ጉዳት ያከሸፋቸዉ

0
148

የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

እግር ኳስ የንክኪ ስፖርት በመሆኑ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ ሲጎዱ ማየት የተለመደ ነው። ምንም እንኳን ተጫዋቾች ከጉዳት ለመራቅ በተቻላቸው መጠን ጥረት ቢያደርጉም አሁንም ግን ከችግሩ ማምለጥ አልቻሉም። የህክምና ሳይንሱ እጅግ በዘመነበት በዚህ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከሚወዱት ሙያ ጋር እየተለያዩ መሆኑን ዋን ፕላኔት የተባለ ድረገጽ አስነብቧል። ባለሙያዎችም ችግሩ ምን ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ። በዘመናዊ እግር ኳስ ተጫዋች በአንድ የውድድር ዘመን የሊግ እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ ብዙ መርሀ ግብሮችን ያከናውናሉ። ታዲያ የማገገሚያ እና የእረፍት ቀናቶች ማጠራቸው ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉ ነው የተዘገበው።
አንዳንድ ተጫዋቾች ለጉዳት ቅርብ የሆኑ እና በቀላሉ ሰውነታቸው ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከጉዳት ነጻ ሆነው የውድድር ዘመኑን የሚያጠናቅቁ እንዳሉ መረጃው ያስነብባል። ለአብነት የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ቡሩኖ ፈርናንዴዝ ኦልትራፎርድ ከደረሰ በኋላ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ጉዳት የገጠመው። ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ የባርሴሎናው አጥቂ ሮበርት ሎዋንዶስኪ፣ የሊቨርፑሉ ኮከብ ሞሀመድ ሳላህ፣ የባየር ሙኒኩ የፊት መስመር ተሰላፊ ቶማስ ሙለር እና የመሳሰሉት ራሳቸውን ከጉዳት ጠብቀው በዓለም እግር ኳስ አንጸባርቀዋል፤ እያንጸባረቁም ይገኛሉ።
ብራዚላዊው ባለተሰጥኦ ኔይማር ጁኔዪር የሊዮኔል ሜሲ እና የሮናልዶ ዙፋንን ይረከባል የሚል ትልቅ ግምት ተሰጥቶት እንደነበር አይዘነጋም። ኔይማር ጁኔር በትውልዱ ካሉ የላቀ ተሰጥኦ እንዳለው ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ይሁን እንጂ ትኩረቱን እግር ኳስ ላይ ባለማድረጉ እና የበዛ ዳንኪራ መውደዱ የእግር ኳስ ህይወቱ እንዲከሽፍ አድርጎታል። በእንቅርት ላይ… እንዲሉ በተደጋጋሚ ያጋጠመው ጉዳትም አቅሙን አውጥቶ እንዳይጠቀም እንቅፋት ሆኖታል።
ኔይማር ጁኔዪር በ2023 እ.አ.አ ነበር የፈረንሳዩን ሀብታም ክለብ ፓሪሰን ጀርሜንን በመልቀቅ ወደ ሳውዲ አረቢያ ያቀናው። ባለተሰጥኦው ብራዚላዊ ምንም እንኳ በሳውዲው ክለብ አል ሂላል ቤት በቀን 478 ሺህ ፓውንድ ደሞዝ እየተከፈለው ቢሆንም ለክለቡ ግን እስካሁን ይህን ነው የሚባል ግልጋሎት አልሰጠም። ለአል ሂላል በአጠቃላይ ሰባት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያደረገው። ኔይማር በ2023 ለሀገሩ ብራዚል ሲጫወት የጉልበት ጉዳት ገጥሞት ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቷል። አገግሞ በቅርቡ ወደ ሜዳ ቢመለስም ድጋሚ ተጨማሪ ጉዳት ገጥሞታል። ታዲያ ክለቡም በጥር ወር ውሉን ሊያቋርጥ እንደሚችል ተዘግቧል:: እንደ ዘ ጋርዲያን መረጃ እድለኛ ካልሆኑት ተጫዋቾች ተርታ እንደሚሰለፍ መረጃው ያስነብባል።
በተመሳሳይ የ2024ቱን የባሎን ዶር ሽልማት ያሸነፈው ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲው አማካይ ሮድሪጎ ሄርናንዴዝም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአምስተኛ ሳምንት ከአርሴናል ጋር በነበረው መርሀ ግብር መጎዳቱ አይዘነጋም። አማካዩ እስከ ውድድር ዓመቱ ከሜዳ እንደሚርቅም ዘ ጋርዲያን አስነብቧል።
ፈረንሳያዊው የቀድሞው የአርሴናሉ አማካይ አቡ ዲያቢ በማጥቃት እና በመከላካል የተካነ፣ ከሳጥን ሳጥን በመሮጥ የሚታወቅ አይደክሜ ተጫዋች እንደነበር ብዙዎች ያስታውሱታል። ደጋፊዎችም ከሌላኛው ፈረንሳያዊ ከቀድሞው የመሀል ሜዳ ሞተር ፓትሪክ ቬዪራ ጋር ያነጻጹርት እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ የዲያቢ ስም ሲነሳ የእግር ኳስ ቤተሰቡ አብሮ የሚያስታውሰው ሜዳ ላይ የሚገጥመውን ጉዳት ጭምር ነው። ተጫዋቹ በተደጋጋሚ ለጉዳት ተጋላጭ እና እንደ ብርጭቆ በቀላሉ ተሰባሪ መሆኑ ተፈጥሮ የሰጠችውን ተሰጥኦ ሳይጠቀም ከእግር ኳስ ጋር ተለያይቷል።
አቡ ዲያቢ በኤምሬትስ በቆየባቸው ዘጠኝ ዓመታት 124 ጨዋታዎችን አድርጓል። ከተደጋጋሚ ጉዳት በኋላ በፈረንጆች 2015 ሰሜን ለንደንን ለቆ የሀገሩን ክለብ ማርሴን ቢቀላቀልም ለፈረንሳዩ ክለብም አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያከናወነው። ከኮትዲቫር ቤተሰቦቹ ፈረንሳይ ውስጥ የተወለደው ዲያቢ በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ አንድ ሺህ 747 (አራት ዓመት ከዘጠኝ ወራት) ቀናትን በጉዳት አሳልፏል። በእነዚህ ቀናቶች 314 ጨዋታዎች አምልጠውታል። ከጉዳት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገው ፈረንሳያዊ ክህሎቱን ሳይጠቀም በመጨረሻም ባለፈው ዓመት ይካቲት ወር ከእግር ኳስ መገለሉን ይፍ አድርጓል።
ዲያቢ በፈረንጆች 2017 ከማርሴ ጋር ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ እንደነበር አይዘነጋም። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ 198 ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያደረገው። የቀድሞው የሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች እና የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች የነበረው ስቲቫን ጆቪቲች ተደጋጋሚ ጉዳት እግር ኳስ ህይወቱን አመሰቃቅሎታል። ሞንቴኔግሮዋዊው አጥቂ አንድ ሺህ 510 ቀናትን (ከአራት ዓመታት በላይ) ከሜዳ ርቆ አሳልፏል። አጥቂው ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁለገብ እንደነበር የዋን ፕላኔት መረጃ ያመለክታል። ፊታውራሪው ጆቪቲች ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ቢፈርምም በተደጋጋሚ በገጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ክህሎቱን እንዳያሳይ አድርጎታል። ነገር ግን የ35 ዓመቱ አጥቂ አሁን ድረስ ለጉዳት እጅ አልሰጥም በማለት በቆጵሮስ አንደኛ ዲቪዚዮን ለኦሞኒያ ኒኮሲያ ክለብ እየተጫወተ ነው።
የኔዘርላንዳዊው አሪያን ሮበን እና የፈረንሳያዊው ፍራንክ ሪቤሪ ጥምረት በባቫሪያኖቹ ቤት የሚዘነጋ አይደለም። የቀድሞው የባየርሙኒኩ ኮከብ አሪያን ሮበን በዓለማችን ከታዩ ምርጥ የክንፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ሮበን በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ተጫውቶ ማሳለፉን የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። ለፒኤስቪ ኢንዶቨን፣ ቸልሲ፣ ሪያል ማድሪድ እና ባየር ሙኒክ ቤት ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። ዐስር ዓመታት ባሳለፈበት አሊያንዝ አሬና ተደጋጋሚ ጉዳት ገጥሞት ነበር። በተለይ እ.አ.አ ከ2016 እስከ 2019 ባሉት ተከታታይ ዓመታት ብዙ ጉዳት ገጥሞታል። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ ደግሞ ለአንድ ሺህ 507 ቀናት (ከአራት ዓመታት በላይ) ከሜዳ ርቋል።
ሌላው ድንቅ ተሰጥኦውን ሳይጠቀም ጉዳት በአጭር ያስቀረው የቀድሞው መድፈኛ ጃክ ዊልሻየር ነው። የቀድሞው አማካይ የላቀ ተሰጥኦ ከነበራቸው እንግሊዛውያን ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ገና በለጋ እድሜው ጉዳት ከሜዳ እንዲርቅ አስገድዶታል። በ19 ዓመቱ አስከፊ ጉዳት የደረሰበት ዊልሻየር ከዚያን ጊዜ ወዲህ ችግሩ ጸንቶበት ጫማውን ሰቅሏል። በአጠቃላይ አንድ ሺህ 470 ቀናትን (ከአራት ዓመታት በላይ) በጉዳት አሳልፏል። አሁን ላይም የአርሴናልን ወጣት ቡድን እያሰለጠነ ይገኛል።
የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲው ተከላካይ የአሁኑ የባየርሙኒክ አሰልጣኝ ቪኒሰንት ኮምፓኒ ከሦስት ዓመታት በላይ፣ የቀድሞው የአርሴናሉ ተከላካይ ቶማስ ቨርማለን ከሦስት ዓመት በላይ እና ስመ ጥሩ ብራዚላዊው ፊታውራሪ ሮናልዶ ናዛሪዮ ዴሊማ ከሁለት ዓመታት በላይ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ የራቁ ተጠቃሽ የቀድሞ ተጫዋቾች ናቸው።
ተጫዋቾች አቅማቸውን እና ክህሎታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ አመጋገባቸውን ማስተካከል፣ በቂ እረፍት ማድረግ፣ ከእድሜያቸው እና ከአቅማቸው በላይ ልምምድ እንዳይሰሩ እና እንዳይጫወቱ ማድረግ፣ ትክክለኛ የቴክኒክ እና የታክቲክ ስልጠናዎችን ብቻ እንዲወስዱ ማበረታታት ክህሎታቸውን ከማሳደጉም በላይ ጉዳቶችን እንደሚቀንስ ነው መረጃው የሚያመለክተው። ኋላ ቀር በሆነው የሀገራችን ሊግም ተጫዋቾች ከጉዳት ለመራቅ የእግር ኳሱ ዓለም የሚከተለውን ሳይንሳዊ መንገድ መረዳት እና መገንዘብ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here