ጉና የባሕል ቡድን

0
108

ደሳለኝ አበበ ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ በእጅጉ  ይወድ እንደነበር ከበኩር ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ አስረድቷል። ከልቡ የሚወደውን ሙዚቃ ከልጅነት ጊዜው ጀምሮ በሰፈር ያንጎራጉር እንደነበር ያስታውሳል። ከዚያም የሚወደውን የሙዚቃ ሥራ ለማዳበር በደብረታቦር ከተማ በሚገኘው ጉና የባሕል፣ ሙዚቃ እና ቲያትር ቡድን ተወዳድሮ በማለፍ ለሦስት ዓመታት ያህል በድምጻዊነት ሠርቷል።

ይህ የሙዚቃ ቡድን ያለኝን የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳወጣ፣ ልምድ እንዳካብት እና እንድጠነክር አድርጎኛል ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በጎንደር፣ በወሎ እና በመቀሌ ተዘዋውሮ ሥራዎቹን ሠርቷል። አሁን ላይ  በአዲስ አበባ የሙዚቃ ሥራዎቹን እየሠራ ይገኛል። ባሕላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃዎችን እንደሚጫወት የተናገረው ድምፃዊ ደሳለኝ በፋና ላምሮት የሙዚቃ ውድድር የአሸናፊዎች አሸናፊ በመሆንም ተመርጦ እንደነበር ተናግሯል።   ባለድምፀ መረዋው ደሳለኝ “ስማ በለው” እና “አዬ ፖለቲካ” የተሰኙ ነጠላ የሙዚቃ ሥራዎችንም ለሕዝብ አድርሷል። ወደፊትም ሀገርን እና ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ የሙዚቃ ሥራዎችን ለማበርከት ማዕቀዱን ነው የነገረን።

ሌላው በጉና የባሕል፣ ሙዚቃ እና ቲያትር ቡድን እየሠራ የሚገኘው ወጣት ያብባል ምስጋናው ደግሞ የሙዚቃ ቡድኑን ከተቀላቀለ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አስቆጥሯል።

በሙዚቃ  የአካባቢውን ወግ፣ ባሕል፣ እሴት እና የአኗኗር ዘይቤ ጎልቶ እንዲወጣ በትጋት እየሠራ የሚገኝ እንቁ ወጣት ነው። ሙዚቃ ማኅበረሰቡን የምታነቃበት፣የምታስተምርበት እና መልዕክት የምታስተላልፍበት አንዱ መሳሪያ ነው ብሏል። ወጣት ያብባል የፋሲል ደሞዝ፣ የደረጀ ደገፋው፣ የሀብተሚካኤል ደምሴን፣ የቴዎድሮስ ታደሰን፣ የጋሽ ጥላሁን ገሰሰን፣ የአበበ ተካን እና የቴዎድሮስ ካሳሁን ሙዚቃን በብዛት ወዷቸው የሚያዜማቸው ናቸው። በኢትዮጵያ በሚዘጋጁ የ“ታለንት ሾው” ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አሸናፊ በመሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ወክሎ መውጣት የወደፊት ምኞቱ ነው። በብሔራዊ ቲያትር በወጣው ቅጥር አልፎ እስኪጠራ እየተጠባበቀ ይገኛል። የሙዚቃ ቡድኑ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ መስክሯል።

ነገር ግን አሁን ያለው የክልሉ የሰላም እጦት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እጅግ አዳጋች ነው ብሎታል። ባሕል ቡድኑ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አመላክቷል። በባህል ቡድኑ “ብዙ ነገር ተምሬአለሁ ባለውለታየም ነው” ሲል አመስግኗል።

ድምፃዊት የስይት ዓለምነው  ሐሳቧን ያጋራችን የዚሁ የሙዚቃ ቡድን አባል ናት። በትምህርት ቤት ክበባት ሙዚቃ መጫዎት የጀመረችው ወጣት የስይት አሁን ላይ  ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን እንደምትጫዎት ነግራናለች።

ለአብነትም የፍቅር አዲስ ነቃጥበብን፣ የሐመልማል አባተን፣ የአምሳል ምትኬን እና ሌሎች የሙዚቃ ሥራዎችን ታዜማለች። የሙዚቃ ቡድኑን ከተቀላቀለች ዐሥር ዓመታትን ያስቆጠረችው ድምፃዊቷ የጥቅማጥቅም እና የክፍያ ማነስ፣ ዘመኑን የሚመጥን ግብዓት አለመሟላት (ሞንታርቦ፣ ማይክ፣ የባሕል አልባሳት)  እና መሰል ግብዓቶች በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠሩባቸው ነግራናለች።

እነዚህ ግብዓቶች ከተስተካከሉ እና ጥቅማቸው ከተከበረ አመርቂ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ነግራናለች። ወደፊት ክልላዊ እና ሀገራዊ ሙዚቃዎችን በማውጣት ለሕዝብ ለማበርከት ተዘጋጅታለች። እነዚህ እንቁ ወጣት ድምፃውያን   ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም በድምቀት ለተከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ድምቀት ሆነው ተመልክተናል። የጉና የባህል፣ ሙዚቃ እና ቲያትር ቡድን በአማራ ክልል በኪነ ጥበብ ዘርፉ በተለይም በባሕላዊ ውዝዋዜ እና ሙዚቃ ላይ ስማቸው ከሚጠሩ የባሕል ቡድኖች ውስጥ አንዱ መሆኑን የነገረን ደግሞ የቡድኑ አስተባባሪ እና የመድረክ አስተዋዋቂው ቴዎድሮስ ካሳሁን ነው። በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችንም ለሀገር አበርክቷል ነው ያለው።

ብዙዎች ጥበብን ፍለጋ ብለው ገብተው ለህይወታቸው መሠረት እንደጣለላቸው የቡድኑ አስተባባሪ ለበኩር ጋዜጣ ተናግሯል። አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገረው የባሕል ቡድኑ ከኪነ ጥበብ ሥራዎቹ ባሻገር በልማት እና በማሕበራዊ ሥራዎችም ተሳትፎ በማድረግ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ነው። በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት እና የሰላም እጦት የሚያስከትለውን ቀውስ በተመለከተም በትኩረት እንደሚሠሩም አስረድቷል። በዚህ ወቅት በሚያገኙት መድረክ ሁሉ ቅድሚያ የሰላም ሙዚቃዎችን እና ቲያትሮችን እንደሚያዘጋጁ አስረድቷል።

በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሰላም መልዕክቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዬች ናቸው ብሏል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የብሔር ብሔረሰቦችን በሥራዎቻቸው ለተመልካቹ  ያሳያሉ። በቲያትር ማህበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮችን የሚያንፀባርቁ አጫጭር ድራማዎችን እና ትዕይንቶችን እንደሚዘጋጁም ተናግሯል።  በዓለም አቀፍ  የሙዚቃ እና ቲያትር በተዘጋጀው መድረክ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ማሊዥያ አቅንተው የሀገራቸውን ባሕል እና ወግ አስተዋውቀዋል።  በቀጣይም የባሕል ቡድኑን ወደ ባሕል ማዕከል ለማሳደግ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሷል። የባህል ቡድኑ በጌምድርን አቃፊ እንዲሆን እና ራሱን ችሎ ቋሚ ገቢ እንዲያመነጭ እና ሌሎችንም ወደ ሙያው እንዲገቡ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገረው። አባላቱንም አሁን ካለበት ቁጥር ከፍ ለማድረግ

ጥረት እየተደረገ ነው። አፀደማሪያም ያረጋል፣ ደሳለኝ አበበ፣ ሄኖክ ጥጋቡ፣ ሄኖክ አበበ፣ የቆየ ምህረት፣ ግርማ ሞገስ፣ ኤፍሬም መልካሙ እና ሌሌች የጥበብ ሰዎች ከዚህ የባሕል፣ ሙዚቃ እና የቲያትር ቡድን የፈለቁ የዘመኑ የጥበብ ሰዎች እንደሆኑም በአብነት ጠቅሷል። በግብዓት እና በተለያዩ ቁሳቁስ እጥረት እየተፈተነ የሚገኘውን የባሕል ቡድን የተሻለ ሥራ ሠርቶ እንዲታይ ደግሞ የሁሉንም ድጋፍ ይሻል ብሏል የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ።

የጉና የባሕል ቡድን በኪነ ጥበብ ዘርፉ እያበረከተው ያለውን አስተዋፅኦ፣ አሁን ላይ ያለበት ደረጃ እና ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ታደሰ ቢያድጌ ናቸው። ይህ ባሕል ቡድን በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ በውዝዋዜ፣ በድምፅ እና በቲያትር አዘጋጅነት ግንባር ቀደም መሆኑን አመላክተዋል። የጉና የባሕል፣ ሙዚቃ እና ቲያትር ቡድን ሕዳር 11 ቀን 2003  ዓ.ም ሥራውን እንደጀመረ አስረድተዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የአካባቢውን ወግ፣ እሴት፣ ታሪክ እና ቱባ ባሕሉን በጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል ሲያገለግል የቆየ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ 10 ተወዛዋዦች፣ አምስት ድምፃዊያን፣ አምስት የሙዚቃ ተጫዎች እና ሁለት ድርሰት አዘጋጅ በአጠቃላይ 22 አባላት እንዳሉት ገልጿል። የጉና የባህል ቡድን የጎንደርን ብሎም የክልሉን እሴቶች፣ ባሕሉን፣ የአኗኗር ዘይቤውን፣ አለባብሱን እና ሌሎች የማኅበረሰቡ ወግ ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እያስተዋወቀ ይገኛልም ብሏል። ኢትዮጵያ ያላትን ዘርፈ ብዙ ማንነት በመድረክ ላይ በጥበብ እየገለጠም ይገኛል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ለሰላም መስፈን በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው እያቀረቡ ይገኛሉ። አቶ ታደሰ እንደተናገሩት የበጌምድርን ታሪክ በሚገባ ለማስተዋወቅ እና የባሕል ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በደብረታቦር ከተማ ሰፊ የባሕል ማዕከል እየተገነባ ነው ብለዋል። ይህም ጥበብን ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድቷል።

ለባሕል ቡድኑ ሥራ የሚያግዙ የቁሳቁስ እጥረት መኖሩን ሐሳቡን የተጋሩት አቶ ታደሰ ግብዓቶች ዘመኑን የሚመጥኑ እንዲሆኑ ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ ነው። ብቁ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለማፍራት ባሕል ቡድኑን መደገፍ ይጠበቃልም ብለዋል። በተለይም የአባላቱ ጥቅማ ጥቅም መከበር እና ግብዓት መሟላት ለሥራቸው ውጤታማነት ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። ስለሆነም ከደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር፣ ከደብረታቦር ከተማ እና ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የስምምነት ሰነድ ተደርጎ የቡድኑን ልጆች ለመደገፍ፣ ለማሳደግ እና ለመጥቀም ጥረት እየተደረገ ነው። አጫጭር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተጠቃሚ እንዲሆኑም መምሪያው እየሠራ ነው። ሆኖም ብዙ ርቀት መሄድ እንዳለበት አመላክተዋል። ለባሕል ትክክለኛነት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የጉና የባሕል ቡድን የኢትዮጵያን ባሕል ለማስተዋወቅ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ትዕይንቶችን አቅርቧል። ይህም የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው አድርጎታል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here