ግብርናው ወቅቱን እንዲዋጅ…

0
72

ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን በመረዳት መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። በመሆኑም መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ግዥ በመፈፀም የታቀደውን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩን የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል። ለዚህም ማሳያው የፌዴራሉ መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ድጎማ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እያስገባ ይገኛል። የሰብል ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ፣ በፍጥነት ማሰራጨት እና መጠቀም ደግሞ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ግዥ ተፈፅሞ ወደብ ላይ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ፈጥኖ ወደ ክልሎች ገብቶ ለአርሶ አደሮች መሠራጨት ይገባዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ያስችላል።

ይህ ወቅት አብዛኛው አርሶ አደር ማሳውን የሚያዘጋጅበት እና ግብዓት በእጁ የሚያስገባበት  ነው። በበጋው ወራት ማሳውን አርሶ እና አዘጋጅቶ የዝናቡን መምጣት የሚጠባበቀው አርሶ አደር ግብዓት በአቅራቢያው፣ በወቅቱ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኝ ይገባዋል።

አቶ ደመላሽ  ታረቀኝ  በምሥራቅ ጎጃም ዞን የቢቡኝ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረቱ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። አለፍ ሲልም ለገበያ ያቀርባሉ። አርሶ አደሩ ለመኸር እርሻ እየተዘጋጁ እና ግብዓት በእጃቸው እያስገቡ መሆኑን ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን ሦስት ሄክታር ተኩል (14 ጥማድ) የእርሻ መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ደጋግሞ የማረስ እና የማለስለስ ሥራ እያከናወኑ ነው። በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ እና የጥራጥሬ ሰብሎችን በስፋት እንደሚያመርቱ ነግረውናል።

አቶ ደመላሽ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚያገለግል ሁለት ኩንታል ዳፕ እና ሦስት ኩንታል ዩሪያ ከሕብረት ሥራ ማሕበራት ገዝተዋል። በቀጣይም  የሚያስፈልጋቸውን  ቀሪ ግብዓት ለማሟላት ተዘጋጅተዋል። መጠነኛ የሆነ የበቆሎ ምርጥ ዘርም ቀድመው በእጃቸው አስገብተዋል።

አርሶ አደሩ ካሁን በፊት የሌሎች አርሶ አደሮችን ማሳ በውል በመያዝ አምርተው ለእኩል ያካፍላሉ፤  ማሳ  ተከራይተውም ያመርቱ ነበር:: ቢሆንም  አሁን ላይ በተፈጠረው የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ጭማሪ የራሳቸውን ማሳ በዘር ለመሸፈን  ብቻ ጥረት እያደረጉ ነው።

እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ቢመጣም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል። ነገር ግን የምናመርተው የሰብል ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ አሳሳቢ ነው።

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪው አቶ መስፍን ተሰማ የበጋ መስኖ ስንዴ አምርተው ወደ ቤት ማስገባታቸውን ለበኵር ጋዜጣ ገልፀዋል። አርሶ አደሩ በስልክ እንደተናገሩት በሦስት ሄክታር መሬታቸው ላይ የተለያዩ ሰብሎችን ለማምረት ማሳቸውን ደጋግመው እያረሱ ይገኛሉ። በቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ በዋናነት የሚያመርቷቸው ሰብሎች ናቸው።

ማሳን ደጋግሞ ማረስ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ እና ምርቱ እንዲጨምር ያደርጋል ያሉት አርሶ አደሩ በአጠቃላይ ከአሥር ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በዚህ ዓመት ያስፈልጋቸዋል። የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋታቸውን ገልፀዋል። የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ከቀረበ የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻል አመላክተዋል። አሁን ላይ ለመኸር እርሻ የሚያገለግል የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት እየተጠባበቁ ነው።

የአርሶ አደር ደመላሽ ታረቀኝ እና የአርሶ አደር መስፍን ተሰማን የመኸር እርሻ ዝግጅት እና ግብዓትን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ተመለከትን እንጂ በአማራ ክልል የሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮችም ከወዲሁ ዘር በወቅቱ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው።

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017/2018 የምርት ዘመን 642 ሺህ 585 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 25 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል። እስካሁንም 258 ሺህ 275 ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር እንዲሁም 114 ሺህ 873 ሄክታር መሬት ደግሞ በሁለተኛ ዙር ታርሷል።

መምሪያው በሄክታር አማካኝ ምርታማነቱን 39 ኩንታል ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ ነው። አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፓስት) በማዘጋጀት የመሬት ለምነቱን እንዲጠበቅ እየተሠራ ነው። በምርት ዘመኑ በታቀደው ልክ ለማምረት የማሳ ዝግጅት፣ የግብዓት አቅርቦት እና አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ናቸው።

በዚህ ወቅት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እየተሠራጨ እንደሆነ አቶ አበበ አሳውቀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በምርት ዘመኑ በሰብል ለሚሸፈነው መሬት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ በዕቅድ ተይዟል። ከዚህ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ  ሰባት መቶ ሺህ ኩንታል ወደ ዞኑ ገብቷል። 556 ሺህ 651 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ተጓጉዞ ደርሷል። ከዚህም  181 ሺህ 224 ኩንታል ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል።

በተመሳሳይ ዞኑ 30 ሺህ 328 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ያስፈልገዋል፤ ከዚህ ውስጥ 11 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያው በሚሰጠው ምክረ ሀሳብ መሠረት ለእያንዳንዱ ሰብል የሚያስፈልገውን የማሳ ዝግጅት እና ግብዓት በመያዝ የዘር ሥራውን በወቅቱ ማከናወን እንዳለበትም መምሪያ ኃላፊው  አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ፣ ሁለት እጁ እነሴ፣ እነብሴ ሳር ምድር፣ ጎንቻ እና ባሶሊበን ወረዳዎች የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ቢሆንም ሥርጭቱ ግን በሚፈለገው ልክ እየፈጠነ አለመሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል:: በመሆኑም አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ይቀንሳል በሚል የተሳሳተ እሳቤ ሳይዘናጋ ፈጥኖ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል። ይህ ካልሆነ ሰብልን በወቅቱ እንዳይዘራ ከማድረጉ ባለፈ  መጉላላትንም ይፈጥራል ብለዋል።

አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ በመተግበር ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በክልሉ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን መረጃው ያመላክታል። መረጃው አክሎም የምርት ዕቅዱን ለማሳካት የአፈር ለምነትን በሚጨምሩ አሠራሮች፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲሁም የባለሙያዎችን እና የአርሶ አደሮችን ግንኙነት በሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ለግብርና ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች ቀደም ብሎ መሰጠቱን ያብራራል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ለ2017/18 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ከሜካናይዜሽን በተጨማሪ 8 ሚሊዮን 800 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 200 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተሠራ እንደሚገኝ በግብርና ቢሮው የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ለበኵር ጋዜጣ ተናግረዋል።

እስካሁን 3 ሚሊዮን 514 ሺህ 249 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን አረጋግጠዋል:: ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን 629 ሺህ 571 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል። እንዲሁም ቀድሞ ለሚዘራው  149 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ተዘጋጅቷል። በቀጣይም ሌሎች የጤፍ፣ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የቦሎቄ… ምርጥ ዘሮችን የዘር ወቅት ሲደርስ ለማሠራጨት ድልድል እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በተለያዩ ምክንያቶች የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭቱ በታሰበው ልክ ባይሆንም አሁን ላይ ወደ ክልሉ የገባው ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች በቂ ነው። መንግሥት የውጭ ምንዛሬን ተቋቁሞ ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ትኩረት በመስጠት ቀድሞ በመግዛት እና በማሠራጨት እያደረገ ያለው ሥራ አበረታች ነው። ለአብነትም ከ84 ቢሊዮን ብር በላይ ለአፈር ማዳበሪያ በመደጎም ግዥ እየተፈፀመ መሆኑን አብራርተዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭቱን ፍትሐዊ ለማድረግ፤ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የክልሉ ግብርና ቢሮ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ወ/ሮ ሙሽራ ገልፀዋል። ቢሮው የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማከሚያ ኖራ፣ የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካል እንዲሁም የቴክኖሎጂ ግብዓትን በማቅረብ እና በማሠራጨት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም አክለዋል::

በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የግብዓት ሥርጭቱ እንዳይስተጓጎል ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ጥበቃ እየተደረገ ስለመሆኑም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል:: ለዚህም ማግኘት የሚገባን ምርት እንዳያሳጣ ፈጥኖ ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከተሜውን የሚመግበው አርሶ አደር በነፃነት ግብዓት እንዲያገኝ፣ እንዲያርስ እና እንዲያመርት ሁሉም ከጎኑ ሊቆም እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ ለ2017/18 የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መግለፁ የሚታወስ ነው። የመጣው የአፈር ማዳበሪያም በአርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።

መንግሥት ያቀደውን የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ አርሶ አደሩ  በወቅቱ ዘርቶ የተሻለ ምርት እንዲያመርት ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዝያ 27  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here