ጉዳት ያደበዘዘዉ መድረክ

0
112

እግር ኳስ የንክኪ ስፖርት በመሆኑ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ ሲጎዱ ማየት የተለመደ ነው:: ምንም እንኳን ተጫዋቾች ከጉዳት ለመራቅ በተቻላቸው መጠን ጥረት ቢያደርጉም አሁንም ግን ከችግሩ  ማምለጥ አልቻሉም::

በዘመናዊ እግር ኳስ ተጫዋች በአንድ የውድድር ዘመን የሊግ እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ ብዙ መርሀ ግብሮችን  ያከናውናሉ:: በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታዲያ የመጫዎቻ እና የልምምድ ቦታዎች ምቹ አለመሆን፣ የማገገሚያ እና የእረፍት ቀናቶች ማጠራቸው  ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል::

በያዝነው የውድድር ዓመት  ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ድሬዳዋ ከነማ፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከነማ፣አርባምንጭ ከነማ፣ ወልዋሎ አዲግራትን የመሳሰሉት ክለቦች በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ዘንድሮ ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማደግ እየተፎካከረ ያለው አርባምንጭ ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ አጥተዋል፡፡ ተከላካዩ  አበበ ጥላሁን በጉዳት ምክንያት ሦስት ጨዋታዎችን ነው እስካሁን በዚህ ዓመት ያከናወነው፡፡

ሌላኛው የአዞዎቹ ተከላካይ ሳሙኤል አስፈሪም ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ማደረጉ አይዘነጋም፡፡ ተከላካዩ ስቴፋን ባዱ አዬርኬ በጉዳት ምክንያት በርካታ ሳምንታትን ማጣታቸው አይዘነጋም፡፡ የአዞዎችን የኋላ ክፍል በጉዳት ክፉኛ መታመሱ በርካታ ግቦች እንዲቆጠርባቸው አድርጓል፡፡ እስካሁንም 22 ግቦች ተቆጥሮባቸዋል፡፡  አሁን ደግሞ  ወሳኙን አጥቂአቸውን አህመድ ሁሴን በጉዳት አጥተውታል::

አዳማ ከተማ ወሳኝ ተጫዋቹን ቢኒያም ዐይተንን፣ ዳንኤል ደምሴ፣ ፍቃዱ ደነቀው እንዲሁም አድናን ረሻድን ለበርካታ ሳምንታት በጉዳት ያጣ ክለብ ነው:: ወልዋሎ አዲግራት ክለብም በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ በአስከፊ ጉዳት እያሱ ለገሰን እስከ ውድድር ዓመቱ ፍፃሜ አጥተውታል፡፡  ከናትናኤል ዘለቀም በቂ ግልጋሎት ያላገኙት በጉዳት ምክንያት ነው፡፡

ሲዳማ ቡና ክለብ ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ለረዥም ጊዜ ካጡ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት  መክብብ ደገፉ ለረዥም ሳምንታት  ከጨዋታ ውጪ የሆነ ተጫዋች ነው:: በመቐለ 70 እንደርታ በኩል  መናፍ ዐወል፣ ዮናስ ግርማይን፣የአብሥራ ተስፋዬ እና አሸናፊ ሀፍቱ በጉዳት ምክንያት በርካታ ጨዋታ ያመለጣቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የአምናው ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሀሚድ ለረዥም ጊዜያት በጉዳት ማጣቱን የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያስነብባል::

ከባለፉት ዓመታት አንጻር ዘንድሮ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጫዋቾች ጉዳት መጨመሩን ከአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ተናግረዋል:: በእርግጥ ከአሰልጣኝ ይታገሱ ተጨማሪ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት አሰልጣኞች ከጨዋታዎች በኋላ በሚሰጧቸው  አስተያየቶች  የተጫዋቾችን ጉዳት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያነሱት መስማት የተለመደ ነው::

ዘንድሮ ሁሉም የሊጉ ክለቦች በሚባል ደረጃ  በተጫዋቾች ጉዳት ታምሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ በፉክክር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት በውድድር ዓመቱ ተጎጂ ከሆኑ ቡድኖች መካከል ድሬዳዋ ከነማ አንዱ ነው:: ብርቱካናማዎች ዘንድሮ ሁለት ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ሲያጡ አንድ ተጫዋች  ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር ተለያይቷል:: አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የመሐመድኑር ናስር ጉዳት የውድድር ዓመቱን መልክ እንደቀየረባቸው ያሰረዳሉ፡፡

በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ የሊግ መርሀግብሮች 14 ግቦች ካስቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው መሀመድኑር ናስር ከተጎዳ በኋላ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ተቸግረው ተስተውለዋል፡፡ እስካሁንም በአጠቃላይ በ20 ጨዋታዎች 17 ግቦችን ብቻ ማስቆጠራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም  በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው አሰልጣኙ የተናገሩት::

በፕሪሚየር ሊጉ ለሚታየው ተደጋጋሚ ጉዳት ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም የጨዋታዎች መደራረብ እና በቂ የማገገምያ ጊዜ እጥረት እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳው ምቹ አለመሆን ለችግሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት እንደሚጠቀሱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ተናግሯል፡፡ የመጫዎቻ እና የልምምድ ሜዳዎች ምቹ አለመሆን ተጫዋቾችን ለጉዳት እያጋለጠ ነው::ዘንድሮ እስካሁን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች  በድሬዳዋ እና በአዳማ ከተማ ነው የተደረጉት:: እነዚህ ሜዳዎች ደግሞ የሚፈልጉትን የአጨዋዎት ስልት ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ካለመሆኑ ባሻገር በቀላሉ ተጫዋቾችን ለጉዳት እንዳጋለጣቸው አሰልጣኞች ሲናገሩ ተደምጠዋል::

“በቂ የመለማመጃ ቦታ አለመኖር፣ በአንድ የልምምድ ቦታ ሦስት ወይም አራት ቡድኖች ናቸው ልምምድ የሚያደርጉት፤ ለአንድ ቡድን የሚሰጠው የልምምድ ጊዜም አንድ ሰዓት ብቻ ነው:: ይህ ደግሞ በቂ እና የምንፈልገውን ልምምድ ለማሰራት ያስቸግራል”:: ታዲያ  ተጫዋቾችን ለጉዳት የሚያጋልጠው አንደኛው ምክንያት ይህ መሆኑን  የብርቱካናማዎቹ አሰልጣኝ ተናግሯል:: በቀጣይ ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት ሀዋሳ ከተማም ከአዳማ እና ድሬዳዋ የተለየ ነገር እንደማይገጥማቸው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ተናግረዋል::

ዳኞች ለተጫዋቾች ከለላ አለመስጠታቸውም ችግሩ የከፋ  እንዲሆን አድርጎታል:: ዳኛ አላየውም እየተባለ እርምጃ ያልተወሰደባቸው ብዙ ጥፋቶች መፈጸማቸውን ያስታወሱት አሰልጣኙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ድጋሚ በመመልከት አስተማሪ ቅጣት መስጠት መለመድ አለበት ብለዋል- አሰልጣኙ::

ከብሄራዊ ቡድን እና  ከኢትዮጵያ ዋንጫ ባሻገር ዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቁጥር መጨመራቸው የጨዋታ መደራረብን ፈጥሯል:: በዐስር ቀን ውስጥ ሦስት ጨዋታ እየተደረገ ያለ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብቻ መሆኑ የተናገሩት አሰልጣኝ ይታገሱ ለተጫዋቾች በቂ የማገገሚያ ጊዜ  አለመኖር ለተጫዋቾች ጉዳቱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል::

ተጫዋቾች ከባለፉት ዓመታት በተለየ የገጠማቸው ያለተለመደ የመርሀግብሮች መደራረብ ለወትሮ የአካል ብቃታቸው ደካማ እንደሆነ በሚነገርላቸው የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ላይ አካላዊ ዝለት ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪ ከባድ የአዕምሮ ጫናም በቀላሉ እንደፈጠረባቸው ነው የተነገረው::

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች በሙያቸው ብቁ (professionals) አለመሆናቸውን ብዙ የእግር ኳስ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው:: ታዲያ ተጫዋቾች በቀላሉ ለጉዳት ተጋላጭ እንዳይሆኑ እና ጫናዎችን እንዲቋቋሙ ራሳቸው ላይ መሥራት አለባቸው የአሰልጣኙ አስተያየት ነው:: የአካል ብቃታቸውን ማስተካከል፣ የስነ ልቦና ደረጃቸውን እና በራስ መተማመናቸውን ማሳደግ ከጉዳት ለማምለጥ ከተጫዋቾች የሚጠበቅ ተግባር ነው:: አሰልጣኞችም በትክክል ተጫዋቾችን ለጉዳት የሚያጋልጣቸውን መንስኤዎች ምን እንደሆኑ ሊያውቁ ይገባል ነው ያሉት- የድሬዳዋ ከነማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here