ገርአይሌ ወይም ገራሌ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል በሊበን ዞን ነው የሚገኘው፡፡ ፓርኩ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 900 ኪሎ ሜትር፣ ከሞያሌ በስተሰሜን 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የተከለለው፡፡ አጠቃላይ ስፋቱም 38 ሺህ 580 ሄክታር ተለክቷል፡፡
በፓርኩ ዙሪያ ነዋሪዎች የማይበዙበት መሆኑ ለዱር እንስሳት መገኛነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዳዋ ወንዝ ተጎራብቶ በቁጥቋጦና በሳር የተሸፈነው ሰፊ ክልል ለቀጭኔ፣ ዝሆን፣ ጥቁር አውራሪስ ለመሳሰሉት ምቹ መሆኑ ተረጋግጦ ጥበቃ ለማድረግ በ2006 ዓ.ም በፓርክነት መከለሉን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
የፓርኩ ክልል መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ከምድር ወለል 800 ሜትር እስከ 1 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ በዚህም አየር ንብረቱ ከፊል በረሀማ መሆኑ ተለይቷል፡፡
የፓርኩ ክልል ለስድስት ወራት ዝናብ አያገኝም፡፡ ዝናብ የሚጥልባቸው ወራትም ከመስከረም እስከ ህዳር እና ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ብቻ ናቸው፡፡
በፓርኩ የግራር ዛፍ እና አጫጭር ቁጥቋጦዎች በሳር ከተሸፈነው የተንጣለለ ሥነ ምህዳር ጐላ ብለው በተመልካች እይታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በፓርኩ የሌሊት ወፍን ጨምሮ በአካላቸው አነስተኛ የሆኑት ሳይቆጠሩ 27 ትልልቅ አጥቢ እንስሳት ይገኛሉ፡፡
ገርአይሌ ፓርክ በአእዋፍት መገኛነቱም እውቅና የተቸረው ነው፡፡ ለዚህም በፓርኩ ክልል 164 የአእዋፍት ዝርያዎች እንደሚገኙ ነው ከተለያዩ ድረ ገፆች ያገኘነው መረጃ ያመላከተው፡፡
በገርአይሌ ብሔራዊ ፓርክ ውጪ በስተደቡብ እና ምስራቅ በቅርብ ርቀት ከራያ፣ ሶሮሮ፣ ገልገሉ የተሰኙ የአርብቶ አደር መንደሮች ይገኛሉ፡፡
በብሔራዊ ፓርኩ ክልል ተዟዙሮ የዱር እንስሳትን በምስል ለመቅረጽ የተቀመጠ ቁርጥ ያለ ተመን የለውም፡፡ ነገር ግን ዙሪያ ክልሉን የሚያውቁ የአካባቢው ነዋሪዎችን በረዳትነት ለመገልገል ተዋውሎ ገንዘብ መስጠትን ግድ ይላል፡፡
በመረጃ ምንጭነት ዎልክ ኢን ኢትዮጵያ፣ ወርቅ አምባ ቱር፣ ፊልም ፊክሰር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም