ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
በቻይና ቾንግቺንግ ግዛት ከመሬት 116 ሜትር ጥልቀት ላይ ወደሚገኘው ሆንግያንኩን የምድር ውስጥ ባቡር ጣቢያ መውጫ እና መውረጃ አሳንሰር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ሲጓጓዙ ጆሯቸው የሚደፈን መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
የጆሮ ለተወሰነ ጊዜ መደፈን ከጆሮ ታምቡር ውስጥ እና የውጪው የዓየር ግፊት መጠኑ የተለያየ በሚሆንበት ጊዜ ይከሰታል:: ሁኔታውን በበለጠ ለማብራራት ተመሣሣይ ሁነት የሆነው አውሮፕላን ወደ ከፍታ ሲወጣና ሲወርድ፣ ወይም በተሽከርካሪ አቀበት ሲወጡ ወይም ሲወርዱ ጊዜያዊ የጆሮ መደፈን እንደሚከሰት ነው የተገለፀው::
አብዛኛዎቹ የባቡር ጣቢያዎች የጆሮ መደፈን እንደሚያስከትሉ ያስነበበው ድረ ገፁ የቾንግቺንግ ግዛቱ ከመሬት ወለል 116 ሜትር ጥልቀት ወይም 40 ፎቆ ቁልቁል የመውረድ ያህል መሆኑ፤ ለጆሮ ጊዜያዊ መደፈን እንደሚያበቃ ነው የተብራራው::
የቻይና ፈጣን የባቡር መስመሮች በመልከዓምድር አቀማመጧ ምክንያት ሽቅብ እና ቁልቁል የሚጠማዘዙ ናቸው። ይህም በዓለም ጥልቅ የመሬት ውስጥ ባቡር መስመር እንዲሠራ ምክንያት መሆኑን ነው ድረ ገፁ ያስነበበው::
የሆንግያን መንደር ደግሞ በጂያሊንግጃንግ ወንዝ አቅራቢያ ከፍ ባለ ኮረብታ ላይ ነው የተቆረቆረችው:: የመንደሯ ኗሪዎች ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ ታዲያ 116 ሜትር ጥልቀት ላይ ወዳለው የባቡር ጣቢያ መውረድ ግድ ይላቸዋል::
ተጓዦች ከላይ ወደታች ወይም ከታች ወደላይ ለመሄድ በእግር 38 ደቂቃ ነበር የሚወስድባቸው:: ይሄ ደግሞ በየዕለቱ ተራራ የመውጣት የመውረድ ያክል አድካሚ እንደነበር ነው የተብራራው:: ለተስተዋለው ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ የተዘየደው ዘመናዊ መጓጓዣ በአሳንሰር 53 ሰከንድ በተቀንቀሣቃሽ የደረጃ መውጫ መውረጃ “ስካሌተር” 10 ደቂቃ ይፈጃል።
በቻይና 116 ሜትር ጥልቀት ላይ የሆንግያንኩን የምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያ ከመሰራቱ በፊት በዓለም በጥልቀቱ ቀዳሚ ሆኖ የተመዘገበው የዩክሬኑ የኪዬቭ የመሬት ውስጥ የባቡር ጣቢያ ነበር።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም