ገበያን ለማረጋጋት እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ

0
93

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን በማረጋጋት በኩል ጥሩ እየሠሩ መሆኑን የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን አስታውቋል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ ወራት አቅጣጫ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

የባለሥልጣኑ ኃላፊ ጌትነት አማረ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በክልሉ ገበያን በማረጋጋት፣ በሰብል ግብይት፣ በግብዓት ስርጭት እንዲሁም ኢንቨስትመንት እና ቁጠባን በሚያበረታታ መልኩ ተልዕኳቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።

ክልሉ በችግር ውስጥ ሆኖም ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫቱ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በምክክሩ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሕዝቡ እያበረከቱት ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ “ያለ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ድጋፍ የተለወጠ ኢኮኖሚ የለም” ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው የግብርናው ዘርፍ የበለጠ ምርታማ እንዲሆን ማኅበራቱ መልካም ሥራ እንዳከናወኑ አስታውሰዋል።

ማኅበራቱ አግልግሎት ከመስጠት አልፈው የኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ ምቹ መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ አጀበ አምራቹ ምርትን ለማሳደግ ግብዓት ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ይጠብቃል ብለዋል።

ክልሉ ለዚህ ዓመት የግብርና ሥራ 8 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮች ከሕብረት ሥራ ማሕበራት ብዙ ይጠብቃሉ ነው ያሉት፡፡

የአርሶ አደሮች ምርት በአንዳንድ አካባቢ የገበያ እጦት ሲያጋጥመዉ በወረደ ዋጋ በመሸጥ እየተጎዱ መሆኑን በማንሳት ማኅበራቱ ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ አርሶ አደሮችን ማትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here