ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
የዚህ እትም እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በሰሜን ሸዋ ዞን መርሀቤት ከተማ ውስጥ ነው:: ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውንም በዚህችው ከተማ ተከታትለዋል:: በቀድሞው ጅባትና ሜጫ አውራጃ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ የተለያዩ አከባቢዎች በመንግሥት ሥራዎች አገልግለዋል:: ለ35 ዓመታት በዘለቀው የመንግሥት ሥራቸው ከመምህራን እና ሠራተኞች ደመወዝ ከፋይነት እስከ ሒሳብ ባለሙያነት ብሎም ኃላፊነት ዘልቀዋል::
በ2007 ዓ.ም ከመንግሥት ሥራ በጡረታ የተገለሉት እንግዳችን አሁን ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚሳተፉ የሀገር ሽማግሌ ናቸው:: አንደበተ ርትኡ እና ከሰዎች ጋር ተግባቢ ናቸው ከሚባሉት እንግዳችን ጋር ከግብረ ገብ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ አድርገናል:: የ67 ዓመት አዛውንት እንደሆኑ ከገለጹልን እንግዳችን አቶ ተስፋዬ በየነ ጋር የነበረን ቆይታ የሚከተለው ነው::
መልካም ንባብ!
ግብረ ገብነት ምንድነው?
ግብረ ገብነት የኅብረተሰብ እና የሀገር መሠረት ነው። ግብረ ገብን የተማረ ሰው ሁሉንም ሰው እንደራሱ ይወዳል:: ሰውን በሰውነቱ እንጂ በብሔሩ፣ በሚከተለው ሀይማኖት፣ በሚያራምደው ፍልስፍና፣ በሚናገረው ቋንቋ ወይም በሌላ አይፈርጀውም:: ግብረ ገብ የሆነ ሰው ታላላቆቹን ብቻ ሳይሆን ታናናሾቹንም ያከብራል::
ግብረ ገብ የሞራል ከፍታን የሚያስገኝ ልዩ ጸጋም ነው፤ ግብረ ገብን የሚያውቅ ሰው ትህትናው የላቀ ነው፤ ሰውን እንደራስ ከመውደድ ባለፈ በሰው ማግኘት እና ስኬት መደሰትም የግብረ ገብ ሰው መገለጫው ነው ማለት እችላለሁ::
ግብረገብነት በእርስዎ ዘመን እና አሁን እንዴት ይነጻጸራል?
ምንም የማይገናኝ ነገር ነው ፤ አሁን እኮ ግላዊነት በዝቷል፤ ሰው የራሱን ኑሮ ብቻ በማን አለብኝነት እና እኔ ብቻ በሚል እሳቤ እየኖረ ነው። እስቲ ተመልከት አሁን ማነው የጎረቤቱን ልጅ ሲሳሳት የሚያርም? በየትኛው ትምህርት ቤት ነው መከባበር ያለው? እንደው ደፍረህ ተው ብትል ምን አገባህ አይደለም እንዴ የምትባለው? እስቲ ወደየቤታችን ልመልስህ፤ የሁሉ ነገር መሰረት ቤተሰብ ነው። ግን የትኛው ቤተሰብ ነው ታናሽ እና ታላቅ መረን በለቀቀ ሁኔታ ሲዘላለፉ የሚገስፀው? ቤት ውስጥ ካልተሰራ ግብረ ገብ ከወዴት ይመጣል ?
በኛ ጊዜ እኮ ከቤተሰብ ብታልፍ ጎረቤት እና የአካባቢው ማህበረሰብ አይተውህም፤ ስታጠፋ ገስፆ፣ ከጠማማ መንገድ መልሶ ፣ ቀናውን አሳይቶህ ነው ግብረ ገብን የሚያስተምርህ። እዚህ ጋር አንድ ትውስታዬን ልንገርህ፤ እኛ ልጆች ሆነን ከብቶች እየጠበቅን አንድ ትልቅ ሰው በሰጋር በቅሎ እየጋለቡ ካጠገባችን ሲደርሱ ሁላችን ብድግ አልን፤ ለካስ አንድ ልጅ በተቀመጠበት ነበር፤ እሳቸውም ተገርመው ለመሆኑ የማን ልጅ ነው? ቢሉ የእከሌ ስንላቸው አይ የሱስ ከሆነ ግድ የለም ብለው እኛን መርቀው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ምን መሰለህ ያኔ ልክ ሳትሆን እንኳን ስትቀር ማነህ ሳይሆን የማነህ ነበር የምትባለው፤ ይሄ በውስጡ ብዙ ነገሮችን ይዟል፤ ስላንተነትህ አስተዳደግህ ያወራል እና ነው ።
በኛ ጊዜ እኮ አብዛኛው ልጅ የመማር እድል አላገኘም፤ ያም ቢሆን ግን አብዛኛው የገበሬ ልጅ ስርዓት ያለው ነው። መከባበሩ፣ መፈቃቀሩ፣ አብሮነቱ፣ በጎነቱ እና ሌላውም በመማር ብቻ አይገኝም:: ግብረ ገብነት የማህበረሰብ ስሪት ነው:: በርግጥ ግብረ ገብነትን በሀይማኖት አባቶች ጭምር ነበር የምንማረው፤ መማር አስተዋፅኦ የለውም ልልህ አልፈልግም፤ ግን መማር ብቻ ሳይሆን ባህልን፣ ወግን እና እሴትን የመጠበቅ ቁርጠኝነታችን ከፍ ያለ በመሆኑ ነው የኔን ትውልድ ጥሩ የሥነ ምግባር ሰው ያደረገው::
አሁናዊ ሁኔታችንን ከግብረ ገብ እና ከሞራል ጋር አያይዘው ቢገልጹልን?
ይሄንን ጉዳይ በሁለት መንገድ እንየው፤ አንዱ ከሌላ ዓለም የኮረጅነው የኛ ያልሆነ ይልቁንም የባዕድ ባህል ላይ ሙጥኝ ማለታችን (ተፅዕኖው እንዳለ ሆኖ) እኔ ብቻ የሚል ስግብግብነት ላይ ማተኮራችን፣ አግላይነቱ እና ሌላውም የጎዳን ይመስለኛል። ለምሳሌ እዚህች ሀገር ላይ ሁሉ ነገር አቋራጭ መንገድ ብቻ ነው። ገንዘብ ብቻ። ይሄ ደግሞ የማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ ያስገድድሀል። ለዚህ ደግሞ በየትኛውም ዘርፍ መሪነት ላይ ያለው አካል አርዓያነቱን ካላሳየህ እንደጠመምክ ነው የምትቀረው::
አንድ አባባል አስታወስኩ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የመጀመሪያው ልጅ ትክክል ባልሆነ መንገድ ከሆነ ቅኝቱ ከታች ያሉት እኔም እንደ እከሌ እያሉ ገደል መግባት ነው ነገሩ። ይሄን አባባሌን በሌላ መንገድ ስገልጽልህ እኛ ትውልድን የምንወቅስ ግን ደግሞ የቤት ሥራችንን በአግባቡ ያልሰራን ሰዎች ውጤት ነን:: አሁን ላይ የትኛው ቤተሰብ ውስጥ ነው እስቲ ለልጁ ጊዜ ሰጥቶ የልጁን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የሚገመግም? ሁሉም በራሱ መንገድ ላይ እና እሩጫ ላይ ነው ።ስለዚህ ከመገፋፋት ከመወቃቀስ ያለፈ ሥራ አለመስራታችን ዋጋ አስከፍሎናል ።
አሁን እኮ በየማህበራዊ ሚዲያው የምታየው ነገር ሁሉ ዘግናኝ ነው። እንዴት ሰው ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ስንት ተዓምር መስራት ሲቻል ሲሰዳደብ ይውላል? ይሄ ከየት የመጣ ነው? ጉዳዩን በጥሞና ካልያዝነው በጣም አስቸጋሪ እና አስደንጋጭም ነው::
ታዲያ እንዴት ነው ነገሮቹ መስመር መያዝ ያለባቸው?
በሁሉም ነገር የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል:: ግብረ ገብነት ሰው ከራሱ፣ ከስነ-ፍጥረት እና ከፈጣሪ ጋር ሰላም የሚመሰርትበት ወሳኝ ነገር ነው፤ ይሄ ማለት ከቤት እስከ ጎረቤት አለፍ ሲል በማህበረሰቡ ውስጥ ብሎም ሀገርን መመስረት ነው። እኛም ታዲያ ይሄን ወሳኝ እንደሆነ ከተረዳን፣ አያገባኝምን ትተን በኔነት ስሜት ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣቱ ነው የሚበጀን፤ ዛሬ ላይ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር መንገድ ላይ እንኳን ሸክም የከበደውን የሚያግዝ ሰው እኮ አትመለከትም፤ በርግጥ ምን ያህል ችግር ውስጥ እንዳለን ማሳያው አንድን ሸክም የከበደውን ሰው እባክህ ላግዝህ ብትለው ወይም ብትላት አይ በፍፁም ነው የሚሉህ፤ ምክንያቱም ቢሰርቀኝስ ብሎ እስከ ማሰብ ተደርሷል። ይሄን ያህል መፈራራት እና መጠራጠር በጣም አስገራሚ ነው።
በኛ የልጅነት ዘመን መንገድ እንኳን ስናቋርጥ ታላላቆቻችንን ደፍረን አናቋርጥም፤ አሁን ላይ ግን ተሽከርካሪ ይዞ እግረኛውን የሚገላምጥ እና ሽምጥ የሚጋልበውን አሽከርካሪ ስታይ ከግብረ ገብነት እና ከሞራል ጋር ምን ያህል እየተራራቅን ስለመሆኑ ማሳያ ነው::
የትውልዱን ልዩነት እስኪ በሌሎች አብነቶችም ይግለጹልን?
አሁን ሴት ልጅን በሚገባት ልክ የሚያከብር ሰው እኮ ጠፍቷል፤ እኔ በዚህ እድሜዬ እንኳን በምንም ተዓምር ሴት ልጅ እጄን ስታስታጥበኝ ቁጭ አልልም፤ ለምን መሰለህ አባቴ ሴት ልጅ ቅዱስም ንጉስም የምትወልድ ናት እንዴት ቁጭ ትላለህ ያለኝን መርሳት ስለማልችል ነው ። እስኪ ተመልከት እዚህ ሀገር ስልጣን ላይ ያለው ወገንህ አፍታም ሳይፈጅበት የሀብት ማማን ባልተገባ መንገድ ይቆናጠጣል:: እንዴትም ብታስበው ያለበት ሁኔታ ለያዘው ሀብት የሚያደርሰው አይደለም:: ይሄ ሰውነት እየረከሰ ገንዘብን ወደማምለክ ስንመጣ የሚከሰት እንጂ ጤነኝነት አይደለም:: ታዲያ ከታች ያለው ምንድነው ሊማር የሚችለው?
በቤተ እምነቶች አከባቢ ያለው ግብረ ገብነትስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
እዚያም አከባቢ ያለው ነገር በኔ አተያይ የተበላሸ ነው:: ዛሬ የሀይማኖት መሪ የምንላቸው ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ ለሥጋቸው ወይስ ለነፍሳቸው አድረዋል? ብለን እስክንጠራጠር ድረስ እኮ ነው ህይወታቸው። የሚይዙት መኪና፣ የሚኖሩበት ቤት፣ በዛ ላይ ሥጋዊ ፍላጎታቸው አደባባይ ላይ ወጥቶ እሰጣ አገባ ውስጥ ሲገቡ እንዴት ነው ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል ከእነሱ የሚማረው? በኛ ጊዜ እኮ( በርግጥ እድሉም ባይኖር) ጫማ እንኳን የሚያደርግ የሀይማኖት መሪ አትመለከትም፤ ስለዚህ ስለ ግብረ ገብ ስናወራ ከላይ ያለው ሳይቀር ነው ብልሽቱ፤ አሁን በሁሉም ዘርፍ መሪ የማይከበርበት ሁኔታ ላይ ነን፤ ለዚህ ደግሞ በሁሉም አቅጣጭ ብትመለከት መልካም እሴቶቻችን በተለይ ግብረ ገብነቱ እየጠፋ በመሄዱ ነው ለዚህ የተዳረግነው።
ከግብረ ገብ ጋር ተያይዞ ገጠመኝስ ይኖርዎት ይሆን?
በጣም የሚገርመኝ ነገር ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ህይወትን ቀለል ማድረግ ሲገባን ሌብነት፣ ኢ ሞራላዊ ተግባር፣ ለማይገባህ ነገር አዳርህን ለሴራ ስትጨነቅ ማደር፣ በሰው ህይወት ላይ ስትጨክን እና ስትፈርድ ማየት ያማል:: በሥራ ዓለም ውስጥ እያለሁ ለመጨረሻ ጊዜ የሰራሁት ማረሚያ ቤት ውስጥ ነበር፤ እንደማስታውሰው በሚኖረኝ ትርፍ ጊዜ ታራሚዎችን የመጠየቅ ልምድ አለኝ፤ ባንድ አጋጣሚ ታዲያ ለመስማት የሚዘገንን ታሪክ ሰማሁ፤ ከአንዱ ታራሚ ጋር እየተጫወትን እያለ በምን ምክንያት ወደ ማረሚያ ቤት እንደገባ ስጠይቀው ‘አባቴን ገድዬው’ ሲለኝ ማመን አልቻልኩም:: በምን ምክንያት? ስለው መሬት ለሁሉም ልጆቹ ለማውረስ ወስኖ ለኔ ግን ማውረስ እንዳልፈለገ ስሰማ ነው እንዲህ ያደረኩት ነበር ያለኝ ። እስቲ አስበው እርግጠኛ ባልሆነበት ነገር ለዚያውም አባቱን ለዚያውም ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት ለጥቅሙ ሲል የዘላለም ፀፀት፣ ጥላው እንኳን የሚያስፈራው ሰው ሲሆን እና ተቅበዝባዥ ህይወት ውስጥ ሲገባ ከዚህ በላይ ምን የሚያም ነገር አለ? በዚህ ልክ ሰውነት ረክሶ ጥቅም ሲቀድም ሞራል ሲከስም እኛ ሳይሆን እኔ የሚል ብቻ ሲበዛ አደገኛ ነው። ስለ ግብረ ገብም ሆነ ስለ ሰው ልጆች ሞራል መላሸቅ ሳስብ የማረሚያ ቤቱ ወጣት ሁሌም ከፊቴ ይደቀናል::
ግብረ ገብነት ላይ ማን ምን ይሥራ?
ከግብረ ገብነት ጋር ተያይዞ ትውልዱን መውቀሴ ለመማር ቢያስችለን ብዬ ነው:: የሆነው ይሁን እና አሁን መወቃቀሱ ምንም ጥቅም ስለማይኖረው ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን፤ አያገባኝምን ትተን እንደሚያገባን አምነን በየትኛውም እሳቤ እና እድገት ውስጥ ግብረ ገብነት ወሳኝነቱ የላቀ በመሆኑ መንግሥት የትምህርት ፖሊሲው ላይ አፅንኦት ሰጥቶ በሚገባ አሠራርን መዘርጋት ይኖርበታል። ፊደል የተማረ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ግብረ ገብን የተማረ ትውልድ ማፍራቱ ጠቀሜታው ሁለንተናዊ ነው::
የሀይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጣታቸውን ወደ ሌሎች ከመጠቆም ባለፈ ከስር መሰረቱ ሊያጠፋን የመጣዉን ዓረም በማረም እና የጎበጠውን በማቅናት ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል:: ወጣቱም ቢሆን የታላላቆቹን ምክር በማድመጥ የቀናውን መንገድ መከተል ያስፈልገዋል:: እንዲህ ሲሆን የግብረ ገብነትን እሴት በአግባቡ በመጠበቅ፣ የማኅበረሰብን አንድነት በማጠናከር፣ ትብብር እና አብሮነትን አንድነትንም በማደርጀት የምናልመውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን::
ለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን!
እኔም ሽምግልናዬን አስተውላችሁ ወጣቱን እመክር ዘንድ ስለ ሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ!
(ዮናስ ታደሰ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም