በዓለም አቀፍ ደረጃ 31 ዩኒቨርሲቲዎች የግእዝ ቋንቋን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፐኤችዲ ድረስ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም አዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሐን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች የቋንቋውን ምስጢራዊነት ተረድተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ አካሂዶት በነበረው የግእዝ ዐውደ ጥናት ላይ ተሳታፊ የነበረው የሦስተኛ ዓመት የግእዝ ተማሪው ዘላለም በላይ ግእዝን መማር “ራስን በእውቀት ማብቃት፣ ታሪክን ማወቅ፣ ሀገርን በቅጡ መረዳት፣ በጥናት እና በምርምር ቀዳሚ መሆን ነው” ይላል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ሀገራት ዛሬ ላይ ለግእዝ ልዩ ትኩረት የሰጡት ቋንቋውን ለመግባቢያነት ለማሳደግ ሳይሆን የዓለም ምስጢር በግእዝ መሰነዱን የሚያሳይ ፍንጭ በማግኘታቸው እንደሆነ ያምናል፡፡ ግእዝ በታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባቢያ ቋንቋ የነበረ፣ እና ቋንቋው ከብሔር እና ከሃይማኖትም በላይ የጋራ መግባቢያ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
“እኛ ግእዝ እንደሌሎቹ የተደበቀ ዕውቀትን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን የምንማረው ቋንቋው እና ፊደሉ በአግባቡ ተመልሶ የኢትዮጵያ መታወቂያ እንዲሆን ነው“ ሲልም ገልጿል፡፡እሱም የሦስተኛ ዲግሪውን እየተማረ ጎን ለጎን ቋንቋውን ለማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች እያስተማረ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ተረክበ ያሳቡ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ ግእዝ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው ይላል፡፡
ታላላቅ መጻሕፍት ሁሉ የተጻፉት በግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማወቅ እና ለመረዳት እንደሚያግዝ ያምናል፡፡ለዚህም ሁሉም ለቋንቋው ትኩረት ሰጥቶ መማር እንዳለበት አሳስቧል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግእዝ ከአብነት ትምህርት ቤቶች ውጪ በመደበኛ ትምህርት መሰጠት መጀመሩ ደግሞ ለቋንቋው ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገረው፡፡በሕጻንነት ዕድሜ ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲወስዱ መደረጉ ደግሞ በጊዜ ሂደት ቋንቋው ተናጋሪ እንዲኖረው፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራትም ወሳኝ መሆኑን ነው የጠቆመው፡፡
በለይኩን ብርሐኑ (ዶ/ር) የተጻፈው የግእዝ መማሪያ መጻሕፍ ግእዝ ኢትዮጵያ ካሏት የተፈጥሮ ሐብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ማንነት ታውቆ እና ተጠንቶ ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረው በግእዝ ቋንቋ ሰነዶች እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡
የግእዝ ማደግ የቋንቋ፣ የፊደል፣ የሥነ ጽሑፍ አጠቃቀም በእጅጉ እንዲሻሻል ፋይዳው ከፍተኛ መሆንንም በማከል አስቀምጧል፡፡
ከኢትዮጵያ በላይ ለመጠቀም ያለ የሌለ አቅማቸውን እየተጠቀሙ ያሉት ግን የውጭ ሀገራት መሆናቸው ሁሉም በቁጭት ሊመለከተው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም በጽሑፋቸው አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ባለማስተዋል ውኃ እንዳጣ አትክልት ጠውልጎ የሚታየውን የግእዝ ቋንቋ ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አካቶ መሥጠት መፍትሔ መሆኑን ጽሑፉ ጠቁሟል፡፡
ግእዝ ከዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ አማራ ክልል በተያዘው ዓመት ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በመሰጠት ላይ ነው፡፡ ይህም ለቋንቋው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተጠቆመው፡፡ተማሪ ጌጤነሽ አበባው ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆና ብትቆይም በዚህ ዓመት ግን ከምትኖርበት ገጠር ቀበሌ ወጥታ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን በቡሬ ከተማ እያስቀጠለች ነው፡፡
የሁለት ዓመታት ቁጭትን በውስጧ ያኖረችው ተማሪዋ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብም ዕቅድ አላት፡፡በተመሳሳይ ወደ ትምህርት ስትመለሰ የግእዝ ትምህርት መጀመሩ እንዳስደሰታት ጌጤነሽ ተናግራለች፡፡ ግእዝ ቀድሞ መጀመር እንደነበረበት የተናገረችው ተማሪዋ ትምህርቱ ለሥነ ምግባር፣ ለፊደላት አጠቃቀም እና ለተጨማሪ ዕውቀት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብላለች፡፡
ትምህርቱ በግል ትምህርት ቤቶች ከዚህ ቀደም ይሰጥ እንደነበር በማንሳት አሁን ላይ ደግሞ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መሰጠቱ ለግእዝ ቋንቋ ዕድገት እና መስፋፋት ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆን ነው ሐሳቧን ያካለችን፡፡በተያያዘ በክልሉ የሚገኙ ዞኖች የግእዝ ትምህርት በውጤታማነት እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ደግሞ አንዱ ሲሆን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የግእዝ ትምህርትን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በወቅቱ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በትግል ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የሙከራ ትምህርት እንደተጀመረ የነገሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ቡድን ባለሙያ ወርቁ አባተ ናቸው፡፡እነዚህ ተማሪዎች አሁን ላይ አምስተኛ ክፍል ደርሰዋል፡፡ ቁጥራቸውም 252 ናቸው፡፡በተያዘው የትምህርት ዘመን ደግሞ በሁሉም ወረዳዎች ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም 60 ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ትምህርቱን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎችም ቁጥር ስምንት ሺህ 107 የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፤ ለውጤታማቱ ደግሞ 67 የግእዝ ትምህርት መምህራን መቀጠራቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ግእዝ በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶ መሰጠቱ የሚበረታታ ቢሆንም የመምህራን እጥረት መኖሩን ግን በስጋትነት ጠቁመዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ታዲያ ወረዳዎች አሁንም ማስታወቂያዎችን እያወጡ መምህራን ለማሟላት ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡የግእዝ ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን የመማሪያ መጻሕፍት አቅርቦት በተለያዩ አማራጮች እየቀረበ መሆኑንም አክለዋል፡፡እስካሁን የመማሪያ መጻሕፍት ይዘቶችን በወረቀት በማባዛት ለተማሪዎች ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የመጽሐፍ ሕትመቱ ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ትምህርት ቤቶች እንደሚደርስም ነው የነገሩን፡፡በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግእዝ መምህርና ተመራማሪ ሙሉቀን አንዷለም (ዶ/ር) “ትምህርት የሚሰርጸው ከሕጻንነት ጀምሮ ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ የግእዝን ፊደል የማያውቀው የማኅረሰብ ክፍል ሰፊ ነው፤ ከታች እንዲጀመር መደረጉ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው” ብለዋል፡፡
ግእዝ ለአንድ ብሔር መግባቢያነት ብቻ የተፈጠረ ቋንቋ እንዳልሆነ መረዳት እንደሚገባም ዶ/ር ሙለቀን አስገንዝበዋል፡፡ግእዝ የኢትዮጵያውያን ብቸኛው የጋራ ቋንቋ ነውም ብለዋል፡፡ ግእዝን ለአንድ ሃይማኖት ብቻ አድርጎ ማሰብም ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ምስጢር… የሰፈረው እና ተደብቆ የሚገኘው በግእዝ ቋንቋ በተጻፉ ሰነዶች ላይ መሆኑን ቀድሞ መረዳት ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ቋንቋውን ከብሔር እና ከሃይማኖት ባሻገር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተረድቶ መማርም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ዶ/ር ሙለቀን አስገንዝበዋል፡፡ኢትዮጵያውያን ግእዝን ወደ ብሔር እና ሃማኖት ለጥፈው የገፉት ቋንቋ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሌላ ከውጭ አካል እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ኢትዮጵያዊ ምሁራንን በራሳችን ዕውቀት በማፍራት የሀገራችንን ታሪክ በራሳችን ሰዎች ለማጥናት በዘርፉ ኢትዮጵያዊ ምሁራንን ማውጣት የማያጠያይቅ ጉዳይ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡ ለዚህም አሁን ለግእዝ የተሰጠው ትኩረት እንዲሰፋ እና እንዲያድግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም የግእዝ ቋንቋን በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡የአሁኑ ትውልድ የመንፈሳዊ እና የታሪካዊ ቅርስ ምስጢር የሚገለጥበትን ግእዝ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አቀናጅቶ እንዲማር መደረጉ በጥልቀት ለመማር እና ለመመራመር በር የሚከፍት መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሰብዕ ፋካሊቲ ዲን ዋልተንጉስ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ለዘመናዊው የዕውቀት መዝገብ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው ግእዝ አሁንም በሚፈለገው ልክ እንዲያድግ እና እንዲሰፋ ሁሉም ትኩረት መስጠት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
ግዕዝ በአማርኛ
ውእቱ – እርሱ
ይኢቲ – እርሷ
ውእቶሙ – እነርሱ (ለወንዶች)
ውእቶን – እነርሱ(ለሴቶች)
አነ – እኔ
ንሕነ – እኛ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


