የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በዘላቂነት የማሳደግ እና የምጣኔ ሀብቱ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርና እና ገጠር ልማት የሚመራበት የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የማስፈጸሚያ ስልቶችን በ1994 ዓ.ም ቀርጾ በሥራ ላይ አውሏል። ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ በተከታታይ ዓመታት የልማት ዕቅዶች ሲተገበሩ የቆዩ ሲሆን ዘርፉም በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ዘርፉ ከነበረበት አነስተኛ የእድገት ደረጃ አንጻር ሲታይ የተሻለ የምርታማነት እድገት ከማስመዝገቡም ባሻገር የሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እድገት እንዲፋጠን የመሪነት ሚናውን ተጫውቷል።
ሆኖም የዘርፉ እድገት ከአዳጊ የምርት ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ አልቻለም፤ በዚህም ምክንያት የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠላቸው ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከፍተኛ ነው፤ ለኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ጥሬ ዕቃ በዓይነት፣ በመጠን እና በጥራት ማቅረብ አልተቻለም። በተጨማሪም ለውጪ ንግድ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን አቅርቦት ማሳደግ እና ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አልተቻለም።
ስለሆነም የግብርና እና ገጠር ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ በዘላቂነት ለመጠቀም፣ የግብርናን ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ እና የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት እንዲሁም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት አዲስ የገጠር ልማት ፖሊሲ መተግበር አስፈልጓል፤ ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው 31ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ላለፉት 22 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው ፖሊሲ በአዲስ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተተክቷል።
በመሆኑም ይህ ፖሊሲ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ከፌደራል ጀምሮ በተዋረድ በተሟል መንገድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ ፖሊሲው እስከታችኛው መዋቅር ወርዶ ተግባራዊ መሆን እንዲችል ደግሞ ለሁሉም የግብርና ተዋንያን በሚገባ ማሳወቅ እና ማስገንዘብ ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ በቀድሞው ፖሊሲ (በ1994 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ልማት ሲመራበት በነበረው የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ) ላይ ዋና ዋና ክፍተቶች ተለይተው መፍትሔዎች ሥራ ላይ በዋለው አዲሱ ፖሊሲ እንዲካተቱም ተደርጓል።
አዲሱን ፖሊሲ በተመለከተ ታዲያ ከሰሞኑ የትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፤ በምክክሩ እንደተብራራው ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርታማነት እድገትን ማረጋገጥ፣ ለሀገራዊ የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና እንዲሁም በምግብ ራስን መቻል እንዲረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረግ፣ ግብርናን በማዘመን ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጪ ንግድ በቂ ምርት ማቅረብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን በማሻሻል ዘላቂ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ የደን ልማትና አጠቃቀምን በማሳደግ ሀገራዊ የደን ውጤት ፍላጎትን ማሟላት፣ የስነ – ምህዳር ደህንነቱ የተጠበቀና ኢኮኖሚያዊ አዋጭ የሆነ የግብርና ልማት ዘይቤ በመከተል በአየር ንብረትና በሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች ተፅዕኖ የሚመጣ ተጋላጭነትን መቋቋም የሚያስችል አቅም ማሳደግ፣ በገጠር የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መሠረተ ልማቶችን ማስፋት፣ የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን በማረጋገጥ ብሎም የገጠሩን ነዋሪ ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ህይወቱን ማሻሻል የፖሊሲው ዓላማዎች ናቸው።
የሀገሪቱን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት የሚመጥን የግብርና ምርትን ለማረጋገጥ አዲስ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ነድፎ መሥራት አስፈላጊ ስለመሆኑም በመድረኩ ተነስቷል። ላለፉት 22 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው ፖሊሲ በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ እንዲቀየር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ የፋይናንስ (ካፒታል) ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ የሕግ ማዕቀፎች ውስንነትን ለመፍታት እና የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን ማበረታቻ ማካተት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ዘመኑን የዋጀ እንደሆነም ተመላክቷል።
ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በየክልሉ የተሻሻለውን የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲን የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ፖሊሲውን የማስተዋወቅ መርሀ ግብር አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሕዝብ ሊመግብ የሚችል ግብርና ያስፈልጋል” ብለዋል። ለአማራ ክልል 52 ከመቶ የገቢ ምንጭ ግብርና መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በግብርናው ዘርፍ የሕዝቡን ፍላጎት እና የኢንዱስትሪዎችን ፍጆታ ለማሟላት ፖሊሲውን በመረዳት በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ፖሊሲው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብና ሥርዓተ ምግብ፣ በቂ ግብዓትና የሰው ኃይል እንዲሁም አካታች የተዋንያን ሚና እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለፁት ፖሊሲው የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው። ፖሊሲው ሲወጣ ከ200 በላይ ባለሙያዎች እና ምሁራን ተሳትፈውበታል፤ አዳዲስ እሳቤዎችም ተካተውበታል።
ከዚህ በፊት የነበረውን የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምርታማነትን ማሳደግ፣ በፍጥነት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ከድህነት መላቀቅ ላይ ማዕከል ያደረገ እንደነበር በማንሳት ለውጦች እንደተመዘገቡበትም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ነባሩ ፖሊሲ ለእንስሳት እርባታ ብዙ ትኩረት ያልሰጠ እንደነበር አንስተዋል። አዲሱ ፖሊሲ ታዲያ ዘመኑ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር የተስማሙ እና የሚመጣጠኑ የልማት እሳቤዎችን እንደያዘ አብራርተዋል።
የአርብቶ አደሮችን፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን እና ጥበቃን እንዲሁም የእንስሳት እርባታን ትኩረት የሰጠ መሆኑንም ዶክተር ድረስ ገልጸዋል። በአጠቃላይ አዲሱ ፖሊሲ ካሁን በፊት የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላ መሆኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም የግብርናውን እድገት ለማስቀጠል ፖሊሲውን በተገቢው መንገድ መረዳት እና በአግባቡ መፈጸም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ዶክተር ድረስ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ነው፣ ይህን የሕዝብ እድገት ሊመጥን የሚችል ግብርና ያስፈልጋል። ተሻሽሎ የተቀረጸው አዲሱ ፖሊሲ ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ ምርታማነትን በማስመዝገብ፣ የገጠር መወዋቅራዊ ሽግግርን በማሳካት፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ እና በዘላቂነት በመጠቀም ግብርናው ለምጣኔ ሀብቱ ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት የሚያስችል ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር ድረስ ማብራሪያ ፖሊሲውን በአግባቡ ተግብሮ ወደ ውጤት ለመቀየር የበርካታ አጋር አካላትን ድጋፍ እና ርብርብ ይጠይቃል፤ በመሆኑም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በትውውቅ መድረኩ እንደተናገሩት ፖሊሲው ሲዘጋጅ ያገባኛል የሚሉ አካላት (የምርምር ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ሌሎች አካላት) እንደተሳተፉበት ተናግረዋል።
የቀደመው ፖሊሲ ብዙ ምዕራፎችን ያስጓዘ እና ብዙ ውጤቶችን ያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሁን ላይ ፖሊሲ ለማሻሻል እንዲቻል ወረት እና ስንቅ የሆነው የቀደመው ፖሊሲ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ከፌደራል ጀምሮ በተዋረድ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
አማራጮችን በመጠቀም ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና ስለፖሊሲው እስከ ቀበሌ ድረስ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ዘላቂ የምርታማነት እድገት፣ ያደገ የግብርና ኮመርሻላይዜሽን (ለውጪ ንግድ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርቦት እንዲሁም ገቢ ምርት መተካት)፣ ያደገ የገጠር ነዋሪዎች ገቢ እና የገጠር መዋቅራዊ ሽግግር፣ ያደገ፣ አካታች እና ዘላቂ የግብርና እና ገጠር ልማት፣ ሀገራዊ የምግብ እና ስነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከፖሊሲው የሚጠበቁ ቁልፍ ውጤቶች ናቸው።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም