የዚህ እትም እንግዳችን ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ ከተማ ውስጥ ነው:: ከአንደኛ እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በደሴ ከተማ ከተከታተለ በኋላ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ደግሞ በኤርትራዋ የአሰብ ከተማ ተምሯል:: ገና በ17 ዓመቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል የሆነው እንግዳችን የሕይወት ጥሪው የሆነውን ኪነ ጥበብን “ሀ” ብሎ የጀመረውም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር “ኪ ቦርድ” የሚባለውን የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ነው::
የውትድርናውን ዓለም ከተቀላቀለ በኋላ አብዛኛውን ጊዜውን በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ያሳለፈው እንግዳችን ከኪቦርድ ተጨዋችነቱ በተጨማሪ በቲያትር ሥራዎችም ተሳትፎ ነበረው:: በ1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት መፍረሱን ተከትሎ ኑሮውን በአዲስ አበባ ያደረገው እንግዳችን በሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋችነት ሙያው በአትላስ፣ በሙኒክ እና ናዝሬት አለማየሁ እሸቴ በሚሠራበት የምሽት ክበብ እንዲሁም በተለያዩ የምሽት ቤቶች ውስጥ ሠርቷል::
በሙዚቃ እና በቲያትር የተለያዩ የሙያ የምስክር ወረቀቶችን ያገኘው እንግዳችን ከሙዚቃ በተጨማሪ የሥዕል እና የቲያትር ባለሙያ እንደሆነም በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይቷል፤ በተለይም በድራማ ሥራዎች ላይ ሙሉ ጊዜውን ማሳለፍ እንደጀመረ “ጐጆ መውጫ” የተሰኘውን ድራማ በ1989 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሕዝብ ሲያቀርብ ከፍተኛ እውቅናን አግኝቶበታል::
ከጐጆ መውጫ ቀጥሎ ትሁኔ /ቲያትር/፣ ከንፈር ወዳጅ /ፊልም/፣ ብራ /ፊልም/፣ የካብ ሀረግ /የሬዲዮ ድራማ/፣ መስታዎት፣ ፍለጋ እና የተለያዩ ድራማዎችን በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለተመልካቾች አድርሷል:: ከአንድ መቶ ሀምሳ የሚበልጡ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድራማዎችንም ለሕዝብ አድርሷል:: ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በምናቡ ከበደ ማስታወቂያ እና ፕሮሞሽን ድርጅትን ከፍቶ በኪነ ጥበቡ ዓለም ውስጥ ቆይታ አድርጓል::
ከአንጋፋው የኪነ ጥበብ ባለሙያ እና ተዋናይ በምናቡ ከበደ ጋር የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎቹን በተመለከተ ቆይታ አድርገናል::
መልካም ንባብ!
ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም እንዴት ገባህ?
የኪነ ጥበቡን ዓለም በተጨባጭ የተቀላቀልኩት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የኪቦርድ ተጫዋች ሆኜ ቢሆንም ተወልጄ ባደኩባት የደሴ ከተማ ውስጥም የገጠር ሰዎችን አነጋገር በማስመሰል እናገር ነበር:: በዚህም በውስጤ የኪነ ጥበብ ፍላጐት እንደነበረኝ እርግጠኝ ነበርኩ:: በአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር እኔ ኪቦርድ በምጫወትበት ጊዜ ማዲንጐ አፈ ወርቅ /ነብሱን ይማረውና/ ይዘፍን ነበር:: ብዙም ባላስቀጥለውም በክፍለ ጦሩ ውስጥ እያለሁ ሥዕሎችንም እስል ነበር፤ የቲያትር ሙያንም የጀመርኩት በዚያው በክፍለ ጦሩ ውስጥ እያለሁ በመሆኑ በአብዛኛው የኪነ ጥበብ ዓለምን የተቀላቀልኩት ወታደር ሆኜ ነው ማለት ይቻላል::
ምንም እንኳን ኪነ ጥበብን በውትድርና ቤት እያለሁ ብጀምርም ይበልጥ ያሳደኳት እና በግሌም ታዋቂነትን ያገኘሁት ግን ከውትድርና ከለቀቅኩ በኋላ ነው:: አሁን ላይ ከኪነ ጥበብ ጋር መተዋወቅ ብቻ ሳይሆን የ80 ውል ፈጽመን ህልሜን የምመራበት እና ቤተሰቤን የማስተዳድርባት ሙያዬ አድርጌያት ቀጥያለሁ:: በነገራችን ላይ የራሴ ድርሰት እና ዝግጅት ከሆኑት ተከታታይ ድራማዎች እና ፊልሞች በተጨማሪ በተለያዩ ደራሲዎች ሥራዎች ላይም በትወና ተሳትፌያለሁ::
የኪነ ጥበብ ሙያን ከገቢ አንፃር እንዴት አገኘኽው?
ኪነ ጥበብ እንደሙያ የሚያስገኘው ገቢ በጣም አነስተኛ ነው:: ብዙ ከያኒዎች እንደሚሉት እና እኔም እንደምጋራው ከኪነ ጥበብ የሰዎችን አድናቆት እንጂ በቂ ክፍያ ማግኘት አይቻልም፤ ያም ቢሆን ግን ለሙያው መጠራትን ስለሚፈልግ አብዛኞቻችን ከያኒያን ከምናገኘው ገንዘብ ይልቅ ለሙያው ፍቅር እንደምንሠራ እርግጠኛ ሆኜ እነግርሀለሁ:: ያ ማለት ግን ኪነ ጥበብ ምንም ገንዘብ የማያስገኝ ሙያ ነው እያልኩም አይደለም::
እዚህ ላይ እንደ አብነት የማነሳልህ እኔ ጐጆ መውጫን ስጽፍ ለድርሰት አንድ ሺህ ብር፣ ለትወና ደግሞ አንድ ሺህ 500 ብር ብቻ ነው የተከፈለኝ:: ያን የገጠር ድራማ ያዩ እና የወደዱት ሰዎች እኔ ከዚያ ድራማ ያገኘሁት 2 ሺህ 500 ብር ብቻ መሆኑን ቢያውቁ መገረማቸው አይቀርም::
ጐጆ መውጫን ሠርቼ ከተከፈለኝ ገንዘብ ይልቅ በጐጆ መውጫ ያገኘሁት እውቅና እና ዝና ለኔ በኪነ ጥበብ ውስጥ መቀጠል ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው:: አሁን ላይ ከጐጆ መውጫ አንስቶ ባገኘሁት እውቅና እና ከፍተኛ የሙያ ልምድ የተነሳ የተለያዩ የቴሌቪዥን ድራማዎችን፣ ፊልሞችን፣ ማስታወቂያዎችን እና ሌሎች ሥራዎችንም ለመሥራት በቅቻለሁ፤ በትንሽ ክፍያ የጀመረው የሕይወት ጉዞዬም በምፈልገው መስመር እየሄደልኝ ነው::
“ጐጆ መውጫ” ድራማ እንዴት እና በምን ምክንያት ተሠራ?
ወደ ትላልቅ ገበያዎች ስንሄድ የተለያዩ የገበያ ተራዎች እንዳሉት ሁሉ ኪነ ጥበብም ልክ እንደገበያው ሁሉ የተለያዩ ዘውጐች ያሏት ናት:: አንዳንድ ሰዎች ተፈጥሮ በጣም ስለምትማርካቸው የሚያዩዋቸው ፊልሞችም ሆኑ ድራማዎች ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ቢሆኑ ደስ ይላቸዋል:: አንዳንዶች ደግሞ ለአስፈሪ ፊልሞች ቅድሚያ ይሰጣሉ:: የፍቅር ታሪኮች የሚመስጧቸው ሰዎች የመኖራቸውን ያህል በጦርነት ፊልሞች የሚዝናኑም ብዙዎች ናቸው:: ቴክኖሎጂ እና ከተሜነት ምርጫቸው የሆኑ ሰዎች ያሉትን ያህል ገጠር እና የገጠር ሕይወት የሚስባቸው ሰዎችም ብዙ ናቸው፤ እኔ ደግሞ ከነዚሁ የገጠር አድናቂዎች ውስጥ አንዱ ነኝ::
በኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች ብዙ እሴቶች ቢኖሩም በበቂ መልኩ በፊልም ፣ በቲያትር እና በድራማ ተሠርተዋል ወይም ተንፀባርቀዋል ብዬ አላምንም:: ጐጆ መውጫ ድራማን እነ አብዬ ይመርን፣ ዘሙን እና ሊበንን ይዞ ስለገጠሩ ሕይወት፣ ስለ መሬት፣ ስለ ፍቅር እና ስለሌሎችም ነገሮች እንዲያሳይ ለማድረግ ሞክሬበታለሁ:: የገጠርኛ ዘውጐች በጣም ስለሚስቡኝ ከዚያ ውስጥ መውጣት አልቻልኩም:: ከዚያ በኋላ የሠራኋቸው ብራ፣ ፍለጋ እና የካብ ሀረግም የሚያጠነጥኑት በገጠር ታሪክ ላይ ነው::
ብዙ የሀገር ውስጥ ፊልሞቻችን እና ድራማዎቻችን የሚያተኩሩት በከተማ ውስጥ ታሪክ ላይ በመሆኑ እኔ ደግሞ ፊቴን ወደ ገጠሩ አዙሬያለሁ:: የኔ ሥራዎች መቼታቸው /መቼ እና የት?/ ገጠር ላይ ለማተኮሩ ምክንያቱ የኔም ፍላጐት ገጠርኛ በመሆኑ ነው:: ገጠር ውስጥ ያሉ እሴቶቻችን ገና ምንም ያልተነኩ ናቸው:: የኢትዮጵያዊያንን ደግነት እና ሩህሩህነት የምታገኘው ገጠር ውስጥ እንጂ ከተማ ውስጥ አይደለም::
እንግዳን ቤት የእግዚያብሔር ነው ብሎ መቀበል፣ እግር ማጠብ፣ አልጋ መልቀቅ እና የመሳሰሉትን እውነተኛ ደግነቶች ገጠር ውስጥ እንጂ ከተማ ወስጥ ማግኘት አይቻልም:: የገጠሩ ማኅበረሰብ ያሉት መልካም እሴቶች እየተበረዙ ያሉት በከተሜነት አስተሳሰብ ነው:: በብዙ ነገሮቿ ትወደስ የነበረችውን ኢትዮጵያን እውነተኛ ሥዕል ማግኘት የሚቻለው ገጠር ውስጥ ነው:: የጐጆ መውጫም ሆነ የሌሎቹ ድራማዎቼ ትኳሬ ገጠር ላይ የመሆኑ ምክንያትም ይሄው ነው::
የገጠሩን ማኅበረሰብ ታሪክ ለመዳሰስ ምክንያት ይኖርህ ይሆን?
እኔ ተወልጄ ያደኩት ደሴ መሀል ከተማ ውስጥ ነው:: ደሴ አውቶቡስ ተራ እና በኋላም ዳውዶ የሚባል አካባቢ ሳድግ ስለ ገጠርም ሆነ ስለ ገጠሩ ማኅበረሰብ የማውቀው ነገር አልነበረኝም፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን ጐረቤቶቻችን የወረሂመኑ ሰዎች ናቸው፤ የእነሱ የአነጋገር ዘዬ በጣም ይስበኝ ነበር፤ ከጐረቤቶቻችን በተጨማሪ ወደ ደሴ ከሚመጡ የገጠር ሰዎች የምሰማውን የአነጋገር ዘዬ በጣም የምወደው እና በቶሎም አጥንቼ የያዝኩት ነው:: የገጠር ሰዎች አለባበሳቸው፤ አነጋገራቸው አመጋገባቸውም ሆነ ሁሉ ነገራቸው ለኔ በጣም የሚስበኝ ነገር ነው::
በደሴ ከተማ ሰዎች መሀል አድጌ ከተሜነት ሊማርከኝ አይችልም:: እኔ ከ10 ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ ጐፈሬ እና አንዱ ብቻ መላጣ ቢሆኑ ትኩረቴን የሚስበው መላጣው ነው:: ይሄንኑ አስተሳሰቤን ወደ ኪነ ጥበቡ ሳመጣውም ብዙዎቹ ስለሚሠሩበት ከተሜነት ከምሠራ ይልቅ በገጠሩ ላይ ሳተኩር ውስጤን ደስታ ይሰማዋል:: ለዛ ነው አብዛኛዎቹ የኔ ሥራዎች ገጠር ተኮር የሆኑት::
የገጠሩን ማኅበረሰብ በድራማም ሆነ በፊልም ለመግለጽ ኪነ ጥበብ መልካም አጋጣሚን ትፈጥራለች:: እኔ ከላይ እንደገለጽኩት በገጠር ውበት የምሳብ ብቻ ሳልሆን የአረንጓዴ ልማት ከሚማርካቸው ሰዎች ውስጥም አንዱ ነኝ:: ክፋት፣ ተንኮል፣ ዘረኝነት፣ ተረኝነት እና ሌሎችም ነገሮች በአእምሯቸው እና በልባቸው ስለሌለው የገጠር ሰዎች ፊልም እና ድራማ መሥራት ብቻ ሳይሆን ስለእነሱ ማውራት በራሱ ለአፍህ ምቾት ይሰጣል:: እኔ ለወደፊቱም በዚሁ ዘውግ ላይ አተኩሬ ለመሥራት ነው እቅዴ::
የውጭ ፊልሞች እና ድራማዎች በሀገራችን ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ ምን ተጽእኖ አሳድረዋል?
ይቀጥላል
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም