ግብዓት እና የአርሶ አደሩ ዝግጅት

0
192

“በበጋ ወራት ማሳችንን አለስልሰን፣ በፈጣሪ ዘንድ የዝናቡን፣ በመንግሥት በኩል ደግሞ የእርሻ ግብዓትን መምጣት ስንጠባበቅ ቆይተን ይሄው ዝናቡም ማካፋት፣ ግብዓትም መምጣት ጀመረ” ብለውናል ለበኩር ሐሳባቸውን ያካፈሉ አርሶ አደሮች። በተመሳሳይ እያደገ የመጣውን የአርሶ አደሩን የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት “የተለያዩ ተግባራትን እያከናወንኩ ነው” ብሏል።

አርሶ አደሮቹ ባሰቡት እና በአቀዱት ልክ ባይሆንም ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ግብዓቶችን በፍጥነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ እንደሆነ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ አርሶ አደሮች በስልክ ነግረውናል። መንግሥት በበቂ ሁኔታ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የፈፀመ ቢሆንም የታቀደውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ ውስንነቶች ይስተዋላሉ።

የሰብል ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና መጠቀም ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ግዥ ተፈፅሞ ወደብ ላይ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ፈጥኖ ወደ ክልሉ ገብቶ ለአርሶ አደሩ መድረስ አለበት። ይህም የአርሶ አደሮች ጥያቄ ቢሆንም የሚፈልገውን ያህል ግብዓት ማግኘት አልቻሉም።

ይህ ወቅት ለአብዛኛው አርሶ አደር የዘር ወቅት ነው። ሲያርስ፣ ሲያለሰልስ የቆየውን ማሳውን በዘር መሸፈን የሚጀምረው ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ እንደሆነ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በስልክ ነግረውናል።

አርሶ አደር በላይ ጌታነህ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የፋግታ ለኮማ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረቱ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። “ለመኸር እርሻው ቀድሜ ተዘጋጅቻለሁ” የሚሉት አርሶ አደሩ ያለሰለሱትን መሬት በዘር ለመሸፈን ደግሞ “በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንፈልጋለን” ብለዋል። ለአብነትም ለምርት ዘመኑ ስድስት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ሁለት ጥማድ መሬታቸውንም በበቆሎ ዘር ሸፍነዋል። ነገር ግን በተፈለገው መልኩ ግብዓት ማግኘት እንዳልቻሉ ለበኩር በስልክ ተናግረዋል። ስለሆነም የሚመለከተው አካል ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን ግብዓት እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

ሌላው አርሶ አደር ደረሰ አዱኛ በጃዊ ወረዳ አልኩራንት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቆሎን ጨምሮ

የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታሉ። ሰባት ሄክታር መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ አለስልሰዋል። ለዚህም ከስምንት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ያገኙት አንድ ኩንታል ብቻ ነው። በምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት የተሻለ እንደሆነ ግን ነግረውናል፣ ባለፈው ዓመት እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች በመግዛታቸው ላልተገባ ወጭ ተዳርገው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ጊዜ እና ጉልበታቸውም ሳይቀር ባክኗል።

አርሶ አደር ደረሰ የሚፈልጉትን የምርጥ ዘር ዓይነት እና ያቀዱትን ያህል ማግኘት እንዳልቻሉም ነግረውናል። አራት ከረጢት ምርጥ ዘር ቢፈልጉም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አንድ ከረጢት ብቻ ነው በእጣ ያገኙት።

ሊሙ የተባለው የምርጥ ዘር ዓይነት በአርሶ አደሮች ዘንድ ተፈላጊ ቢሆንም እየቀረበ እንዳልሆነ ነው ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮቹ የሚናገሩት። የታቀደው እና የታሰበው ምርት እንዲገኝ መንግሥት አርሶ አደሩ ለመሬቱ የሚስማማውን ግብዓት ማቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ አስፋው የ2016/2017 የመኸር እርሻን ውጤታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በንቅናቄ  መጀመሩን ነው ለበኩር በስልክ የተናገሩት። የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዞኑ 338 ሺህ 606 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል። እስካሁን በተሠራው ሥራም 210 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን የመምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል:: ከዚህ ውስጥ ስምንት ሺህ ሄክታር የሚሆነው በትራክተር መታረሱን ነው ለበኩር በስልክ በሰጡት መረጃ የተናገሩት። አምስት መቶ ሄክታሩ ደግሞ በዘር መሸፈን ተችሏል።

ብሔረሰብ አስተዳደሩ በምርት ዘመኑ 842 ሺህ 362 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልገው አቅዷል። ከዚህ ውስጥም 498 ሺህ ኩንታል ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን 336 ሺህ 308 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል:: ኃላፊው አክለውም አንደኛ እና ሁለተኛ  ዙር እርሻ ሙሉ በሙሉ የታረሰ ሲሆን ሦስተኛ እርሻ እየታረሰ መሆኑን ተናግረዋል::

ዶ/ር ታደሰ እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ድግግሞሽ፣ የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት፣ በመስመር መዝራት እና የኩታ ገጠም እርሻ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ባልቀረበባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ዓይነት እና የአቅርቦት እጥረትን በተመለከተ አርሶ አደሮች ያነሱትን ጥያቄ ለኃላፊው አንስተንላቸዋል። እርሳቸውም አርሶ አደሮች  የሚፈልጉት የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩን ተናግረዋል። የሚፈልጉትን ዘር ሊተካ የሚችል የበቆሎ ምርጥ ዘር መቅረቡን ግን አስረድተዋል።

“አርሶ አደሩ ሊሙ የተባለውን የምርጥ ዘር ዓይነት ቀድሞ ስለተግባባው ሌሎችን ለመጠቀም ሲቸገር ተስተውሏል። ነገር ግን ይህን ሊተካ የሚችል “ቢ ኤች 661”፣ ዲኬ 77፣  ሾኔ እና ሌሎች አዳዲስ ዘሮችን እያቀረብን ነው” ብለዋል።

በጃዊ እና በፋግታ ለኮማ ያለውን የግብዓት እጥረት የሰላም እጦቱ የፈጠረው ችግር መሆንኑን ኃላፊው አስረድተዋል። አንፃራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ዘግይቶ የተጀመረው በጃዊ ወረዳ በመሆኑ በወረዳው የተመደበው የአፈር ማዳበሪያ ፈጥኖ እንዲደርስ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በቀጣይ የግብርና ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዲችሉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በማንሳት አርሶ አደሮችም ማሳቸውን በወቅቱ በዘር በመሸፈን፣ ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ምርታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ለ2016/2017 የምርት ዘመን ስምንት ሚሊዮን 57 ሺህ 900 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ታቅዶ ግዥ ተፈጽሟል። ከተገዛው ውስጥ ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደብ የደረሰ ሲሆን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ክልሉ ገብቷል። ሦስት ሚሊዮን 936 ሺህ 397 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከዩኒየኖች ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጓጉዟል። እስካሁን ባለው መረጃ ከሦስት ሚሊዮን 547 ሺህ 340 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል:: ምርታማነትን በሄክታር ከ28 ወደ 32 ነጥብ 4 ኩንታል ለማድረስ መታቀዱንም መረጃው ያሳያል።

በተመሳሳይ በ2016/2017  የምርት ዘመን 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል:: የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ መጠን በ2015/2016 የምርት ዘመን ከቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ጋር ሲነጻጸር የዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው።  የግብርናን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከማዳበሪያ ግዥ እስከ አርሶ አደሮች ድረስ ያለውን ሂደት በየደረጃው ያሉ ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት በመሥራት የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽነት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የመጣው የአፈር ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል። መንግሥት ያቀደውን የአፈር  ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ በወቅቱ ዘርቶ የተሻለ ምርት እንዲያመርት የተጀመሩ መልካም ነገሮችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ነው የተጠቆመው።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here