…ግን ይሳካል?

0
115

ሁላችንም ከራሳችን ጋር የንግግር ጉባኤ አለን። የውስጥ ንግግር ማለት በጭንቅላታችን ወይም በልቦናችን ውስጥ ከራሳችን ጋር የምናደርገው የማያቋርጥ ውይይት ነው። ድምፅ አውጥተን ሳንናገር፣ ሐሳቦችን የምናውጠነጥንበት፣ ክስተቶችን የምንተረጉምበት እና ለራሳችን የምንሰጠው ግብረ መልስ ነው።

የውስጥ ንግግራችን የስሜታችን መሪ ነው። ቀመሩ እንዲህ ነው። ሐሳብ (የውስጥ ንግግር)  ስሜት ይፈጥራል  ስሜት ደግሞ  ተግባርን  ይወልዳል። ከዚያ  ውጤት ይቀጥላል። ሀሳባችን በስሜታችን በኩል ተቆጣጥሮን ወደ ድርጊት ያስገባናል። በቀጥታ ከውጤታችን ጋር ይተሳሰራል።

አብዛኞቻችን በቀን ውስጥ ከ6ሺህ እስከ 8ሺህ የሚደርሱ ሐሳቦችን እናስባለን:: ከእነዚህ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ውስጣዊ ንግግሮች ናቸው:: ይህ በዝምታ የሚካሄድ ንግግር የጤናችን፣ የደስታችን እና የስኬታችን ዋና መሐንዲስ ነው:: በዚህ መጣጥፍ የውስጥ የንግግራችንን ሳይንሳዊ መሠረት፣ በሰውነታችን ላይ የሚያመጣውን ለውጥ እና እንዴት አድርገን ወደ ስኬት መሣሪያነት እንደምንቀይረው እንመለከታለን::

የውስጥ ንግግር ዝም ብሎ የሚመጣ ሐሳብ አይደለም። በአእምሯችን ውስጥ የሚካሄድ የነርቭ ሴሎች ግንኙነት ውጤት ነው:: በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ኢታን ክሮስ   ባሳተሙት ቻተር የተሰኘ መጽሐፍ አእምሯችን እንዴት ከራሱ ጋር እንደሚነጋገር በዝርዝር አስቀምጠዋል::

እንደ ክሮስ ገለጻ  የሰው ልጅ አእምሮ ዲፎልት ሞድ ኔትወርክ (DMN) የሚባል ክፍል አለው:: ይህ ክፍል ስራ ፈትተን ስንቀመጥ ወይም በትኩረት የምንሰራው ስራ በማይኖርበት ጊዜ ንቁ ይሆናል:: በዚህ ጊዜ ነው አእምሯችን ወደ ትናንትናው ስህተት እየተመለሰ የሚቆጨው ወይም ስለ ነገው ስጋት እያወራ የሚጨነቀው:: ይህ ቻተር ወይም የአእምሮ ወሬ ካልተገራ የአእምሮን ኃይል የመበታተን እና የጭንቀት ሆርሞኖችን (እንደ ኮርቲሶል ያሉ) የመጨመር ኃይል አለው::

የነርቭ ሳይንስ ሊቃውንት እንደሚነግሩን አእምሯችን ልክ እንደ ፕላስቲክ ሊቀረጽ የሚችል ነው:: ዶ/ር ሪቻርድ ሃንሰን በታዋቂው “ሀርድዋየሪንግ ሀፒነስ” መጽሐፋቸው አእምሮአችን ለነገሮች የሚሰጠውን ምላሽ በልምምድ መቀየር እንደሚቻል ያስረዳሉ:: ራሳችንን ሁልጊዜ የምንነቅፍ ከሆነ አእምሯችን ለትችት እና ለውድቀት የተጋለጠ እንዲሆን ነርቮቹን ያገናኛል:: በአንጻሩ አዎንታዊ እና ገንቢ የውስጥ ንግግር ካዘወተርን አእምሯችን ለደስታ እና ለስኬት የተዘጋጀ ይሆናል:: አእምሯችን ለውጥን ለመቀበል ሁልጊዜ ዝግጁ ስለሆነ፤ ዛሬ የምንጀምረው አዎንታዊ ንግግር ነገ አዲስ ማንነትን ይፈጥርልናል::

እነዚህን አሉታዊ ንግግሮች ማሸነፍ የሚቻለው መኖራቸውን በመረዳት ብቻ ነው:: በፔንሲልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲን ሴሊግማን  “ለርንድ ኢፕቲሚዝም” በተሰኘው  መጽሐፋቸው ብሩህ ተስፋ ወይም ኦፕቲሚዝም መማር የሚቻል ክህሎት መሆኑን አረጋግጠዋል:: ሴሊግማን የማብራሪያ ዘይቤ  የሚሉት ጽንሰ ሐሳብ አንድ ሰው ለደረሰበት ችግር የሚሰጠው የውስጥ ማብራሪያ ሕይወቱን እንደሚወስነው ያሳያሉ:: ችግሮች ጊዜያዊና ሊፈቱ የሚችሉ እንደሆኑ ለራሳችን የምንነግር ከሆነ፣ አሸናፊ የመሆን እድላችን ሰፊ ነው:: አክብደን ካየናቸው አይፈቱም።

በስፖርት ስነ ልቦና የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አትሌቶች ከመወዳደራቸው በፊት “ትችላለህ፣ ተዘጋጅተሃል፣ ትኩረት አድርግ” የሚል የውስጥ ንግግር ሲጠቀሙ፣ ውጤታማነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል:: በተቃራኒው ስለ ሽንፈት የሚያወሩ አትሌቶች የጡንቻዎቻቸው መኮማተር እና ትኩረት ማጣት ያጋጥማቸዋል:: ይህ የሚያሳየው አእምሯችን ለራሱ የሚነግረው ነገር በቀጥታ ለጡንቻዎቻችን ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ነው::

የውስጥ ንግግራችን አእምሮአችንን ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነታችንን ይነካል:: ሜዮ ክሊኒክ  ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው አዎንታዊ የውስጥ ንግግር ያላቸው ሰዎች የሚከተሉት ጥቅሞች አሏቸው። ረጅም እድሜ መኖር፣ ዝቅተኛ የልብ ምት እና የተረጋጋ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም፣ ከከባድ ሕመሞች የማገገም ፍጥነት ይኖራቸዋል::

ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አእምሯችን “አደጋ ላይ ነኝ” ወይም “አልችልም” የሚል ንግግር ሲያሰላስል፣ ሰውነታችን የጭንቀት ሆርሞኖችን ይረጫል:: እነዚህ ሆርሞኖች ለረጅም ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ሲቆዩ የደም ቧንቧዎችን ያጠባሉ፣ የምግብ መፈጨትን ያውካሉ፣ እንዲሁም እንቅልፍ ይነሳሉ:: በአንጻሩ “ተረጋጋ፣ ሁሉም ያልፋል” የሚል ንግግር ሲኖር፣ ሰውነታችን ኦክሲቶሲን እና ዶፓሚን የተባሉ የደስታ ሆርሞኖችን ያመነጫል:: እነዚህ ሆርሞኖች ሕዋሳቶቻችን እንዲታደሱና ጤናማ እንድንሆን ይረዱናል:: በመሆኑም የውስጥ ንግግር ለጤና የምንወስደው በነፃ የሚገኝ መድኃኒት ነው::

ይህ ከሆነ ታዲያ ንግግሮቻችንን እንዴት እንቀይራቸው? የውስጥ ንግግርን ለመቀየር የሚከተሉትን  ሳይንሳዊ ስልቶች አሉ። ራስን በስም መጥራት የመጀመሪያው ነው። ፕሮፌሰር ኢታን ክሮስ እንደሚመክሩት ለራስህ ስትናገር “እኔ” ከሚለው ይልቅ የራስህን ስም ተጠቀም ይላሉ። ለምሳሌ፦ “እኔ ለምን ተጨነቅሁ?” ከማለት ይልቅ “አቢብ ሆይ! ለምንድነው የምትጨነቀው? ትችላለህ እኮ!” በል ይላሉ። ይህ ዘዴ በእኔና  በጭንቀቴ መካከል ርቀት ይፈጥራል:: ይህ የስነ-ልቦና ርቀት ችግርህን ከውጭ ሆኖ እንደሚያይ ጓደኛ እንድናየውና የተሻለ መፍትሄ እንድናገኝ ይረዳናል።

ሁለተኛው ለነቃፊው ድምፅ ስም  ማውጣት ነው። ውስጣችን የሚመጣውን አሉታዊ ድምፅ እንደ እኛ  አካል ሳይሆን እንደ ሌላ ሰው መመልከት ነው:: ለምሳሌ “ተጠራጣሪው ድምፅ መጣ” ወይም “ነቃፊው መጣ” ማለት:: ይህ ድምፁን የመቆጣጠር ኃይል ይሰጠናል:: ድምፁን ስንለየው የእኛ ማንነት እንዳልሆነና ዝም ብሎ የሚያልፍ ሐሳብ እንደሆነ እንረዳለን።

“ግን” የሚል ስትራቴጂን መጠቀም ሦስተኛው ነው። አንድ አሉታዊ ሐሳብ ሲመጣ “ግን” በሚል ቃል መቀጠል ጥሩ ነው:: ለምሳሌ “ዛሬ ስራዬ አልተሳካም፤ ግን ከስህተቴ ተምሬ ነገ በተሻለ መንገድ እሰራዋለሁ” ስንል አእምሯችን ከአሉታዊው ነገር ተነስቶ ወደ መፍትሄው እንዲጓዝ ያደርገዋል::

ራስን እንደ ጓደኛ ማየት የመጨረሻው መፍትሔ ነው። ዶ/ር ክሪስቲን ኔፍ በጻፉት “ሰልፍ ኮምፓሽን” መጽሐፍ፣ ብዙዎቻችን ለጓደኞቻችን የምንሰጠውን ርህራሄ ለራሳችን አንሰጥም ይላሉ:: ጓደኛችን ቢሳሳት የምንለውን ቃል ለራሳችንም መንገር እንዳለብን ይመክራሉ:: ለራሳችን ደግ መሆን ድክመትን ሳይሆን ጥንካሬንና በራስ መተማመንን ይገነባል::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here