ጉዞ ወደ በረሃማዋ ንግሥት …

0
210

መነሻዬ አዲስ አበባ ነው።  ጎህ ሲቀድ ጓዜን ሸክፌ አውቶብስ ተራ ደረስኩ። እንደ ሁልጊዜው አውቶብስ ተራው በወያላ ጩኸት መናወጡን ቀጥሏል::

“ሐረር! ድሬደዋ! ሐረር! ድሬደዋ! ወደዚህ!” አለ ሰማያዊ ኮት የለበሰ ደንብ አስከባሪ። ከኋላ ኪሴ የተጨማደደች ትኬቴን አውጥቼ እያሳየሁ  ወደ ወንበሬ አመራሁ።

ብዙም ሳይቆይ ሁሉም ተጓዥ መግባቱ ተረጋግጦ ጉዞ ጀመርን። ወዲያውኑ  አንግቴ ወደ አንድ በኩል ዘንበል እንዳለ እንቅልፍ አሸለበኝ። ረፋድ ላይ ግን በመስኮት የገባችው ፀሐይ  ከእንቅልፍ አነቃችኝ።

“ናዝሬት ደርሰናል” አለ ጎርነን ባለ  ድምፅ በቀኝ በኩል እጐኔ የተቀመጠ ሰው። ቀና ብዬ ዙሪያዬን ስማትር “የደከመህ ትመስላለህ” አለ፤ አሁንም ያው ድምጽ ። እህህ ብዬ ድምፄን ከሳልኩ በኋላ፣ እዎ ትላንትም ስጓዝ ነው የዋልሁ።  በቂ እንቅልፍ ስላልተኛሁ ለዛ ነው ትንሽ የተጫጫነኝ። “ተማሪ ነህ?”…አዎ ተማሪ ነኝ። “ገምቻለኁ” አለ ጭንቅላቱን እላይ ታች እየወዘወዘ:: “የት ዩንቨርስቲ”? የባህር ዳር ዩንቨርስቲ ተማሪ ነኝ። “ሳንተዋወቅ በጥያቄ አጣደፍኩህ፤ እይ የኔ ነገር፤ መምህር ጥጋቡ እባላለሁ”  ኢዮብ እባላለሁ በማለት መለስኩለት ።

መምህር ጥጋቡ መካከለኛ ተክለ ሰውነት ያለው፣አርባዎቹን ያጋመሰ ጐልማሳ ነው። እንደ በረሃ ቋጥኝ ተራርቀው የበቀሉ ፀጉሮቹ፤ በቅርቡ መመለጡ አይቀሬ መሆኑን ቀድመው ያበሰሩ ይመስላል። ቁልጭልጭ አይኖቹ፣ጮሌና ቀዥቃዣ ቢያስመስሉትም፣ ቀርቦ ላየው ሰው ረጋ ያለ  ጨዋታ አዋቂ ነው።

መምህር ጥጋቡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጂዎሎጂ አስተማሪ ሲሆን የ12ኛ ክፍል የብሄራዊ ፈተና ለመፈተን ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ .እንደሚሄድ ገልፆልኝ እረፋድ ላይ መተሓራ ቁርስ ተመገብን። በመምህር ጥጋቡ ሙያዊ ትንታኔ የምስራቅ ሸዋን መልከዓ ምድር እያደነቅን፣ ሜዳማውን እና ሞቃታማውን የአዋሽ በረሓ ተያያዝነው።

አዋሽ የከረዩ እና የአፋር ማህበረሰብ ተጐራብተው እሚኖሩባት፤ በውስጧም  የእንስሳት ማቆያ ብህራዊ ፓርክ እና የወታደራዊ ትምህርት ቤት እሚገኙባት ሞቃታማ ከተማ ናት።

ቀትር ላይ በረሓማውን የስምጥ ሸለቆ ክፍል አገባደን ባርደዴን ፣ሚኤሳን አልፈን የምዕራብ ሐረርጌ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አሰበ ከተማ ደረስን::

አሰበ  ወይና ደጋማ የአየር ፀባይ ያላት፣ በተራሮች የተከበበች ብዙም ሰፊ ያልሆነች፣ ጠባብም እማትባል መጠነኛ ከተማ ነች። በውስጧም የኦዳቡልቱምን ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ፤ አንድ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተጠሪነቱ ለሓሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሆነ የግብርና ምርምር ማዕከል መገኛ ነች።

የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ እኩሌታ በመሆኗ ከድሬ የሚመጣው ለቁርስ፤ ከሸገር የሚመጣው ለምሳ፤ አሰበን መጐብኘት ግድ ነው።

በከተማዋ በርከት ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ። በተለይ የጫት ንግድ በስፋት ይካሄድባታል:: በተጓዳኝም  የኮንትሮባንድ መዳረሻ ናት:: አንድ ላይ ተዳምረው የድምቀት ፀዳል እንድትጐናፅፍ አስችለዋታል።

ከመምህር ጥጋቡ ጋር የስንብት ምሳችንን በልተን፤ ስልክ ተቀያይረን፤ የጉዞዬ መዳረሻ ወደ  ሆነችው ድሬ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ሂርናን፣ ቦሮዳን፣ ጨለንቆን አልፌ ቁልቢ ደረስኩ።

ውድ  አንባቢያን፣ አሁን ድሬ ልንደርስ ነው! እስቲ ቁልቢ ላይ ጥቂት አረፍ እንበል።

ቁልቢ ከድሬደዋ 48  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ፤ በከፍታ ላይ የተቆረቆረች ጥንታዊ ከተማ ናት። ታሪኳ ከራሷ ስለሚገዝፍ የከተማነት መዓረግን አንንፈጋት ብዬ እንጂ ከተማ ለማለት ይቸግረኛል፤ መንደር ለማለትም ይከብዳል። የከተማነት ወግ ወጉን የያዘች  ብል ይቀለኛል።

ቁልቢ በዓመት ሁለት ጊዜ ታህሳስ 19 እና ሃምሌ 19  እሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ገዳም መገኛ፤ የእውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ እንዲሁም የቀድሞው የሐረር ሬድዮ ጣቢያ ባልደረባ እና የዶቼቬሌ ሪፖርተሩ ጋዜጠኛ ጃፈር አሊ የትውልድ ስፍራ ነች።

እንግዲህ የቁልቢ ገብርኤልን ታሪክ በአካል አሊያም በዝና እማያውቅ አለ ለማለት ይከብዳል።

ቀጠልኩ … መዳረሻዬ  ወደ ሆነችው የበረሃዋ ንግሥት ድሬዳዋ:: አሁን ቁልቢን አልፌ፣ ላንጌይን፣ ቀርሳን አልፌ የደጋማው አየር ንብረት ማብቂያ፤ የድሬዳዋ እና የሓረር መስመር እሚለያዩበት ደንገጐ ደረስኩ።

ደንገጐ ላይ ሁለት መንገዶች አሉ:: አንደኛው በቀጥታ ወደ ሐረር የሚወስደው ነው:: ወደ ግራ የሚታጠፈው ደግሞ የድሬ መስመር ነው።

የደንገጐ መንደር ሰዎች ይኖሩበታል ለማለት ይከብዳል:: በጣት የሚቆጠሩ ቤቶች፣ አንድ አገልግሎት ከሰጠ በጣም የቆየ የሚመስል ዙሪያው በሳር እና አረም የተከበበ ማደያ እንዲሁም ለምን አላማ እንደተሰራ ለመገመት የሚከብድ ባረጁ ኮንቴነሮች የተሞላ ባዶ ግቢ፣ አልፎ አልፎ፣ ብርቱካን፣  ጊሽጣ በሰፌድ የያዙ ልጃገረዶች ውርውር ከማለታቸው በቀር ምንም የሌለባት መንደር ነች።

የሐረሩን መስመር ወደ ግራ ትተን ጠመዝማዛውን የደንገጐ ቁልቁለት ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እየተናጥን ጉዞ ቀጠልን።

የደንገጐ ሰንስለታማ ተራሮች ተኮፍሰው ድሬደዋን ቁልቁል ሲያዩዋት በተራሮች የተከበበች ከተማ መሆኗን መገመት ይቻላል።

ቢርካንና ሻዪ አሰፍን አልፈን ሀሪላ ደረስን። ሀሪላ ከታሪክ መፅሐፍ ውጭ ዓለም የዘነጋት ከድሬ መቆርቆር በፊት የነበረች ታሪክ ሆና የቀረች የጐስቋሎች መንደር ናት።

ሀሪላ በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ ከሆኑ ጥቂት ስፍራዎች አንዷ ነች። ስያሜዋም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው:: ሀሪላ ማለት በአካባቢው ስያሜ “ግዙፍ” ማለት ነው። እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሰዎች መኖሪያ የነበረች፣ብዙም ያልተባለላት  መንደር ሀሪላ…. ህዝቧ  የኑሮን ውጣ ውረድ መጋፈጥ ግድ ሆኖቧቸው ህይወትን ለማስቀጠል ከተፈጥሮ ጋር ግብ ግብ የገጠሙ  ይመስላል።

ገነት መናፈሻን አለፍኩ፤ ናሽናል ሲሚንትን፣ሶስት ኪሎ የተባለውን በቅርቡ የተመሰረተ ሰፈር አልፌ ምሽት ላይ ድሬ ገባሁ።

ድሬ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት… ተምሳሌት የሆነች ከተማ። የበረሃዋ ንግሥት ድሬደዋ ላይ  ጉዞዬን  ቋጨሁ።

ድሬደዋ ከአዲስ አበባ 515 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ስትገኝ፣ ከጅቡቲ 318 ኪሎ ሜትር ርቃ በምስራቅ የሱማሌ ክልል፣ በሰሜን የኦሮሚያ ክልል ያዋስኗታል። የተለያዩ ብሄሮች ተሳስበው ይኖሩባታል::

ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለተኛዋ  ራስ ገዝ ከተማ ናት። ህዝቧ ቀለል ያለ ኑሮን የሚመርጥ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ተግባቢ ለቸገረው ደራሽ፣ “አብሽሩ እና ሃዬ” ከአፉ እማይጠፉ ገራገር እሚባል አይነት ነው።

ድሬደዋ የኢትዮጵያዊያን  ብቻ ሳትሆን የሌሎችም አገራት ዜጐች ኖረውባታል። ለአብነትም ግሪኮች፣ ፈረንሳይ፣ ኩባ፣ አርመኖች፣ አረቦች ተጠቃሽ ናቸው።

ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች መገኛ እንዲሁም በቅርቡ ተጠናቆ ወድ ስራ የገባው ከቀረጥ  ነፃ የሆነው የደረቅ ወደብ መገኛ ነች። የኔም የጉዞ ቅኝት በዚሁ ተቋጨ፤ ቸር ይግጠመን!

(ኢዮብ  ሰይፉ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here