ግን ለምን?

0
51

በአማራ ክልል ከሐምሌ 1/2017 እስከ መስከረም 30/ 2018 ዓ.ም ድረስ (በሦስት ወር ብቻ) 304 ወገኖች  የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 96ቱ  ሕጻናት ናቸው:: ይህ መረጃ ይፋ የተደረገው ከሰሞኑ የአብክመ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የነጭ ሪቫን ቀንን  ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ሲያከበር ነበር::

በቢሮው የሴቶች ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ደስታ ፈንታ እንደገለጹት ነጭ ሪቫን ወንዶች በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ማንኛውም አይነት ጥቃት  ላለመፈጸምና ጥቃቱ በሌሎች ሲፈፀም ደግሞ ዝም ላለማለት ቃል የሚገቡበት መለያ ምልክት ነው:: ታሪካዊ አመጣጡም በካናዳ ሞንተሪያል ኢንጂነሪንግ ት/ቤት ውስጥ አንድ ወንድ አክራሪ የሴቶች መብት አራማጆች (femenist) ናቸው ያላቸውን 14 ሴቶች መግደሉን ተከትሎ  ነው፡

በተጨማሪም  በአምባገነኑ የዶሚነካን ሪፐብሊክ  መሪ በራፋኤል ቱሪጂሎ የተገደሉትን ሦስት እህትማማቾችን ለማስታወስ ቀኑ ታስቦ እንዲውል መደረጉን ነው የጠቆሙት::

በነጭ ሪቫን ሳምንታት ውስጥ ወንዶችም በት/ቤቶች፣ በሥራ  እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለጥቃት እና ስለሚያስከትለው ችግር በስፋት ይወያያሉ:: ይህም ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት የወንዶች ሚና /አጋርነት/ አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክት ወሳኝ ተግባር ነው::

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ  ተከብሯል::  በዓሉ የዲጅታል ቴክኖሎጅን በመጠቀም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርስን ጥቃት መከላከልና ማስቆም ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነበር የተከበረው::

በዓሉ ዘንድሮ በኢትዮጵያ “ጥቃትን የማይታገስ ማሕበረሰብ ለትውልድ ግንባታ!”  በሚል መሪ ቃል  ከሕዳር 16 እስከ ሕዳር 30 ቀን  2018 ዓ.ም በየደረጃው ባሉ በሁሉም የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች እና የወጣጦች አደረጃጀቶች፣  በሁሉም የፍትሕ አካላት (ዳኞች፣ አቃቢ ሕጎች እና ፖሊስ)… ምክክር ተካሂዷል::

በዓሉ በተለይ የሴት አደረጃጀቶች ጥቃትን እንዲከላከሉና እንዲያወግዙ ሰፊ የንቅናቄ ዘመቻ በማድረግ፣ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር፣ ሀብት በማሰባሰብና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣው መሪ-ቃል መሰረት የሚዲያ ዘመቻ በማካሄድ ተከብሯል::

በእለቱም ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት እንደሚፈፀም   የድርጊቱ ዋና ሰለባዎችም ሴቶች እና ልጃገረዶች መሆናቸውን  የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት በ2008 ዓ.ም  ያወጣውን መረጃ አድርገው ወ/ሮ ደስታ ፈንታ ጠቁመዋል::

ዳይሬክተሯ እንዳብራሩት  ነፍሰ ጡሮች እና  ባለትዳሮች በትዳር አጋሮቻቸው  አካላዊ ፣ ወሲባዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል::

ጥናቱን መነሻ አደርገው ዳይሬክተሯ ስለሴት ልጅ ግራዛት እንዳብራሩት  ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሆኑ ሴቶች መካከል 23 ነጥብ ስድስት በመቶ፣ ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 59 መካከል ከሆኑ ወንዶች ደግሞ 16 ነጥብ ስምንት በመቶ  ሃይማኖታዊ ድጋፍ ያለው ነው ብለው ያምናሉ:: 23 በመቶ ሴቶች እና 28 በመቶ ወንዶች ደግሞ አንድ ሴት ከባሏ ጋር ከተከራከረች፣ ያለ ባሏ ፈቃድ ከቤት ከወጣች፣ ልጆችን ካልተንከባከበች፣ ወይም ከባሏ ጋር ፆታዊ ግንኙነት ለመፈፀም ፈቃደኛ ካልሆነች ብትመታ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ:: 48 በመቶ ሴቶችና ዘጠኝ በመቶ ወንዶች ደግሞ አንዲት ሴት ልጆቿን ካልተንከባከበች በባሏ ብትመታ ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው::

አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል እርዳታ የሚሹ አንድ አራተኛዎቹ ብቻ መሆናቸውን መረጃው አመላክቷል::  አብዛኞቹ (34 በመቶ) ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እርዳታ የሚሹት ከጎረቤቶቻቸው ሲሆን፤ ከሕግ ባለሙያዎች፣ ከሀኪሞች ወይም ከሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት እርዳታ የሚጠይቁት ስምንት በመቶ ብቻ ናቸው::  ከነዚህ መካከል እርዳታ የጠየቁት ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ የሚበልጡ እንዳልሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል::

በአጠቃላይ በቤትና ከቤት ውጭ ፆታን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም ጥቃት የስርጭት ደረጃ አሳሳቢ ከመሆኑም በተጨማሪ ውጤቱም ግለሰብ፣ ቤተሰብና ማሕበረሰብን እንደሚነካም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል::

የሴቶች ጥቃት የሴቶችን የእኩልነት መብት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰብአዊ ማለትም በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ዓይነት ልዩነት/መድልኦ ነፃ የመሆን፣ የነፃነትና የአካል ደኅንነት፣ የመማር፣ የመሥራት፣ የአካልና የአዕምሮ ጤንነት… መብቶችን ይጥሳል::

በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውን እና ተቀብላ ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች እየተጣሱ እንደሚገኙ ወ/ሮ ደስታ ጠቁመዋል::

ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መንስኤያቸው የግንዛቤ ዕጥረት፣ ድህነት እና የኢኮኖሚ ልዩነት፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ ሴቶችና ሕጻናት ባላቸው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ  ጥገኛ መሆናቸው… ድርጊቶቹን ለማስወገድ ተግዳሮት መሆናቸውን  ተገልጿል::  ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ እና አነስተኛ የሥልጠና እድል የሴቶች  የሕይወት አማራጭ እንዲጠብ በማድረግ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹና ጥቃቶቹ እንዲፈፀሙ ተጨማሪ  ምክንያት  መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል::

በመድረኩ ተሳታፊ ከነበሩ የሕብረተሰብ ተወካዮች መካከል የአማራ ክልል የሃይማኖት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ታየ እንደተናገሩት ብዙ ነገሮች ተሸፍነው አይቀሩም:: በአሁኑ ጊዜ እጅግ አስደንጋጭ ጥቃቶች እና ወንጀሎች በሴቶች ላይ ሲፈጸሙ እየተስተዋለ ነው::

የጾታ ጥቃት የሰው ልጅ የአዕምሯዊው ጥንካሬው መድከሙን የሚያሳይበት ነው:: ሰው ከሌሎች እንስሳት በተለየ ማሰብ  እንዲችል ተደርጎ ነው የተፈጠረው፡: ነገር ግን አዕምሮ እንደሌለው የሚፈልገውን ነገር በጉልበት ለማድረግ ሲሞከር ከሰውነቱ ይወጣል:: “ኢትዮጵያ በርካታ ሕዝቧ አማኝ ነው“ ከተባለ ይህ ሁሉ ጥቃት እንዴት ሊፈጸም ቻለ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል:: በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ጠንክረው ተከታዮቻቸው ከእንደዚህ አይነት አስነዋሪ ድርጊት እንዲርቁ ሊያደርጉ ይገባል በመማለት አስገንዝበዋል::

የአማራ ክልል የሴት ሠራተኞች ማሕበራት ፕሬዝዳንት ወ/ሪት ባንችአየሁ ተፈራ  በበኩላቸው በቤት ሠራተኞች ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች እያደረሱባቸው መሆኑን ጠቁመዋል::   በቤት ሠራተኞች ላይ በዋናነት የአካል፣ የጾታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች  የሚፈጽሙባቸው በሕገወጥ ደላሎች፣ በአሠሪዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው መሆኑንም ወ/ሪት ባንችአየሁ  ተናግረዋል::

ደላላሎች ከሚኖሩበት አካባቢ በማታለል ጥሩ ሥራ ታገኛላችሁ” በማለት በሕገወጥ መንገድ ወደ ከተሞች በማምጣት ለአሠሪዎቻቸው ይሰጧቸዋል:: አሠሪዎች ደግሞ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሥራ ያሠሯቸዋል ፣ ሥነ ልቦናቸውን በሚጎዱ ቃላት ይሰድቧቸዋል እንዲሁም  የሠሩበትን ክፍያ በአግባቡ ሳይከፍሉ ያባርሯቸዋል:: ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ  የሠሩበትን ገንዘብ ይወስዱባቸዋል::

በአንዳንዶች ላይ ደግሞ ከደላላ ጀምሮ በአሠሪዎቻቸው(ዘመድም ሊሆን  ይችላል) የአካል ጉዳት (ድብደባ)፣ የመደፈር ጥቃት እንደሚደርስባቸው ነው ፕሬዝዳንትቷ ያስገነዘቡት:: በመሆኑም መንግሥት ለቤት ሠራተኞች ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም ሕገወጥ ደላሎችንም ቁጥጥር እንዲያደርግባቸው አሳስበዋል::

እንደ ፕሬዝዳንትቷ ማብራሪያ በተለይም ወደ አረብ ሀገራት በሕገወጥ መንገድ የሚሄዱ የቤት ሠራተኞች በርካታ በደሎች ይደርስባቸዋል:: ይህን ሁኔታ ለማስተካከል የረቀቀው ሕግ እንዲጸድቅ እየተጠየቀ ነው:: ሕጉ ከጸደቀ የቤት ሠራተኞች ጥቃት ይቀንሳል ብለን እናስባለን::

የአማራ ክልል ሴት አካል ጉዳተኞች ማሕበር ሰብሳቢ  ወ/ሮ ከድጃ ሐሰን በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች በተለየ ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ የሚሆኑት   በውጭ አካል ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ ጀምሮ መሆኑን ነው የጠቆሙት:: የሚደርስባቸውን ጥቃትም ለማን መናገር እንዳለባቸው በትክክል አያውቁም:: በዚህም ችግሩ ተባብሷል::

በተለይም በቅርብ ዘመድ ወሲባዊ ጥቃት የሚደርስባቸውን አካል ጉዳተኞች ሕብረተሰቡ ቶሎ ማመን ስለማይፈልግ ደፋራን  ለሕግ አካላት ማሳወቅ ሳይችሉ እንደቀሩ ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል:: በዚህም በተደጋጋሚ ለጥቃቱ ሰለባ እንደሚሆኑና ይህን ሁኔታም መታገል እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሳቡት::

በአማራ ክልል ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ደስታ ፈንታ እንደገለጹት በክልሉ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች እና ድጋፍ ተደርጎላቸዋል:: ከነዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት  የሥነ ላቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ወደ ተሀድሶ ሴንተር ተልከዋል::

ፆታን መሰረት  ያደረገ ጥቃት ለመከላከልና ለማስወገድ የአንድ ተቋም ብቻ ተግባር ባለመሆኑ የተለያዩ የትብብርና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመፍጠር ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ የሚሰጡ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች እንዲስፋፋ፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማረፊያና ማገገሚያ ማዕከላት ቁጥራቸው ከፍ እንዲል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ወ/ሮ ደስታ የገለጹት::

በመድረኩ ባለድርሻ አካላት ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች የሴት አደረጃጀቶች የሴትን ልጅ ጥቃት ለማስቆም መረባረብ እንዳለባቸው ተጠቁሟል:: በተለይም  ጥቃት አድራሾቹ ወንዶች በመሆናቸው  የወንድ አጋርነት ያስፈልጋል:: በዚህም በቤተሰብ፣ በቅርብ አጋር፣ በጓደኛ፣ በዘመድ የሚደረሱ ጥቃቶችን ወንዶች መከላከል እንዳለባቸው ዳይሬክተሯ ጥሪ አስተላልፈዋል::

 

መረጃ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ – መንግሥት (1995)ምን ይላል?

 

  • አንቀፅ 25 ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን እና በጾታ ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት ያለአድልዎ እኩል የሕግ ጥበቃ መብት

እንዳላቸው ይገልፃል፡፡

  • አንቀፅ 34 (1-2) ለወንዶችና ለሴቶች በጋብቻ ጉዳዮች ላይ እኩል መብት ይሰጣል፡፡
  • አንቀፅ 35 መንግሥት የሴቶች መብቶች በመጠበቅ በኩል በንቃት እንዲሳተፍ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ዝርዝር አካትቷል (የጋብቻ፣ የንብረት፣

የወሊድ፣ አዎንታዊ እርምጃ፣ የግል ጥበቃ፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ቅጥር/ክፍያ፣ በልማት ፖሊሲዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ)  እኩል መሆኑን ያሳያል፡፡

  • አንቀፅ 89 ላይ እንደተቀመጠው ሴቶች ከወንዶች እኩል በሁሉም ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ይኖራቸዋል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር  29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here