“ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች” መጽሐፍ ተመረቀ

0
135

የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

በጋዜጠኛ እና ደራሲ እሱባለው ይርጋ የተጻፈው “ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች” መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢ ደርሷል፤ ትኩረቱን በሰሜኑ ጦርነት ላይ ያደረገው መጽሐፉ ገጠመኞችም ተካተውበታል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለደረባው ጋዜጠኛ እና ደራሲ እሱባለው ይርጋ በሰሜኑ ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች በመገኘት ዘገባዎችን ሠርቷል። በዚህ ወቅት መሰል መጽሐፎች ባልተለመዱበት ይህ መጽሐፍ ለአንባቢ መቅረቡ ታዲያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በምረቃው ላይ የተገኙ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን አስገንዝበዋል።

ዶክተር አንተነህ አወቀ  በባሕር ዳር ዩኒሸርሲቲ የቋንቋና ስነ ጽሑፍ መምህር ናቸው፤ ምሁሩ እንዳሉት ሥነ ጽሑፍን በገጠመኝ መልክ ማቅረብ ብዙም ማሸት የማይፈልግ፣ የታየውን እና የታወቀውን ለአንባቢ ተደራሽ የሚደረግበት ነው።  “ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ይህን መሰሉን አስፈላጊ ስልት እያጣነው መጥተናል፤  ከዚህ አኳያ “ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች” መጽሐፍ አስተማሪነቱ የጎላ ነው” ብለዋል።

ዶክተር አንተነህ እንዳሉት መጽሐፉ  ምልከታን ሰፋ አድርጎ ለማቅረብ ዕድል የሚሰጥ ነው። ይህም የታሪክ ምንጭ ይሆናል። በመሆኑም በተለይ ነገ ታሪክን ለመሰነድ መጽሐፉ አበርክቶው የጎላ መሆኑን በማንሳት በመሰል ጉዳይ ላይ ማተኮር ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከባሕል አኳያ ሙያዊ ሐሳብ የሰጡት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የባሕል ጥናት መምህር ሰሎሞን ተሾመ (ዶ/ር) ናቸው። መጽሐፉ ለታሪክ እና ለባሕል ጥናት ግብዓት ከመሆን ባለፈ ለተማሪዎችም የማሟያ ጽሁፍ ማጣቀሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

እውነታ ከምንጩ የቀረበበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው በማንሳት በአሁኑ ወቅት መሰል አጻጻፍ ያልተለመደ በመሆኑ “ትልቅ ስንቅ ነው” ብለዋል።

ሌላው ሐሳብ የሰጠው ጋዜጠኛ ታዘብ አራጋው መጽሐፉ ሚዛኑን ጠብቆ እውነታ የተገለጠበት መሆኑን ተናግሯል። ይህ ደግሞ የጋዜጠኝነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በመሆኑም መጽሐፉ የሙያው ወርቃማ ሕግ እየተባለ የሚጠራው ‘እውነታ’ መሠረት የሆነበት እና የፖለቲካ ባሕላችንንም በሚገባ ያሳዬ ነው።

የመጽሐፉ ደራሲ ጋዜጠኛ እሱባለው ይርጋ በጦር ግንባር ቆይታው የተመለከታቸውን ክስተቶች እና ገጠመኞች ሚዛናቸውን በመጠበቅ ለአንባቢ ማድረሱን ተናግሯል። የጦርነት ውሎ ዘገባ የጋዜጠኞች የዘገባ ልኬት (ከፍታ) መሆኑን ያነሳው ደራሲው ይህን ዕድል በማግኘቱም “ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥረዋለሁ። ይህን ዕድል ለሰጠኝ አሚኮ ምስጋናዬ የላቀ ነው” ብሏል።

ሙያዊ ሐሳቦችን በማካተት በመጽሐፉ ላይ ያዘጋጀነውን ዳሰሳ በሚቀጥለው ዕትማችን ለንባብ እናበቃለን።

(ጌትሽጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 24  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here