ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በጋምቤላ ክልል ከአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በስተምእራብ 850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው:: ፓርኩ በ1973 ዓ.ም በቀጣናው የሚገኙ የዱር እንስሳትን እና መኖሪያቸውን ለመጠበቅ 50 ሺህ 600 ሄክታር ስፋት ይዞ ነው የተከለለው::
በፓርኩ ክልል የሚገኙት የባሮ እና የጊሎ ወንዞች ለዱር እንስሳቱም ሆነ ለእፅዋቱ አስፈላጊ መሠረት ሆነዋል:: ለዱር እንስሳቱ ከጥም መቁረጫነት ባሻገር ለሳር እና ቅጠላ ቅጠል በሎቹ ልምላሜን ፈጥሮ መልሶ የስጋ በሎቹን ከርስ ይሞላል::
የፓርኩ አበዛኛው ክልል ሳር እና ቁጥቁጦ የለበሰ ነው::
የፓርኩ ቀጣና የኑዌር እና የአኝዋክ ነባር ጐሳዎች መኖሪያ ነው:: በስፋቱም ከሌሎቹ በአገሪቱ ካሉት ሁሉ ቀዳሚ ነው:: ለፓርኩ የሚደረግለት የጥበቃ እና እንክብካቤ ስራዎች በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ አለመሆናቸው ነው የተጠቀሰው:: ለዚህም የደን መመንጠር – ለእርሻ ልማት፤ አደን እና ድንበር ተሻጋሪ ተፈናቃዮች በቀጣናው መስፈራቸው በምክንያትነት ተቀምጧል::
በፓርኩ 69 አጥቢ የዱር እንስሳት መኖራቸውም ተረጋግጧል:: ከነዚህ ውስጥ አንበሳ፣ ዝሆን፣ ጐሽ፣ ቀጭኔ፣ ነብር፣ የሜዳ አህያ ይገኙበታል:: ዓእዋፍን በተለከተም 327 ዝርያዎች እንደሚገኙ ተመዝግበዋል- በፓርኩ:: አብዛኛዎቹ እንደየወቅቶች ሁኔታ ኮቦታ ቦታ የሚፈልሱ ናቸው::
በወንዞች የተከበበው የፓርኩ ክልል ከየብስ የዱር እንስሳት ባሻገር በዓሳ ሃብትም መገኛነቱም ተጠቃሽ ነው::
በፓርኩ ክልል የሚገኙ የድር እንስሳት እና አእዋፍ ጥበቃ እና እንክብካቤ የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ አለመሆናቸው ነው የተጠቆመው:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ ወርልድ ዋይድ እና ዊኪፒዲያን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም