በባልካን ባሕረ ገብ መሬት ደቡባዊ ጫፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በሰሜን ምዕራብ ከአልባኒያ፣ በሰሜን ከመቄዶንያና ቡልጋሪያ፣ በምሥራቅ ከቱርክ ጋር ድንበር ትጋራለች። 131,957 ስኰር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው መሬቷ ከ10 ሚሊየን በላይ ህዝብ ይኖርባታል። የግዛቷ ኣብዛኛው ክፍል በባሕር የታጠረ ነው ግሪክ።
በግሪክ ደቡብና ምሥራቅ አዋሳኝ አያሌ ደሴቶች አሉ። ደሴቶቹም በርካታ መንደሮችና ከተሞች ተሠርተውባቸዋል። ከከተሞቹ አንዱ ደግሞ አንቲፖሮስ ይባላል። በእዚህም ስፍራ ያለው ታላቅ ያጌጠ ዋሻ የታወቀ ስመ ጥር ቅርስ የጉብኝት ስፍራም ነው። ቀሪዎችም የግሪክ ደሴቶች ለተመልካች ከባሕር ወደ ውጪ ተወርውረው የወጡ ይመስላሉ።
በየጠረፉ የመርከብ መቆሚያ ወደቦች ይገኛሉ። ብዙዎቹ ዜጐቿም መርከበኞች ናቸው።
የጥንት ግሪክ ሥልጣኔ በ1200 ዓ.ዓ ገደማ ካበቃው ከሜሶፖታሚያ ሥልጣኔ እስከ ታላቁ እስክንድር የስልጣን ዘመን ማብቂያ 323 ዓ.ዓ. እንደሚደርስ ይነገራል:: ዓለም ዛሬም በዘርፉ የምትጠቀምባቸው በፖለቲካ፣ በፍልስፍና፣ በኪነጥበብ እና በሳይንስ የተመዘገቡት ዘመን የማይሽራቸው ውጤቶች የጥንታዊ ግሪክ ሥልጣኔ መለያ ናቸው::
በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጥንታዊ ግሪክ ደራሲ ሆሜር አንስቶ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮማ ግዛት እስከ ወደቀበት ድረስ ያለው ትልቁ ታሪካዊ ወቅት ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ያጣመረ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ::
በስልጣኔ፣ በፖለቲካ፣ በኪነጥበብ ፣በሳይንስ እና በፍልስፍና ፈር ቀዳጅ የሆነችው ግሪክ በወቅቱ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በስፋት የሚካሄዱባት ሀገር ጭምር ነበረች::
በጥንታዊቷ ግሪክ ደቡባዊት ክፍል ኦሎምፒያ እ.ኤ.አ በ776 የተካሄዱ ጨዋታዎች ዓለም አሁንም ድረስ በጉጉት የሚጠብቀውን እና በየ4ዓመቱ የሚዘጋጀው የኦሎምፒክ ውድድር መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል:: አሁን ድረስ ኦሎምፒክ በመባል የሚታወቀው ስፖርታዊ ውድድር ስሙንም ያገኘው ግሪክ ውስጥ ከሚገኘው የኦሎምፒያ ተራራ ነው።
የዘመናዊው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መስራች የሆነው ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደ ኩበርቲን ነበር። ባሮን በ393 ዓ.ም በኦሎምፒያ ግሪክ በተካሄደው እና በርካታ ይዘት ባላቸው ጥንታዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በመማረክ ሀገራት ውድድር ለማዘጋጀት የሚፎካከሩበትን የዛሬውን የኦሎምፒክ ጨዋታ ለዓለም ህዝብ አስተዋውቋል::
የኦሎምፒክ ውድድር መስራች የሆነቸው ግሪክ የሠረገላ ውድድር፣ የፈረስ እሽቅድምድም፣ ሩጫ፣ ነፃ ትግል፣ ፔንታሊዮን እና ቦክስ በጊዜው ከተለመዱ የስፖርት ውድድሮች ቀዳሚዎቹ ነበሩ።
እ.ኤ.አ በ1896 የመጀመሪያው እና ዘመናዊው የኦሎምፒክ ጨዋታ በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ነበር የተካሄደው።
ግሪኮች በቀደመው የአውሮፓ ታሪክ ላይ በፍልስፍና፣ በሂሳብ፣ በሥነ ፈለግ ጥናት (አስትሮኖሚ) እና በሕክምና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ሥነ ጽሑፍ እና ቴያትር የግሪክ ባህል የጎላ ገጽታ ሲሆን ለዘመናዊ ድራማ መጀመር ተጽዕኖው የጎላ ነበር።
ግሪኮች በተራቀቁ ሀውልቶቻቸው እና የህንፃ ጥበባቸው ይታወቃሉ። ሶቅራጥስ፣ ፕላቶ እና አርስቶትልን የመሳሰሉ ታዋቂ ፈላስፎች መፍለቂያቸው ግሪክ ናት:: ግሪክ በኦሎምፒክ ጀማሪነቷ እና በጥንት ስልጣኔዋ ለዓለም ካበረከተቻቸው ትሩፋቶቿ ባለፈ ሃገሪቷ ሊጎበኙ በሚችሉ አስደናቂ ቦታዎች የተሞላች ናት:: ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ይተማሉ:: ከመዲናዋ አቴንስ ጀምሮ እስከ 11 ካሬ ማይል ስፋት እስካላት የሃሊኪ ደሴት በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ::ያልተለመደ ስነ-ህንፃ ዲዛይን ያለው የቻኒያ ከተማ የግሪክ አንዱ መገለጫ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የሆሊዉድ ፊልሞች እና ተከታታይ የቲቪ ድራማዎች መቼት በመሆን እያገለገለ ይገኛል::
ሳንቶሪኒ የተሰኘው ከተማ ደግሞ በኖራ በተለበጡ ህንፃዎች፣ለዓይን በሚስቡ ትንንሽ ቀለማት ያሸበረቁ ቤቶች፣ጠመዝማዛ መንገዶች እና ከፍ ያሉ ጉልላቶች የተገነቡበት ነው። ስፍራው ያለው እይታ እና ማራኪ ስነ-ህንፃ ዲዛይን የቱሪስትን ቀልብ ይስባል:: በግሪክ የሚኖአን ሥልጣኔ መነሻዋ የኖሶስ ከተማ በብዙዎች ዘንድ በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከተማ እንደሆነች ይነገራል::
በውስጧ የያዘቻቸው ታሪካዊ እና ጥንታዊ ስፍራዎች ልዩ ያደርጋታል:: ከተማዋ በሄራክሊዮን ዳርቻ ላይ የምትገኝ ሲሆን ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ ሆና ዓመታትን ተሻግራለች:: የአስደናቂው የኖሶስ ቤተ-መንግስት ቅሪቶች የዚያን ጊዜ አስደናቂዊ ስነ-ህንፃ ዲዛይን ክህሎት ማስረጃዎች ናቸው።በተጨማሪም በሄራክሊን በሚገኘው የአርኪኦሎጂ ቤተ መዘክር ጥንታዊ ግሪካዊያን ሲገለገሉባቸው የነበሩ የተለያዩ ዕቃዎችን እና ምስሎችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ስፍራን አካቶ የያዘ ነው::
ከነዚህ ከተሞች በተጨማሪ የማይኮኖስ ባህር ዳርቻ፣በናፍፕሊዮ ያሉ የቬኒስ አርክቴክቸር፣ የኦቶማን አወቃቀሮች፣የጥንት ግድግዳዎች፣ የመካከለኛው ዘመን ሐውልቶች እንዲሁም የዴልፊ ከተማ ባለው ጥንታዊነት እና ታሪካዊነቱ በዩኔስኮ መዘገብ ላይ ሊሰፍር ችሏል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም