“ግብፅ ግድቡን የሚመታ ራፋል የተባለ የጦር አውሮፕላን  ገዝታ ነበር”

0
102

የተወለዱት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ የጁ ወረዳ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው። የልጅነት ጊዚያቸውን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አሳልፈዋል። የሆነ አጋጣሚ ግን ወደ ሳውዲ እንዲጓዙ ዕድል ሰጣቸው። በሳውዲም ትምህርታቸውን ተከታተሉ፤ አረብኛ ቋንቋን በደንብ ተማሩ እና የአረቡ ሀገራትን በውል እንዲረዱም እድሉን አገኙ።

ግብፅን በደንብ ያውቃሉ፤ በተለይ በሱዳን እና በአካባቢው ለ30 ዓመታት ኑረዋል። በዓባይ እና በኢትዮጵያ ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች ሲሟገቱም እናውቃቸዋለን። የዛሬ የበኩር እንግዳችን የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው።  የህዳሴ ግድብ ግንባታ እና ጫናዎችን በተመለከተ ቆይታ አድርገናል ለአንባቢያንም እንዲህ አቅርበነዋል።

 

በዓባይ ወንዝ ላይ ግብፅ እና ሱዳን ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ሀሳብ ምንድን ነው?

ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ መጠቀም የለባትም፤ የእኛ ብቻ የፈጣሪ ስጦታ ነው  ብለው ነው የሚያስቡት። ስለዚህም ከጥንት ጀምረው   በሚዲያቸውም፣ በወጋቸውም በባሕላቸውም ዓባይ ማለት ፈጣሪ ለእኛ የቸረን ገፀ በረከታችን ነው  ብለው ስለሚያምኑ የኢትዮጵያ ዓባይን መጠቀም ሰላም ይነሳቸዋል። ለምሳሌ አንዲት የግብፅ እናት ልጅ ወልዳ ስታሳደግ ልጇን ጡት ስታጠባው የሚጠባው ወተት ፈጣሪ በዓባይ በኩል እንደሰጠው እየነገረች እያስተማረች ነው የምታሳድገው። ይሄ ዓባይ ውኃ ምን  ያህል በውስጣቸው እንደሰሠርፀ እና ለትውልዱ በምን መንገድ እያስተላለፉ እንደሆነ ያስረዳል።

 

በግብፆች በኩል እንዲህ ከሆነ በኢትዮጵያ  በኩልስ ስለዓባይ ወንዝ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል?

ወደኛ ስንመጣ ዓባይ የራሳቸን ንብረት ሆኖ 86 በመቶ ውኃውን እያዋጣን ግን ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል የሚል የሚያስቆጭ አመለካከት ተጭኖን  ነው ለዘመናት የኖርነው። ይሄ “ከሞኝ  ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” የሆነ አመለካከት ለዓመታት ሰርፆብን እንዲኖር ግብፆች የተለያዩ ሴራዎችን በዘመናት መካከል ሲፈፅሙብን ቆይተዋል። የእዛ ዳፋ በዓባይ ወንዝ ላይ የበይ ተመልካች አድርጎን ዓባይን ይዘን በድህነት እና በጨለማ ለዘመናት እንድንኖር አድርጎናል።

 

ግብፆች በኢትዮጵያ ላይ ሴራ የሚፈፅሙብን በምን መንገድ ነበር?

አንደኛው ሴራ ፈጣሪ በሰጠን ቀናት ሥራ እንዳንሠራ የሴራ  አመለካከት ይጭኑብናል። በግብፅ ውስጥ ያለሥራ የሚያልፍ ቀን የለም ፤ የማይሠራበት ዕለት የለም። ግብፅ ውስጥ የክርስትና እምነት ተከታዮች አሉ። እንደሚታወቀውም የግብፅ አብያተክርስትያናት አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን አብያተክርስትያናት ያስተዳድሩ ነበር።

አንድ ወቅት ከግብፅ  ፓትሪያሪክ ጋር በአረበኛ  ስንወያይ “በእናንት ሀይማኖት በዓመት ስንት ቀን ነው በዓል የምታከብሩት? ሥራ የማትሠሩት?” ብዬ ጠይቄአቸው፤  የሰጡኝ መልስ በእኛ “ ሥራ የማያሠራ በዓል የሚባል የለም” የሚል ነበር። እኔ ጥያቄዬን አስከትዬ “ታዲያ ለምን እኛን በበዓል ምክንያት በዓመት  124 ቀናት ብቻ እንድንሠራ አደረጋችሁ? ለምንስ ይሄንን አስተማራችሁ” አልኳቸው፤ የሰጡኝ መልስ አጭር ነበር “ እናንተማ እንኳን ሠርታችሁ ሳትሠሩም ሰላም እያሳጣችሁን ነው የሚል ነበር። በአጠቃላይ ግብፆች በእኛ ላይ ከሀይማኖት ጨምሮ ብዙ ሴራዎችን ሲያሴሩብን ነው የኖሩት።

ከዚህ ውጭ በግብጽ መሪዎች በኩል የተሠራው ሴራ በምን ይገለፃል? ከታሪክ አኳያ?

የግብፅ መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ሴራና ተንኮል ከመጠምጠም ለአፍታ ተዘናግተው አያቁም። ከጥንት ጀምሮ የግብፅ መሪዎች  ኢትዮጵያ ጠንካራ እንዳትሆን እንዲሁም አንድነት እንዳይኖራት  ያላደረጉት ጥረት ያልፈፀሙትም ሴራ የለም። ለምሳሌ በፕሬዝደንት መሀመድ አሊባሽ አማካኝነት በ1868 እ.አ.አ ዐፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር እንዲጋጩና በመጨረሻም በጀግንነት ራሳቸውን እንዲሰው ግብፆች ከንግሥት ቪክቶሪያ ጋር በመተባበር ያሴሩት ሴራም ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ግብፆች  20ሺህ ወታደሮች አልቀውባቸው ተመለሱ እንጂ በ1875-1876  በኢትዮጵያ ላይ የፈፀሙት የጦር ዘመቻም የሴራቸው ህያው ማሳያ ነው።

ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ የግብጽ መሪዎች የፈፀሙት ደባስ እንዴት ይገለፃል?

ፕሬዝደንት ጋማል አብድል ናስር  በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አልከፍትም፤ ግን ግድብ እገድባለሁ ብሎ ተነሳ። ከዚያም የእኛን  የዓባይን  ወንዝ ተጠቅሞ ውኃውን አከማችቶ አስዋን ግድብን ገደበ። ግብጾች የእኛን ውኃ አከማችተው መጠቀም ጀመሩ።

ሌላው የግብፅ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት ደግሞ ኢትዮጵያ  ስለግድብ ጥናት እያደረገች መሆኑን ሲሰማ በአደባባይ ወጥቶ “ ኢትዮጵያ ግድብ እገነባለሁ ብላ ከተነሳች ኃይሌን አሟጥጬ በመጠቀም ኢትዮጵያን  አጠፋታለሁ” ብሎ ዝቶ ፎክሮ እንደነበረም ታሪክ ምስክር ነው።

ሌላው በሆስኒሙባረከ ዘመን ደግሞ  ግብፅ ከፍተኛ የጦር ጄነራል ወደ ሱዳን አልበሽር  ልካ ኢትዮጵያን ለመምታት  የወታደር ካምፕ የማቋቁምበት ቦታ ይሰጠኝ ስትልም  ጠይቃ ነበር። በወቅቱ አልበሽር የደቡብ ሱዳን አስቸጋሪ ጉዳይ ስለነበረበት ከኢትዮጵያ ጋር ላለመጋጨትም በማሰብ የግብፅን ጥያቄ አልተቀበለውም ነበር። ሌላው በፕሬዝደንት ሙርሲ ዘመን ግንቦት 26 2005 ዓ.ም  እኛ የግድቡን መሰረት ጥለን ነበር። ሙርሲ  ካቢኔአቸውን ጠርተው አምስት ዕቅድ አወጡ፤ በእቅዳቸውም ኤርትራን ከማስታጠቅ ጀምሮ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ኃይሎችን በማጠናከር ኢትዮጵያን እንዲወጉ ማድረግን አካትተው ነበር።

 

እኛ የህዳሴውን ግድብ ግንባታውን ከጀመርን በኃላ የግብፆች የማደናቀፍ ተግባር እስከምን ደርሶ ነበር?

እኛ ግንባታውን ስናካሂድ የግብፅ ፕሬዝደንት አልሲሲ ነበሩ። አልሲሲ የሚያስቡት ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አትገነባውም የሚል የንቀት የትዕቢት ሀሳብ ነበር። ከዚህ ሀሳባቸው የተነሳ በዓለም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ግብፃዊያንን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ዘመቻን ማቀጣጠል እንደ ሁነኛ መሳሪያ መጠቀም ጀመሩ። በአውሮፓ ከ150ሺህ በላይ ግብፃዊ ሀኪሞች አሉ፤ የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች ሲኤንኤን እና ቢቢሲን ጨምሮ በግብፆች ይዘወራሉ፤ በግብፅም ከ4ሺህ በላይ ሚዲያዎች አሉ፤ እንዲሁም 800 ሺህ ግብፃዊያን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ  ተቀጥረው ይሠራሉ። ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም  አልሲሲ የኢትዮጵያን የግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ዓለማቀፍ ዘመቻን መጠቀም ምርጫ አድርገው ተገበሩት። በዚህ ሳቢያ ኢትዮጵያ ለጀመረችው  የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓለም በሯን እንድትዘጋብን አደረጉ። 30 ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር  እንድናጣም ማድረግ ቻሉ።

 

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብስ ሴራውን ለማክሸፍ ምን ዘየደ ?

በዚህ ወቅት በመሪዎች አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንደ ንብ መንጋ ሆ! ብሎ ተነስቶ በጉልበቱም በዕውቀቱም በገንዘቡም ለግድቡ ርብርብ ማድረግ ጀመረ። የሚገርመው ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን የግድቡን ግንባታ 40 በመቶ አስክናደርስ ድረስ የግብፅ መሪዎች “በራሳቸው አቅም አይሠሩትም” በሚል ትዕቢት ውስጥ ነበሩ።

 

ግብፅ የዓለም ሀገራትን ለማሳመን የተጠቀመችው ምንድን ነው?

ግብፆች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የዓለም ሀገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ እና ኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ 560 ጊዜ ስብሰባ አድርገዋል። 1850 ጊዜ በኢትዮጵያ ግድብ ላይ ሴራን የሚጠነስሱ ሴሚናሮችን አካሂደዋል። ከዚህ በተጨማሪም 222 መጽሐፎች በአረብኛ ቋንቋ ተጽፈው በዓለም ተሰራጭተዋል። ይህን ሁሉ ደባ ሲፈፀም ግን በመካከለኛው ምስራቅ የነበሩ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች አረብኛ ቋንቋን በውል የሚረዱ እና የሚናገሩም አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ሴራውን በሚገባ ሊረዱና በጊዜው ሊያከሽፉት አልቻሉም ነበር። ኢትዮጵያ ጫናዎችን እየተቋቋመች የግድቡን ግንባታ ስትቀጥል ግብፅ ሌላ የጉልበት ውጥን አፀደቀች፤  የህዳሴው ግድብ በጦር አውሮፕላን ይመታ የሚል።

ግድቡን የሚመታ ራፋል የተባለ ዘመናዊ የሆነ የጦር አውሮፕላን  በብዙ ሚሊዮን ዶላር ተገዛ። ይህ አውሮፕላን ከግብፅ አስከ ህዳሴው ግድብ ድረስ ያለምንም ተጨማሪ ነዳጅ  ከ2ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ  ግድቡን እንዲያፈነዳ ለአየር ኃይላቸው አዛዣ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጥቶም ነበር። ይሁንና  በብዙ ሚሊዮን ዶላር የገዙት የጦር አውሮፕላን ሳይነሳ  የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት ተካሄደ። ግድቡ ውኃ መቋጠር ሲጀምር  ስጋታቸው እየጨመረ መጣ፤ በመካከላቸውም መከፋፈል ተጀመረ። አሜሪካ የሚኖሩ የግብፅ መንግሥት ተቃዋሚዎችም ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ብቻ ችግሩ መፈታት አለበት እያሉ እንቅስቃሴ ጀመሩ።

ጎን ለጎንም ታሪካዊው ስምምነት መጣስ የለበትም እያሉ ዘመቻም ከፈቱ፡፡ ኢትዮጵያም የቀኝ ግዛት ውልን አልቀበልም እኔ  አልተሳተፍኩበትምና በማለት ፀናች።

ግብፆች ከአፍሪካዊነት ይልቅ አረብነት ላይ ይንጠለጠላሉ እና የዓባይ ውኃን ጉዳይ ወደ ፀጥታው ጉዳይ ምክር ቤት ሲወስዱት መቆየታቸው ይታወሳል። በፀጥታው ምክር ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች የድንበር ግጭት እና መሰል ጉዳዮች ሲሆኑ የውኃ ጉዳይ ግን በታሪክ የፀጥታው ምክር ቤት ቀርቦ አያቅም። ቢሆንም ግን የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ወደ አፍሪካ ህብረት ተመልሳችሁ ጉዳያችሁን ፍቱ የሚል ሆነ።

ግብፆች ግን ተገደው ወደ አፍሪካ ህብረት ከመጡ በኃላ የአሜሪካ እና የምዕራባዊያን ታዛቢዎች ይሳተፉ፤ በበጋም ሆነ በክረምት የዓባይን የውሃ ልቀት የግብፅ ባለሙያ መቆጣጠር አለበት  የሚል ሆነ። ይህ ሀሳባቸው ግን በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነትን አላገኘም።

ሌላ የሚጨምሩልን ሀሳብ ካለ?

በግድቡ ዙሪያ ከሀገራችን ብዙ ይጠበቃል እና ሁላችንም እንበርታ።

ለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን?

እኔም ከልብ አመሰግናለሁ!

 

(ግርማ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here