ጌትስ ኦፍ ዘ አርክቲክ ብሔራዊ ፓርክ

0
216

በአሜሪካ ሰሜናዊ ቀጣና በአላስካ በታህሳስ 20/1980 እ.አ.አ የተቋቋመ ፓርክ ነው፡፡ ፓርኩ በአሜሪካ ከሚገኙ በስፋቱ ከ “ሬንጂል” ቅዱስ ኤልያስ ብሔራዊ ፓርክ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን 34,287 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡

በአገሪቱ በብሔራዊ ፓርክነት ህጋዊ መሰረት ይዞ እንዲመሰረት በፊርማቸው ያረጋገጡት የወቅቱ ኘሮዘዳንት ጂሚ ካርተር ናቸው፡፡ በፓርክነት ለመቋቋሙ ዋነኛው ምክንያት በርካታ የዱር አራዊት፣ ያልተዳሰሰ ሰፊ ተፈጥራዊ አካባቢ እና የጥንታዊ ሰፋሪዎች መገኛ መሆኑ ነው በቀዳሚት የተጠቀሰው፡፡

የፓርኩ መጠሪያ በሰሜናዊ ዋልታ ግራ እና ቀኝ በቆሙ ተራሮች መካከል አልፎ የበረዶ ንጣፍ ለማየት መግቢያ መሆኑን ለማመላከት የተሰጠው ነው፡፡

ፓርኩ ከየአቅጣጫው ጐብኚዎችን ለማስገባት የሚያስችል የተደላደለ መንገድ የለውም፡፡ መሰረተ ልማት ካልተሟሉላቸው ፓርኮች ቀዳሚ ተጠቃሽም ነው፡፡ ለዚህ አብነት በ2021 እ.አ.አ 7362 ጐብኚዎችን ብቻ ያስተናገደ ሲሆን ግራንድ ካንዬን ብሔራዊ ፓርክ በዚያው ዓመት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዬን ጐብኚዎችን ተቀብሏል፡፡

የፓርኩ ዋና መስሪያ ቤት “ፌይር ባንክ” በተሰኘ ቦታ የከተመ ሲሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጠው የ “ቢትልስ ሬንጀር” ጣቢያ ደግሞ  ከፓርኩ ደቡባዊ ቀጣና ነው ሚገኘው፡፡

አብዛኛዎቹ ጐብኚዎች በፓርኩ ቀጣና ተንቀሳቅሰው ለመመልከት ጓዛቸውን በጀርባቸው ይዘው በሚፈቀድላቸው አቅጣጫ እና ክልል ብቻ መጓጓዝ ግድ ይላቸዋል፡፡ ለዚህም ቀድሞ ለፓርኩ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ማስታወቅ፣ ቦታ ማስያዝ ወይም መመዝገብ የመጀመሪያው ግዴታ መሆኑ  ተጠቁሟል፡፡

በፓርኩ ተራራዎች እና ስድስት ወንዞች ይገኙበታል፤ የፓርኩ ክልል አማካይ የዓየር ንብረት ቀዝቃዛ ሲሆን ዝቅተኛው አማካይ ከዜሮ በታች 41 ዲግሪ ሴንትግሬድ ነው፡፡

በፓርኩ ቀጣና ከሚገኙ የዱር እንስሳት ካሪቡ የበረዶ ላይ በጐች፣ ተኩላዎች፣ የምድር ሽኮኮዎች፣ የሰሜን ጭልፊቶች፤ ጉጉት፣ ንስሮች የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸው ተመዝግቧል፡፡ ከሁሉም በላይ አዳኞቹ ጥቁር ድቦች እንደሚገኙበት በየድረ ገፆች ለንባብ በቅቷል፡፡ ለዘገባችን ዘግሬት ሮድ ትሪኘ፤ ትራቭል አላስካ፣ አርክቲክ ዋይልድ ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here