ጊዜ እና ልጆች

0
4

ሰላም ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ደህና ናችሁ? ጊዜያችሁን እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? መልካም! ልጆች በዚህ ወቅት የግል ንጽህናችሁን በአግባቡ በመጠበቅ እና በያዝነው የትምህርት ዘመን ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እያሳለፋችሁ እንደሆነ እንገምታለን። ከዚህ ባለፈም ልጆችዬ እውቀታችሁ የበለጠ እንዲዳብር እንደ እድሜ ደረጃችሁ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ማንበብ እና ከቤተሰቦቻችሁ ጋርም ውይይት ማድረግ፣ ያልገባችሁን ነገርም መጠየቅ ይኖርባችኋል::

ልጆችዬ ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ጊዜውን በአግባቡ የሚጠቀም እና መልካም ሥነ ምግባር ያለውን ልጅ ነው:: አዶናይ ዳንኤል ይባላል። በባሕር ዳር አካዳሚ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ወደ አራተኛ ክፍል በአመርቂ ውጤት ተዘዋውሯል። አምና 92 አማካኝ ውጤት አምጥቷል::

አዶናይ ጊዜውን በአግባቡ ያሳልፋል። በተለይም ትምህርቱ ላይ በማተኮር ለክፍል ደረጃው የሚመጥኑ መጻሕፍትን በማስገዛት ፕሮግራም አውጥቶ ያጠናል። ባለው ትርፍ ጊዜም ቤተሰቦቹን ይታዘዛል፣ በሥራም ይረዳል። የአብነት ትምህርት ለመከታተል ተመዝግቧል።

ልጆችዬ ተማሪ አዶናይ ወደፊት ሃኪም መሆን ይፈልጋል:: እዚያ ደረጃ ለመድረስም ጊዜውን በአግባቡ ከፋፍሎ በመጠቀምና በማጥናት በትርፍ ጊዜውም ኳስ በመጫወት እና ቴሌቪዥን በማየት ሰዓቱን በአግባቡ ይጠቀማል፤ ተማሪ አዶናይ ሁሉም ልጆች ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ይላል:: ቤተሰቦቻቸውን፣ ጐረቤቶቻቸውን እና ታላላቅ ሰዎችን ማክበር እና መታዘዝ አለባቸው ሲል ምክሩንም ለግሷል::

 

ተረት

ፍርዱ

ሁለት ድሃ ጎረቤታማቾች ነበሩ:: እነርሱም አንድ በጋራ የሚጠቀሙበት አህያ ነበራቸው:: ከጊዜ በኋላ አንደኛው ሰው ሃብታም ሲሆን ሌላኛው ድሃ ሆኖ ቀረ:: ሃብታሙም ሰው እንዲህ አለ፡- “አህያውን አርደን እንካፈለው” ድሃውም “ለምን? ወይ ገንዘቡን ሰጥተኸኝ አህያውን ውሰድ፣ አለበለዚያ እንደቀድሞው አህያውን በጋራ እንጠቀምበት” አለው:: ባለጠጋውም ሰው “አይሆንም! አህያውን አርደን ሥጋውን ለውሾቼ እወስዳለሁ:: ሥጋውን ለውሾቼ እፈልገዋለሁ” አለ::

ከዚያም ተያይዘው ወደ አንድ ፍርደ ገምድል ዳኛ ሄደው ሃብታሙ ሰው ክሱን እንዲህ ሲል አቀረበ “ይህ አህያ የጋራችን ነው:: ስለዚህ ገሚሱ የእኔ ድርሻ ስለሆነ መካፈል እፈልጋለሁ”። ፍርደ ገምድሉም ዳኛ “አዎ! እረዱትና እንደፈለጋችሁ ተካፈሉት” ብሎ ፈረደ:: አህያውም ታርዶ ሃብታሙ ሰው ግማሹን ሥጋ ለውሾቹ ሲሰጥ ድሃው ሰው አህያው ሲታረድ ከማየት በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻለም::

በሌላ ጊዜ ሃብታሙ ሰው ንብረቱን በሙሉ ከቤቱ አውጥቶ “ቤቴን ላቃጥለው ነው” ብሎ ተናገረ:: “ለምን?” አለ ድሃው ሰው:: “የእኔ ቤት የአንተ ቤት አጠገብ ስላለ አብሮ ይቃጠልብኛል” አለው:: ወደ ቀድሞው ዳኛም ለፍርድ ሄዱ። ፍርደ ገምድሉም ዳኛ “የራሱ ቤት ስለሆነ የፈቀደውን ያድርግ” ብሎ ፈረደ:: በዚህም ሁኔታ ሃብታሙ ሰው የራሱን ቤት ሲያቃጥል የድሃውም ቤት አብሮ ተቃጠለ:: ድሃውም ሰው “ሊከፍለኝ ይገባል” ብሎ ተከራከረ:: ዳኛው “ያንተን ቤት ሊያቃጥል አልሞከረም:: የራሱን ቤት ብቻ ስለሆነ ያቃጠለው ምንም ሊከፍልህ አይገባም” ብሎ ፈረደ::

ቤቱ የተቃጠለበትም ድሃ ሰው ዛፍ ሥር እየኖረ ቤቱ የተቃጠለበትን ሥፍራ አርሶ ሽንብራ ዘራበት:: ሽምብራውም በቅሎ ማሸት ሲጀምር ሃብታሙ ሰው የነበሩት አራት ልጆች መጥተው የሽንብራውን እሸት በሉበት:: ድሃውም ሰው ወደ ሃብታሙ ሰው ሄዶ “ልጆችህ ሽንብራዬን እየበሉብኝ ስለሆነ ሽንብራዬን መልስልኝ?” ይለዋል:: ሃብታሙም ሰው “እሺ ገንዘብ እሰጥሃለሁ” አለው:: ድሃው ሰው ግን “ገንዘብ ሳይሆን ሽንብራዬን ነው የምፈልገው” አለ:: ከዚያም ፍርደ ገምድሉ ዳኛ ዘንድ ሲሄዱ ዳኛው “ሽንብራውን ከፈለገ ሽንብራውን ስጠው” ብሎ ፈረደበት:: ድሃውም ሰው “አዎ! ጨጓራቸውን ዘርግፌ ሽንብራዬን እወስዳለሁ” አለ:: ሃብታሙም ሰው ልጆቹ እንዳይገደሉበት በመስጋት ወደ ሀገር ሽማግሌዎች ሄደ:: ሽማግሌዎቹም ሠላም ለማውረድ ተወያዩ:: ሽማግሌዎቹም እንዲህ አሉ:: “ልጆችህን እንዳይገድል ከፈለግህ የንብረትህን አጋማሽ ልትሰጠው ይገባል” በዚህም ዓይነት የከብቶቹን፣ የበጎቹንና የፍየሎቹን ገሚስ ሰጠው ይባላል::

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች

 

ይሞክሩ

ያገኘውን ሁሉ ይበላል፤ በውኃ ግን ይሸነፋል፤ ምንድን ነው?

ከአንድ ጊዜ ውጭ አይዘራም፤ እስከ ሕይወት ፍጻሜ በአብሮነት ይዘልቃል፤ ታጭዶም ምርት አይሰጥም፤ ምንድን ነው?

አፍ  የለውም ግን ይናገራል፤ እግር የለውም ግን ቀን ከሌት መሄድ አይሰለቸውም፤ መተኛ ሳይኖረው ይተኛል፤ ምንድን ነው?

መልስ

እሳት

ፀጉር

ወንዝ

ነገር በምሳሌ

ስንቁን የተቀማ ነጋዴ፣ ዋግ የመታው ስንዴ፤

ብርታት የሚገኘው ጤና ከመሆን እና ከምግብ ነው፡፡

መተው ነገሬን ከተተው፤

ትግስት ጥሩ ነው፡፡

ለማይሰጥ ሰው ስጡኝን ማን አስተማረው?

ሳይሰጡ መቀበል የለም፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here