም አልቀበለውም:: መነሳሳት እኔ ላይ ለመፍጠር “ስፖርት ቤት ከፍቷል” ብሎ ለሰዎች ማውራት ጀመረ:: ጓደኞቼ “ስፖርት ቤት ከፈትክ አይደል?” ይሉኛል፤ እዚህ ያሉት ቤተሰቦቼም “ና እና ክፈት ብዙ ሰው ታገኛለህ” እያሉ ይወተውቱኛል:: ቤተሰብ ጥየቃ ወደ መካነ ሰላም ስመጣ ተመልሼ እንዳልሄድ ገፋፉኝ፤ እኔም ውስጤን አሳመንኩ፤ ከዚያ ሁሉን ነገር ጨርሼ 2011 ዓ.ም ላይ የጂት ኩንዶ ማዕከሉን ከፍቼ ስልጠናውን መስጠት ጀመርኩ::
የማኅበረሱ አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
እውነት ለመናገር አብዛኛው ሰው ስፖርቱ ምን እንደሆነ በስም እንኳ አያውቀውም:: አጠቃላይ ለስፖርት የነበረው ንቃትም ይህን ያህል ነው የነበረው:: የሚያውቁትም ተደባዳቢ እና ምግባረ ብልሹ አድርጎ የማሰብ ነገር ነበር::
ስፖርቱ አዲስ እና በአይነቱ የተለየ በመሆኑ የተወሰኑ ተማሪዎችን አገኘሁ:: እነሱን ይዤ በደንብ መሥራት ጀመርኩ:: ስልጠና የሚወስዱ ልጆች በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣታቸውን ቤተሰቦቻቸው ሲመለከቱ ደስተኛ ሆኑ፤ ለስፖርቱም የበለጠ ጥሩ አመለካከት አደረባቸው፤ ለሌሎች ሰዎችም ማስተዋወቅ እና ስለስፖርቱ በጎ ነገር ማውራት ጀመሩ:: በዚህ ሂደት የአካባቢው ማኅበረሰብ አመለካከቱ መቀየር ጀመረ::
ስፖርት ቤቱን ስጀምር አልባሌ ወሬ የሚያወሩ እና እንቅፋት ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች ነበሩ:: “ብራችሁን ይዞ ሊሄድ ነው፤ መጤ ነው፤ ተደባዳቢ ነው፣ አታላይ ነው” ሌላም ሌላም ነገር በማውራት ሊያደናቅፉ የሞከሩ አሉ:: ሁሉንም በትዕግስት አልፌ፣ ስፖርቱም የሚያስተምረው ይሄንኑ ነው፤ ትልቅ ማዕከል ሊሆን ችሏል::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም