በዛሬው ሽርሽር ወደ ምእራብ ጎጃም ልውሰዳችሁ። የሸንኮራዋ ምድር፣ የገራይ ግድብ መገኛ፣ የምእራብ ጎጃም ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ፍኖተ ሰላም ልናቀና ነው። ከባህር ዳር 180 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው ፍኖተ ሰላም የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም እምብዛም አይታወቁም ። እናም አንድ ወቅት ወደ ከተማዋ ጎራ ባልንበት ወቅት ከቅርሶቿ አንዱ የሆነውን የጆርጌ ድልድይ ለማየት እድሉን ስላገኘን ወደ ጆርጌ ገሰገስን። አብረን እንጓዝ።
ከፍኖተ ሰላም ተነስተን ከወቅቱ የባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ባለሙያዎች ጋር ወደ አዲስ አበባ አቅጣጫ ጉዞ ጀመርን። የሚያዝያው ሙቀት ከባድ ስለነበር በረድ እስኪልልን መቆየት ስለነበረብን ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነው የተነሳነው። ጥቂት እንደተጓዝን ዋናውን የአስፋልት መንገድ አቋርጦ የሚያልፈውን የብር ወንዝ ድልድይ አገኘን።
ብር ወንዝ ፍፁም በሆነ እርጋታ ወደ ምእራብ አቅጣጫ ይፈስሳል። ብር ወንዝ መዳረሻውን ዓባይ ያደረገ በዞኑ ከሚገኙ ታዋቂ ወንዞች አንዱ ነው። በበጋ ወቅት ያን ያህል አስጊ ባይሆንም በክረምት ግን ከአፍ እስከ ደገፉ ሞልቶ ለገላጋይ የማይመች ሀይለኛ ወንዝ መሆኑን ባለሙያዎቹ አጫውተውናል፡፡ ይህ ሀይለኝነቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ እንቅስቃሴ በእጅጉ ሲገድብ እንደቆየም ነግረውናል።
ብር ወንዝ ጉልበታም እና አስቸጋሪ ብቻ አይደለም፣ አገልጋይም እንጂ። ለአካባቢው ማህበረሰብ የኑሮ ምርኩዝ መሆን የቻለ ከፍተኛ አሸዋ የሚታፈስበትም ነው። በዚህ ላይ በወንዙ ዳር ለዳር የበቀሉት የተፈጥሮ ዘንባባዎች እና ሌሎች ዛፎች ለአካባቢው ውበትን ከመለገሳቸው በላይ ለተመለከታቸው ሁሉ መንፈስን ያድሳሉ።
“ለኃይለኛም ኃይለኛ አለው” ነውና ብሂሉ ብር ወንዝ ግን በጉልበታምነቱ የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ ገድቦ እንዳይቀጥል መላ የተበጀለት ይመስላል። እድሜ ለጆርጌ ድልድይ ብር ወንዝ አደብ ገዝቶ ከህብረተሰቡ ስር ሆኖ በፀባይ እንዲፈስ ተገድዷል።
ጆርጌ ድልድይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ እንደተገነባ የሚነገርለት ጠንካራ እድሜ ጠገብ ድልድይ ነው። ጆርጌ ከዋናው አስፋልት 500 ሜትር ወደ ምእራብ አቅጣጫ ገባ ብሎ ይገኛል። አንድ በትውልድ ግሪካዊ በዜግነት ኢትዮጵያዊ የነበሩ ቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ የተባሉ ሰው በአካባቢው ይኖሩ ነበር፣ በአካባቢው አጠራር “ጆርጌ” በሚል ስም ይታወቁ ነበር። እርሳቸው ለድልድዩ መሰራት ምክንያት እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ ወደ ጎጃም ምድር በመምጣት ግራርማ በምትባል ጃቢ ጠህናን ወረዳ ውስጥ በምትገኝ የገጠር ቀበሌው የመጀመሪያ ቆይታቸውን አድርገው ነበር። ጥቂት ቆይተውም ባከል ወደተባለችው ቀበሌ በመሄድ ቋሚ ኑሯቸውን በዚያው መስርተው ከአንዲት ኢትዮጵያዊት ጋር በትዳር ተጣምረው ወልደው ከብደው ያለፉ ባለታሪክ ናቸው። እኝህን ሰው የአካባቢው ማህበረሰብ “ጆርጌ” እያለ ይጠራቸው እንደነበር እና ድልድዩም “ጆርጌ” እንደተባለ መቅረቱን አስጎብኝዎቻችን አጫውተውናል።
ቀኝ አዝማች ጆርጌ በስራ ወዳድነታቸው የታወቁ ሲሆኑ ለአካባቢው የመጀመሪያውን የውሃ ወፍጮ አስገብተው ህብረተሰቡን የጠቀሙ ሰው በመሆናቸው የሀገሬው ሕዝብ ይወዳቸው እንደነበርም እያወጉን ወደ ድልድዩ ጉዟችንን ቀጠልን።
ቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ የአካባቢውን ማህበረሰብ ወግ እና አኗኗር በማክበር እና በመላመድ አብረው እየኖሩ የማህበረሰቡን ሀዘን እና ደስታ እየተጋሩ የኖሩት እኒህ ተወዳጅ ሰው በብር ወንዝ ሙላት የአካባቢው ህብረተሰብ ይደርስበት የነበረውን ችግር በደንብ ይረዱ ነበር፤ እናም ቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ያዋለ ተግባር በመፈፀም የህብረተሰቡን እፎይታ ለማየት በመነሳሳት በብር ወንዝ ላይ ድልድይ ለመስራት አሰቡ፣ ያሰቡትንም ፈፀሙት።
ጆርጌ ድልድይ ላይ ደረስን፤ በስፍራው ስንገኝ የተመለከትነው ድልድይ ጥንታዊ የስልጣኔ አሻራ ያረፈበት መሆኑን እና የእድሜ ባለፀጋነቱን አይቶ ለመገመት ጊዜ አልፈጀብንም። ምንም እንኳ ጥልቅ በሆነ ጥናት የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ጆርጌ ድልድይ በጎጃም ከተገነቡት ድልድዮች ሲተያይ በጥንታዊነቱ ቀዳሚ እንደሚሆን ይገመታል።
የጆርጌ ድልድይ የአፄ ፋሲል ግንብ በተገነባበት አግባብ በሚያስገርም ጥበብ ተጋጥመው ተጣብቀው የቆመ፣ ውብ ንድፍ ያለው፣ የሀይለኛውን ወንዝ ጉልበት መቋቋም ያስቻለ ጥንካሬ ይዞ የተሰራ አስገራሚ ቅርስ ነው። የአሰራር ጥበቡ የዘመኑን ስልጣኔ የሚያንፀባርቅ ድንቅ ስራ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሰዎች እና እንስሳት የብር ወንዝን ሳይፈሩ ቁልቁል እያዩት እንደፈለጉት ይተላለፉበታል። እድሜ ለቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ፣ እያሉ ይጠቀሙበታል።
የሚገርመው ግን የቀኝ አዝማች ጆርጅ ዮሀንስ ዘመዶች ከግሪክ ሀገር ተነስተው ስለ ድልድዩ ያላቸውን ጥቂት መረጃ ይዘው እንኳ አልፎ አልፎ እየመጡ እንደሚጎበኙት ያጫወቱን የቱሪዝም ባለሙያው የአካባቢው ሰው ግን ዞር ብሎ እንደማያየው ነግረውናል። በአካባቢያችን ያሉ ቅርሶችን መጎብኘት ባህል እናድርግ እያልን በዚሁ አበቃን።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም