ጋሽ ስብሃት

0
171

ካለፈው የቀጠለ
በጥቅምት 11 ቀን 2017 እትም የመጀመሪያውን ክፍል አስነብበናል።
በመጀመሪያው ክፍል እውቁን ደራሲ፤ መምህርና አርታኢ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔርን የተመለከተ ከልጅነት እስከ ተማሪነት ከዚያም የደራሲነት ዘመኑን ጀምረን ነበር ያቆምነው፤ ቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።
ከፃፈው ያነበበው እጅግ የሚልቀው ጋሽ ስብሃት ከ2ሺ በላይ መፃህፍት እንዳነበበ ይነገራል። ከስብሃት ጋር ስንወያይ ምንም አለማወቃችንን እናውቃለን የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እና በዚህ ዙሪያ ምን እንደሚል ሲጠየቅ የስብሃት መልስ፣ ‘ጥሩ ነው የበለጠ ማወቅ እንዳለባቸው አወቁ ማለት ነው። ማንበብ ስለተማርኩ ደስ ይለኛል፣ እድለኛ ነኝ። ማንበብ ለአንዳንዱ እጣ ነው። ነገር ግን ሳያነቡ ከእኔ የበለጠ ሕይወት የሚኖሩ አሉ። እነርሱ ወደ ሕይወት ታጥቀው ገብተውበታል እና የተሳካ ይኖራሉ። እኛ በቃላት ተደብቀን ነው የምንኖር” ይላል ስብሃት።
“ተንቀሳቃሽ ሕያው ቤተመጻሕፍት ነው” ሲል አድናቆቱን የሚገልፀው ደራሲ ዘነበ ወላ ስለስብሃት በፃፈው መፅሀፉ ውስጥ የስብሃትን አንባቢነት እና የእውቀት ታላቅነት ፅፎታል። በሦስት ቋንቋዎች አሳምሮ ያነባል፣ ይፅፋል። ፈረንሳይኛ አሳምሮ ይችላል። የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ጨምሮ በአራት ቋንቋዎች ይናገራል። በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ። ስለ ስነፅሁፍ፣ ስለፍልስፍና፣ ስለታሪክ፣ ስለስነልቦና እና ስለ ወታደራዊ ሳይንስ አንብቧል።
ስብሃት የሕይወት ፍልስፍናው ከተለመደው ወጣ ያለ እንደሆነ ይታወቃል። ሕይወትን ‘እንደመጣ መኖር’ ነው የእርሱ ፍላጎት። ማንንም አለመጉዳት፣ ልጆቼን መውደድ፣ ጓደኞቼን መውደድ ማክበር፣ ‘…ደግሞ ቀሽም አባባል እንዳይመስልህ እንጂ ሀገሬንም እወዳለሁ’ ሲል አንድ ወቅት ከአለቤ ሾው ጋር በነበረው ቃለምልልስ ላይ ተናግሮ ነበር። ስብሀት በርግጥም ሀገሩን እና ባህሏን እንደሚወድ የብላክ ላይወን ፀሀፊ ሬዱልፍ ሞልቫየር ፅፎታል።
የስብሃት ማስታወሻ በሚል አርእስቶች ላይ ዘነበ ወላ እንደፃፈው፣ ስብሃት ለሁለት ነገሮች አይጨነቅም-ለገንዘብ እና ለልብስ። “ካገኘ ንፁህ ቢለብስ ደስ ይለዋል። ከሌለው ደግሞ ባደፈውም ቢሆን ሀፍረቱን ይሸፍናል። “ጋሼ ስብሃት ገንዘብ በቅቶት አያውቅም፣ “ የሚለው ዘነበ ወላ ስለዚህ ጉዳይ እርሱ ራሱ እንደነገረው ደመወዙን እንደተቀበለ ለተለያዩ እዳዎች ይከፍላል። ለቤተሰቡ የሚበቃውን ይሰጣል። ከዚያ የተረፈውን ቸግሮት ለጠየቀው፣ እርቦት ለለመነው ሁሉ አለመስጠት አይችልም። አንዳንዴ የያዘውን ሁሉ መንገድ ላይ ለተቸገሩት ሰጥቶት ባዶ እጁን ይገባል።
ሬዱልፍ ሞልቫየር ነገረኝ ብሎ እንደፃፈው ትዳር ለመያዝ እቅድ አልነበረውም። በዚህ መካከል ግን የሀገሪቱ አንድ ባለስልጣን ልጅ ጋር በፍቅር ተጣመሩት። ሐና ደሬሳ ትባላለች። የይልማ ደሬሳ ልጅ ናት። ከብዙ ደጅ መጥናት በኋላ የቤተሰቧን ፍቃድ ያገኘው ስብሃት በመጨረሻም ከሐና ጋር በትዳር ተጣምረው መኖር ጀመሩ። ስምንት የፍቅር ዓመታትን ከትዳር አጋሩ ጋር ሲያሳልፉ እያሱ የሚባል ልጅ አፍርተው ነበር። ዘነበ ወላ እንደፃፈው በወቅቱ በሀገሪቱ አብዮት ነበረ ። ሀና ደግሞ የልብ ታማሚ ነበረች። እናም ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ ለመታከም ብትጠይቅ የሚፈቅድ አንድም የመንግሥት አካል ጠፋ። እናም ሀና በሚስጥር ኮበለለች። ነገሩ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለስብሃትም ምስጢር ነበር። ከዚህ በኋላ ነበር ስብሃት አልኮል መጎንጨት የጀመረው። መጠጥን እየጣላ፣ ስካርን የወደደው።
ከዚህ በኋላ ሌሎች ትዳሮችን መስርቶ ልጆችን ማፍራትም ችሏል። ለልጆቹ ልዩ ፍቅር የነበረው መልካም አባት ነበር። ዜና ስብሃት የእርሱን ፈለግ ለመከተል የሞከረች፣ ልጅ ብቻ ሳትሆን የአባቷ አድናቂ፣ አቅብጦ ያሳደጋት ነበረች። ከአፉ ለሚወጡ ቃሎቹ የምትደነቅበት፣ ቀልዶቹ የሚናፍቋት የምትወደው ልጁ ነበረች። ስብሃት በእርሷ ስሜ በክብር ይጠራል፣ ወደፊት ታስከብረኛለች እስከማለት የሚመካባት ልጁ ነበረች። ግን ይህች ተወዳጅ ልጁን በጠዋቱ ሞት ቀማው። ልቡ ተሰበረ፣ በቃ እቀድማታለሁ እንጂ ትቀድመኛለች ብሎ አልጠበቀም። ግን ምን ይሆናል፣ ስብሃት አዝኖ ወደ መፅናናት መጥቷል። እንዳለጌታ ከበደ እንደፃፈው።
ስብሃትን ፈላስፋ አድርገው የሚመለከቱት የተነፈሳት ሁሉ የሚገርማቸው አድናቂዎቹ ብዙ ናቸው። አንድ ወቅት ሰዎች ፈላስፋው እያሉ ሲጠሩህ ደስ ይልሃል? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ለመልስ፣ ‘…በጣም ደስ ይለኛል። አንተም፣ አንችም፣ ሁሉም ሰው ፈላስፋ ነው። ፈላስፋ ማለት እኮ.. እኔ ማን ነኝ? የት ነው ያለሁት? ከየት ነው የመጣሁት? ብሎ የሚጠይቅ ነው። ሕፃን ልጅም ፈላስፋ ነው፣ ‘ አባየ ከየት መጣሁ፣ እሱስ ከየት መጣ? እያለ ይጠይቃል በኋላ ግን ፍልስፍናን አንዳንዶቹ ልክ እንደሙዚቃ ሙያ አድርገውታል…” በማለት የመለሰው ስብሃት በርግጥም ፍልስፍና መማሩም ለዚህ ማንነቱ መስካሪ ነው።
ፅሁፎቹን እንደወረደ ስለሚፅፋቸው ናቹራሊስት ፀሀፊ ነው ይሉታል። ነገር ግን ሬዱልፍ ሞልቫየር እንደፃፈው ስብሃት የሚፅፈው ለማሳተም ብሎ ሳይሆን ለራሱ ብሎ ነበር የሚፅፋቸው። ይፅፋል፣ ከዚያ ለጓደኞቹ ያነብላቸዋል፤ አለቀ ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ሳይጠነቀቅ እንዳመጣለት ስለሚፅፋቸው ስብሃትን እንደ ወረደ ፀሀፊ የሚሉት።
ስለ ወጣትነት ሲናገር “ጥሩ ነው ወጣት መሆን ! ገንዘብ ባይኖርህ ጤናው ይኖርሃል፣ መልክ ባይኖርህ አንጎል ይኖርሃል። ደስታ ባይኖርህም፣ ንዴት ይኖርሃል፤ ፍቅር ባይኖርህ ተስፋ ይኖርሃል፣ እውቀት ባይኖርህ ጉራ ይኖርሃል። መጨቆን ቢበዛብህ ሪቮሉሽን ታስነሳለህ፣ …ሰው ባያውቀውም ታሪክ ይኖርሃል። ስብሃት እርጅናንም እንደ ፀጋ ይቆጥረዋል። ለዚያ በመብቃቱም ደስተኛ እና አመስጋኝ ነበር። እናም ይህ ታላቅ ሰው በ78 ዓመቱ አርፏል። ታዲያ ስለስብሃት እንዲህ በአጭሩ ነግሮ ወይም ተፅፎ ስለማይዘለቅ እኛ በዚሁ ለማብቃት ወደድን፣ ሰላም።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here